2022-07-03 14:21:47
ጭንቅላቱ ዞሯል
የቄራ ሞተረኞች ወግ ነው :-
አንድ ወጣት ሞተረኛ በአንድ ምሽት ከከተማ እየወጣ ነው፡፡ ጭር ባለ አስፋልት ላይ እንደ ጀት እየበረረ ላሰበበት ቀጠሮ ለመድረስ ይከንፋል፡፡ ምንም እንኳን ጃኬት ደርቦ ቢለብስም ከፊት ለፊቱ የሚመጣው ነፋስ ደረቱንና ፊቱን እየገረፈው ተቸገረ፡፡ የለበሰው ጃኬት ደግሞ ከበስተኋላው ፈር ያለው ስለነበር ይሞቃል፡፡ ከፊት ግን ከምንም ሊያስጥለው አልቻለም፡፡ ምርር ሲለው ሞተሩን ከመንገድ ዳር ሱቅ አጠገብ አቆመ፡፡ ጃኬቱን አውልቆ አዙሮ ለበሰና አንዱን ጎረምሳ ‘እባክህ የጃኬቴን ዚፕ ከጀርባ ዝጋልኝ’ አለው፡፡ ጎረምሳው እሺ ብሎ ዞሮ የተለበሰውን ጃኬት እስከ ላይ ድረስ ግጥም አድርጎ ዘጋለት፡፡
አሁን ነፋሱ ደረቱን አይመታውም፡፡ ስለዚህ በላቀ ፍጥነት መብረር ጀመረ፡፡ ከከተማ ከወጣ በኋላ የበለጠ መክነፍ ጀመረ፡፡ ድንገት ግን ከፊቱ ደርቦ ለማለፍ የሚሞክር መኪና ብቅ አለበት፡፡ ራሱን ለማዳን ከመንገዱ ወጥቶ ሲበርር ሞተሩ ከቁጥጥሩ ውጪ ነበርና ተወርውሮ ከገደል ማዶ ያለ እርሻ ውስጥ ወደቀ፡፡ ከዚያ የሆነውን አያስታውስም፡፡ በዚያ ጨለማ እርሻ መካከል የሞተር ጩኸት የሰሙ ሰዎች ወደ ሥፍራው በሩጫ ሲደርሱ ሞተሩ በአንድ ወገን ሞተረኛው በሌላ ወገን ወድቀዋል፡፡ ተጯጯኹ፡፡ በዚያ ጨለማ ወጣቱን ከወደቀበት ሊያነሱት ተረባረቡ፡፡
‘ተርፎ ይሆን? አዪ የሰው ነገር’’
‘ምን አስሮጠው እስቲ!’’
‘ይሄ ሞተር ካልተከለከለማ መች ሰው ይተርፋል?’’
‘ኸረ እስቲ ወሬውን ትታችሁ ሆስፒታል ውሰዱት ‘
ቦታው በጫጫታ ተናወጸ።
በዚህ መካከል አንዱ በጨለማም ቢሆን የተጎጂውን አለባበስ አተኩሮ አየና ‘ኸረ ጭንቅላቱ ዞሮአል!’’ ብሎ ጮኸ ‘አዎ ዞሮአል አንተ እንዴት ቢወድቅ ነው ተባባሉ’’ አንዱ ወጣት እስቲ ከተስተካከለ ብሎ ተቻኩሎ አንገቱን ለማዞር ሲታገልም ምስኪኑን ሞተረኛ አንገቱን ቀጨው!
