Get Mystery Box with random crypto!

በኤርትራ የታሰሩ ጋዜጠኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲለቀቁ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት አቤቱታ | ዶይቸ ቬለን | DW AMHARIC NEWS🇪🇹

በኤርትራ የታሰሩ ጋዜጠኞች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲለቀቁ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት አቤቱታ ቀረበ።
የጋዜጠኞች መብት የሚከራከረው ፤ የጋዜጠኞች ጥበቃ ኮሚቴ በእንግሊዥኛው ምህፃሩ CPJ እና ሌሎች ሰባት የመብት ድርጅቶች እና የህግ ባለሙያዎች በጎርጎሪያኑ ሀምሌ 21 ቀን 2022 በጋራ ባወጡት መግለጫ በኤርትራ የታሰሩ ጋዜጠኞችን በተመለከተ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት አቤቱታ አቅርበዋል።
በኤርትራ በእስር ላይ በሚገኘው በጋዜጠኛ ዳዊት ይስሃቅ እና በሌሎች 15 ጋዜጠኞች በተፈፀመው የዘፈቀደ እስር ላይ ተጠያቂነት እንዲሰፍንም አሳስበዋል።
የመብት ተከራካሪ ቡድኖቹ ዳዊት እና ሌሎች ጋዜጠኞች ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ እና ከቤተሰቦቻቸው ወይም ከጠበቆቻቸቸው ጋር ሳይገናኙ መቆየታቸውን ገልፀው፤ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ ጠይቀዋል። .ይህ ጉዳይ በዓለም ዙሪያ ለረጅም ጊዜ ከታሰሩ ጋዜጠኞች መካከል ያደርጋቸዋልም ብለዋል።
የተባበሩት መንግስታት የኤርትራ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ልዩ ዘጋቢ መሀመድ አብደልሰላም ባቢከር በበኩላቸው የዳዊት ጉዳይ ከ2000ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞች ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ፤ በመንግስት ላይ ባደረጉት ትችት ያለ ህጋዊ ሂደት በኤርትራ እስር ቤት ውስጥ ታስረው የሚማቅቁ በመቶዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን ጉዳይ ይጨምራል ብለዋል።
የጋዜጠኞች መብት ኮሚቴ የአፍሪካ ፕሮግራም አስተባባሪ አንጄላ ኩንታል ደግሞ በዳዊትና በባልደረቦቹ ጉዳይ ድርጅታቸው «የትኛውንም የፍትህ መንገድ መከተልን ይቀጥላል» ብለዋል።