Get Mystery Box with random crypto!

ርስትህን ለማላገጫ አሳልፈህ አትስጥ የኢዩኤል ዘመን ወይም ትንቢተ ኢዩኤል የተጻፈበት ዘመን የታወ | El OlaM ▣

ርስትህን ለማላገጫ አሳልፈህ አትስጥ

የኢዩኤል ዘመን ወይም ትንቢተ ኢዩኤል የተጻፈበት ዘመን የታወቀ አይደለም። በመጽሐፉ የትኛውም ንጉሥ በስም ስላልተጠቀሰ ወይም ምንም ፍንጭ ስላልተሰጠ፥ ወይም በመጽሐፉ ውስጥ የተጻፈው በተከታታይ ዓመታት የተፈጸመ የአንበጣ ወረራ በሌሎች መጻሕፍት እና ታሪኮች ውስጥ ስላልተዘገበ፥ ኢዩኤል ስለኖረበት ወይም መጽሐፉ ስለተጻፈበት ዘመን የሚታወቅ ነገር የለም። ስለ ካህናት፥ ስለ እግዚአብሔር ቤት፥ ስለ መቅደስ አገልጋዮች፥ ስለ ይሁዳ፥ ስለ ጽዮን፥ ስለ ኢየሩሳሌም ስለሚናገር ኢዩኤል ያገለገለው በኢየሩሳሌም ወይም በይሁዳ ሆኖ ከኢየሩሳሌም መወረርና ከመቅደሱ መፍረስ በጣም ቀድሞ ሳይሆን አይቀርም። በትንቢቱ ውስጥ ከልመናዎቹ አንዱ ርስቱን ለማላገጫ አሳልፎ እንዳይሰጥ ነው።

አስፈሪው ነገር፥ ኋላ ግን ሰጠ። እግዚአብሔር ርስቱን በገዛ እጁ አሳልፎ ሰጠ። (ዳን. 1፥2)

ርስቱ ሕዝቡ ነው፤ ርስቱ ሕዝቡ ነን።

ኢዩ. 2፥12-17
12፥ አሁንስ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ በፍጹም ልባችሁ፥ በጾምም፥ በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ። 13፥ ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ፤ አምላካችሁም እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ፥ ቍጣው የዘገየ፥ ምሕረቱም የበዛ፥ ለክፋትም የተጸጸተ ነውና ወደ እርሱ ተመለሱ። 14፥ የሚመለስና የሚጸጸት እንደ ሆነ፥ ለአምላካችሁም ለእግዚአብሔር የእህልና የመጠጥ ቍርባን የሚሆነውን በረከት የሚያተርፍ እንደ ሆነ ማን ያውቃል? 15፥ በጽዮን መለከትን ንፉ፥ ጾምንም ቀድሱ፥ ጉባኤውንም አውጁ፥ 16፥ ሕዝቡንም አከማቹ፥ ማኅበሩንም ቀድሱ፥ ሽማግሌዎቹንም ሰብስቡ፥ ሕፃናቱንና ጡት የሚጠቡትን አከማቹ ሙሽራው ከእልፍኙ፥ ሙሽራይቱም ከጫጉላዋ ይውጡ። 17፥ የእግዚአብሔርም አገልጋዮች ካህናት ከወለሉና ከመሠዊያው መካከል እያለቀሱ፦ አቤቱ፥ ለሕዝብህ ራራ፥ አሕዛብም እንዳይነቅፉአቸው ርስትህን ለማላገጫ አሳልፈህ አትስጥ፤ ከአሕዛብ መካከል፦ አምላካቸው ወዴት ነው? ስለ ምን ይላሉ? ይበሉ።

ይህ መዝሙር ብዙ ተንበርክኬ የሰማሁትና አብሬ የዘመርኩት ነው። አድምጡት፤ ዘምሩት፤ ጸልዩት።

በደልን ይቅር የሚል፥ ዓመጻን የሚያሳልፍ፥
ከጠላት ሊያድናቸው በሕዝቡ ላይ የሚሰፍፍ፥
እንዳንተ ያለ አምላክ ምሕረቱ የበዛ፥
ቅዱሳንንህ ሲሰደዱ መከራውም ሲበዛ።

ርስትህን ለማላገጫ አሳልፈህ አትስጥ፤
የተቀደሰ መቅደስህን ለጠላት አታስረግጥ።

የእግዚአብሔር እድል ፈንታ ተጽፏል ሕዝቡ ነው፤
ሊያመልከው ሊያገለግለው ከግብጽ አገር ያፈለሰው፥
አርነቱን በባርነት ሊተካ የሚከጅለው፥
ይገባኛል የሚል ማነው? ሕዝቡ የእግዚአብሔር ነው።

እስከዛሬ ከብረሃል በአሕዛብ ተፈርተሃል፤
የጠላትን እርግማን በረከት አድርገሃል፤
ያሳዳጁን ፈረሶች በባህር አስጥመሃል፤
በክንድህ ተከላክለህ ርስትህን ጠብቀሃል።

(መዝሙር በተስፋዬ ጋቢሶ)

ዘላለም መንግሥቱ