ነገሩ ያስቅም ያሳዝንም ይሆናል :: "ጭንቅላቱ ዞሯል" ብሎ መቅጨት ግን በሀገር የመጣ ችግራችን ይመስለኛል፡፡
ሰዎች በራሳቸው አስተሳሰብ ፣ አመለካከት ልክ ሆነው ሳለ እኛን ስላልመሰሉ ብቻ በግድ አዙረን የምንቀጫቸው ብዙ ናቸው፡፡ አንድ ሰው በአንተ አቅጣጫ ስላልዞረ : አንተ ያልከውን ስላላለ ብቻ ተሳስቷል ማለት አይደለም፡፡ አንተ የወደድከውን ስላልወደደ ፣ አንተ የጠላከውን ስላልጠላ ተሳስቷል ብለህ በግድ ልትቀጨው መሞከር የለብህም፡፡
"ወደ ምሥራቅ ተመልከቱ" የሚለው አዋጅ አልፎ አልፎ ወደ ምዕራብም ወደ ሰሜንም ወደ ደቡብም ማየት አንደሚቻል ያሳያል:: ለተለያዩ አቅጣጫዎች ክፍት መሆን የግድ ነው::
የነጻነት ታጋዩ ኔልሰን ማንዴላ ፕሬዝዳንት ከሆኑ በኋላ በአሜሪካን ሀገር ባደረጉት የመጀመሪያ ጉብኝት ወቅት በኒውዮርክ ሲቲ ኮሌጅ አዳራሽ ይፋዊ ቃለ መጠይቅ ላይ ለአንድ ጋዜጠኛ የሰጡት መልስ አይረሳኝም፡፡
ጋዜጠኛው ‘እንደ ፍልስጤሙ ያሲን አረፋት ፣ ጋዳፊ ፣ ካስትሮ ያሉ በጨቋኝነታቸው የታወቁ ሰዎች ጋር ወዳጅነት ያሳያሉ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሰዎች የደቡብ አፍሪካ መሪ ቢሆኑ ደስ ይልዎታል ወይ?’’ ብሎ ጠየቃቸው፡፡ኔልሰን ማንዴላ ዘና ብለው የተናገሩት የመጀመሪያ ዐረፍተ ነገር ሕዝቡን አስቁሞ ያስጨበጨበ ነበር፡፡
‘አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ከሚሠሯቸው ስኅተቶች አንዱ የእነርሱ ጠላቶች የእኛም ጠላቶች መሆን አለባቸው ብለው ማመናቸው ነው’’ እኛ የጠላነውን ያልጠላ ፣ እኛ የደገፍነውን ያልደገፈ ሰው ማንጓጠጥ የእኛ ሀገር አንዱ ሕመም ነው፡፡ እኛ የወደድነውን የቀለም ዓይነት ፣ እኛ የለበስነውን አለባበስ ፣ እኛ የምንወደውን ምግብ ፣ የእኛን አስተዳደግና ባሕል ሳይቀር ካልተከተለ በንቀት እንፈርጀዋለን፡፡ እኛ ካሰብነው አቅጣጫ ውልፍት ያለ ሲመስለን ጭንቅላቱ ዞሯል ብለን የምንቀጨው ብዙ ሰው አለ፡፡
አንድን ነገር ስንደግፍም ስንቃወምም እስከ ጥግ ነው፡፡ የወደድነውን ወገን ስናመሰግን የፈጣሪ ያህል እንከን አልባ አድርገን ነው [ፈጣሪ እንኳን በትሕትና ‘ኑ እንዋቀስ’ ‘እስቲ ፍረዱ! ያላደረግኩት ምን አለ?’ ብሏል] ፣ የጠላነውን ስናንኳስስ ደግሞ ትንሣኤ እንዳይኖረው አድርገን ነው፡፡ ስለዚህ በእኛ ሀገር ወይ ጠላት ወይ ወዳጅ ከሚል ውጪ ምንም የሥራ መደብ የለም፡፡ ሚዛናዊነት ፣
ግሬይ ዞን ፣ ‘አንተም ተው አንተም ተው’ ብሎ ነገር ሥፍራ አጥቷል፡፡ መሃል ሰፋሪ በሁለት ጥይት ይሞታል የሚለው ድሮ የቀረ ነው፡፡ በአሁን ዘመን አካሄድ መሃል ሰፋሪ በላውንቸር ይሞታል፡፡
የአጼ ኃይለ ሥላሴ ንጉሣዊ ቤተሰብ አባል የሆኑት ልዑል አስፋ ወሰን አስፋ ወሰን ዐሥራት ለአንድ የጀርመን ቴሌቪዥን ጣቢያ ሲናገሩ ‘ከሁለት ሺህ የአፍሪካ ቋንቋዎች ውስጥ Opponent ለሚለው ቃል ተስተካካይ ትርጉም ያለው ቃል የለም፡፡ አፍሪካውያን የምናውቀው ወይ ወዳጅ ፣ ወይ ጠላት ነው እንጂ በሁለቱ መካከል ላለ ሰው መጥሪያ ስም እንኳን የለንም’ ብለው አስደንቀውኝ ነበር፡፡ እርግጥ ነው ቃል እንኳን አናጣም ብለን መሟገታችን አይቀርም፡፡ በተግባር ግን ከወዳጅና ጠላት በቀር መካከል ላይ ላለ ሰው ሥፍራ የለንም፡፡ ወይ እኛ ወደ ገመትነው አቅጣጫ መዞር አለበት፡፡ አለዚያም ጭንቅላቱ ዞሯል ብለን
እንቀጨዋለን፡፡
ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ
ዩቲዩብ ቻናል➠ https://m.youtube.com/channel/UCNjEKBSeBmsSGrHdlN3aSpQ
ፌስቡክ ገጽ➠https://m.facebook.com/EMislene
ቴሌግራም ቻናል➠ https://t.me/EMislene
ኢንስተግራም➠https://www.instagram.com/egziabher_meslene28/
ቲክቶክ ➠ https://vm.tiktok.com/ZMdm9g2TR
ድረ ገጽ➠ https://www.debregelila.org
┈┈┈┈••●◉❖◉●••┈┈┈
1.5K viewsedited 11:21