2022-07-22 15:38:44
መዝሙር በቀዳሚ ገብረ ከሐምሌ ፲፯ እስከ ሐምሌ ፳፫
(በ፪/ዩ) በቀዳሚ ገብረ እግዚአብሔር ሰማየ ወምድረ ወኵሎ ፈጺሞ አዕረፈ በሰንበት ወይቤሎ ለኖኅ አመ አይኅ ግበር ታቦተ በዘትድኅን አነ አቀውም ኪዳንየ ዘምስሌከ ለዓለም ከመ ዳግመ ለምድር ኢያማስና በአይኅ ከመ አሀባ ለምድር ሣዕረ ሐመልማለ ክረምተ ወሐጋየ ዘርዐ ወማዕረረ ዝኬ ውእቱ ጸጋሁ ለእግዚአብሔር በአማን ኢይኄሱ ቃሎ ዘነበበ።
ትርጕም፦
በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ፈጠረ ሁሉን ፈጽሞ በሰንበት አረፈ በጥፋት ውኃ ጊዜ ኖኅን የምትድንበትን መርከብ ሥራ አለው እኔ ዳግመኛ ምድርን በጥፋት ውኃ እንዳላጠፋት ለዘለዓለም ኪዳኔን ከአንተ ጋር አቆማለሁ/አጸናለሁ ለምድር ሣርን ልምላሜን ክረምትን በጋን ዘርና መከርን እሰጣት ዘንድ ኪዳኔን ከአንተ ጋር አጸናለሁ የእግዚአብሔር ስጦታው ይህ ነው በእውነት የተናገረውን ቃሉን አይዋሽም።
የዕለቱ ምንባባት፦
ቲቶ ፫፥፩ - ፍ፤
፩ጴጥ ፬፥፮ - ፲፰፤
ግብ ፳፰፥፩ - ፲፯፤
ወንጌል፦ ማቴ ፳፬፥፴፮ - ፍጻሜ፤ ወይም ማር ፮፥፵፯ - ፍጻሜ፤
ቅዳሴ - ዘኤጲፋንዮስ
የዕለቱ ምስባክ፦
እስመ ትቤ ለዓለም አሐንጽ ምሕረተ፤
በሰማይ ጸንዐ ጽድቅከ፤
ኪዳነ ተካየድኩ ምስለ ኅሩያንየ። መዝ ፹፰፥፪
ትርጕም፦
ምሕረትን ለዘለዓለም አጸናለሁ ብለሃልና፤
ጽድቅህ በሰማይ ጸና፤
ከመረጥኋቸው ጋር ቃል ኪዳን አደረግሁ።
ምሥጢር፦
አሐንጽ ያለውን እገብር ሲል ነው ቸርነትን ለዘለዓለም አደርጋለሁ ማለት አጸናለሁ ብለሃልና "አጽንዐ ምሕረቶ እግዚአብሔር ላዕለ እለ ይፈርህዎ - እግዚአብሔር በሚፈሩት ላይ ምሕረቱን አጸና" እንዲል መዝ ፻፪፥፲፩
ቸርነትህ እንደ ሰማይ ጸንቶ ይኖራል። ይህም በምድር ላይ የቱንም ያህል መናወጥ ቢደረግም ሰማይ እንደማይናወጥ የኃጢአታችን ብዛት በኖኅ ዘመን የገባልልንን ኪዳን እንዲናወጥ የማያደርገው መሆኑን መናገር ነው። በደመና የሚሳለው ምልክት እስካሁን አልተለወጠምና።
አንድም ቸርነትህ በፈጢረ ፀሐይ ጸና። በናቡከደነጾር ያሳይበታል "አነ ዘአሠርቅ ፀሐየ - ፀሐይን የማወጣ እኔ ነኝ” እስከ ማለት ደርሶ ነበርና
አንድም ሊቃነ መላእክትን ሠራዊተ መላእክትን በመፍጠር ጸና። "ገባሬ መላእክት አበ ኵሉ ዓለም - የመላእክት ፈጣሪ የዓለሙ ሁሉ አባት" እንዲል።
ትቤ ያለበት ነው ለአባትነት ከመረጥኋቸው ከወዳጆቼ ከባለሟሎቼ ከአብርሃም ከይስሐቅ ከያዕቆብ ጋር መሐላን ተማማልሁ ብለህ ነበር ማለት ይህንን መሐላ አስብ አስበህ ይቅር በለን ማለት ነው።
ወይም፦
ሐወፅካ ለምድር ወአርወይካ፤
ወአብዛኅኮ ለብዕላ፤
ፈለገ እግዚአብሔር ምሉዕ ማያተ። መዝ ፷፬፥፱
ትርጕም፦
ምድርን ጐበኘኻት አረካሃትም፤
ብልጥግናዋን እጅግ አበዛህ፤
የእግዚአብሔር ወንዝ ውኆችን የተመላ ነው።
ምሥጢር፦
ይህችን ዓለም በረድኤት ጐበኘሃት፤ ቦ ኢየሩሳሌምን ከሰባ ዘመን በኋላ ጐበኘሃት ማለት የዘሩባትን እንድታበቅል የተከሉባትን እንድታጸድቅ አደረግሃት።
የዚችን ዓለም ቦ የኢየሩሳሌምን ብዕለ ሥጋዋን ማለትም አዝርዕቱን አትክልቱን አበዛህላት፤ ቦ ለምእመን ብዙ ጸጋ ክብር የሚገኝበትን ልጅነትን ሰጠሃት።
እግዚአብሔር የፈጠራቸው አራቱ አፍላጋት ኤፌሶን ኤፍራጥስ ግዮን ጤግሮስ ውኃን የተመሉ ናቸው።
774 views12:38