Get Mystery Box with random crypto!

ተወዳጁ ድምጻዊ የክብር ዶክተር አሊ ቢራ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ ***** ድምጻዊ አሊ ቢራ በአ | EBC(Ethiopian Brodcasting Corboration(EBC)

ተወዳጁ ድምጻዊ የክብር ዶክተር አሊ ቢራ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ
*****

ድምጻዊ አሊ ቢራ በአዳማ አጠቃላይ ሆስፒታል በህክምና ሲረዳ የቆየ ሲሆን ዛሬ ምሽት ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱን ከኦሮሚያ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በኢትዮጵያ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ አሁን ለደረሰበት ደረጃ ባለውለታ ከሆኑት አንጋፋ ከያኒያን መካከል ዓሊ ቢራ በቀዳሚነት ከሚቀመጡት ይመደባል። በበርካታ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጭምር በተጫወታቸው ሙዚቃዎቹ የሚታወቀው አርቲስት ዓሊ ቢራ በተለይ በአፋን ኦሮሞ በተጫወታቸው በርካታ ሙዚቃዎቹ ዘመን ተሻጋሪ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆን በመቻሉ የቋንቋው ምልክት እስከመሆን ደርሷል ይሉታል በርካቶች።

በግንቦት 1940 ዓ.ም በድሬዳዋ የተወለደው አርቲስት ዓሊ ቢራ፣ በህጻንነቱ የተለያዩ የአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ ሙዚቃዎችን እያደመጠ ማደጉን እና ለትምህርት ቤት ጓደኞቹ እና ለቤተሰቦቹ በማንጎራጎር የሙዚቃ ህይወቱን መጀመሩን በተለያያ ጊዜ ከሰጣቸው ቃለ ምልልሶች መረዳት ይቻላል።

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በድሬዳዋ ከተማ ፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በአዲስ አበባ ካቴድራል ትምህርት ቤት ተከታትሏል። አሜሪካ ሀገር በሚገኘው የሳንታ ሞኒካ ኮሌጅም የሙዚቃ ትምህርቱን ተምሯል።

አርቲስት ዓሊ ቢራ በ1954 ዓ.ም የኦሮሞን ሙዚቃ ለማስተዋወቅ ዓላማ ያደረገ የባህላዊ ሙዚቃ ቡድን “አፍረን ቀሎ”ን በመቀላቀል ነበር የሙዚቃ ስራውን የጀመረው። በቡድኑ ውስጥ ሌላ ዓሊ የተባለ ልጅ በመኖሩ ሁለቱን ለመለየት መጀመሪያ ከሚያዜመው "ቢራ ዳ ባሬ" ዘፈን ተወስዶ "ዓሊ ቢራ" የሚለው ሰም ተሰጠው። ዓሊ ስለ አፍረንቀሎ የሙዚቃ ባንድ ወቅት ሲናገር “ እኔ ከመስራቾቹ አንዱ ነኝ እንጂ መስራች አይደለሁም፤በእድሜ ከነሱ አነስ እላለሁ።

አፍረንቀሎን ከመሰረቱት ውስጥ ዓሊ ሸቦ የሚባል እሱም ከሃረማያ ዩኒቨርሰቲ የክብር ዶክትሬት ተሰጥቶታል። እኔ ከነሱ ጋር ተቀላቅዬ አፍረንቀሎን መሰረትኩ” ብሏል።

አርቲስት ዓሊ ቢራ በክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ ተቀጥሮ ለሦስት ዓመታት ሰርቷል፤ እንዲሁም ‘አይቤክስ’ ባንድን በመቀላቀል ለስምንት ዓመታት የሙዚቃ ስራዎቹን በዲ አፍሪካ ሲያቀርብ ቆይቷል። ስለ ፍቅር፣ አካባቢ እና ፖለቲካ በጥቅሉ ከ267 በላይ ሙዚቃዎችን ተጫውቷል። ዓሊ ጊታር፣ ፒያኖ፣ ኡድ እና ሌሎች የሙዚቃ መሳሪያዎችን ይጫወታል። ከአርባ በላይ ሀገራት (በሁሉም አህጉራት) እጅግ በርካታ በሆኑ መድረኮች የሙዚቃ ስራዎችን ተጫውቷል።

ዓሊ ቢራ “Birra Children’s Education Fund” የተባለ ምግባረ ሰናይ ድርጅት ከባለቤቱ ጋር አቋቁመው ለሕፃናት ትምህርት ድጋፍ በመስጠት ላይ ይገኛሉ።

አርቲስት ዓሊ ከኦሮምኛ በተጨማሪ፣ በሶማሊኛ፣ በአፋርኛ፡ በሐረሪ፣ በአማርኛ እና በአረብኛ ቋንቋዎች በርካታ ዘፈኖችን መጫወት ችሏል።አንድ ሰሞን ስለ ራሱ የተናገረው አርቲስት ዓሊ ቢራ "ራሴን የምፈርጀው የሀቅ ታጋይ ነኝ ብዬ ነው" ብሏል።

የ75 ዓመቱ አርቲስት ዓሊ ቢራ ለኢትዮጵያ ህዝቦች አብሮነትና ማህበራዊ ትስስር ከፍ ያለ አስተዋጽኦ አበርክቷል።በሙዚቃዎቹ ዘመን ተሻጋሪ መልዕክቶችን በማስተላለፍ መልካም ትውልድ እንዲቀረጽ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።የተለያዩ ፈተናዎችን ተሻግሮ በከፍተኛ ጽናትና ብቃት ለረጅም ዓመታት በኪነ ጥበቡ ውስጥ ያሳለፈ መሆኑ ደግሞ አሁን ላለው ትውልድ ታላቅ ተምሳሌት ያደርገዋል።

አርቲስቱ በተስረቅራቂ ድምፁ ዘመን ተሸጋሪ ጥዑም ሙዚቃን ከመጫወት በተጨማሪ የግጥምና ዜማ ደራሲም ነው። አርቲስት ዓሊ ቢራ ባለፉት 50 ዓመታት በኦሮሞ የሙዚቃ ስራዎች ውስጥ እንቁ ሆኖ ቆይቷል።

ለቋንቋው የሙዚቃ እድገትም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

በኪነጥበቡ ዘርፍ ላበረከተው አስተዋፅኦ የክብር ዶክተሬት ማዕረግ የተሰጠው አርቲስት ዓሊ ቢራ፣ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገር ተቋማት የተለያዩ እውቅናዎችን እና ሽልማቶችን አግኝቷል።

• በአጠቃላይ ከሃምሳ በላይ ታላላቅ ሽልማቶች ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ተቋማት ወስዷል።
• ከድሬዳዋ እና ከጅማ ዩኒቨርስቲዎች የክብር ዶክትሬት ተበርክቶለታል።
• በድሬደዋ ከተማ ፓርክ እንዲሁም በአዳማ መንገድ በስሙ ተስይሟል።
• የኦሮሚያ ክልል በሙዚቃው ዘርፍ ላበረከተው አስተዋጽኦ ልዩ የኒሻን ሽልማት አበርክቶለታል።
• የመጀመሪያው የኢሬቻ የሰላም ሽልማት ተሸላሚም ነው።
• የመጀመሪያው የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ የኪነጥበብ ሽልማት የህይወት ዘመን ተሸላሚም ሆኗል።
• የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ከፍተኛ ሽልማት
• በካናዳ ቶሮንቶ የአፍሪካን የምንግዜም አንጋፋ ሙዚቀኛ ሽልማት እና
• የኦዳ አዋርድ የሕይወት ዘመን ተሸላሚ ነው።