Get Mystery Box with random crypto!

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የምርጫ ጠቅላላ ጉባኤ የመጀመሪያ ቀን ውሎ ተገባዷል በኢ ሲ ኤ የመ | Dire Soccer

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የምርጫ ጠቅላላ ጉባኤ የመጀመሪያ ቀን ውሎ ተገባዷል

በኢ ሲ ኤ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የቀጠለው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የምርጫ ጠቅላላ ጉባኤ በባሕል እና ስፖርት ሚንስቴሩ ክቡር አቶ ቀጀላ መርዳሳ የመክፈቻ ንግግር ከተከፈተ በኋላ የጉባኤው አጀንዳዎች ቀርበው ፀድቀው የፌዴሬሽኑ የጽሕፈት ቤት ሀላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን የ2014 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም ላይ የተሰሩ ሥራዎችን አብራርተዋል። በማስከተል የፋይናንስ ሀላፊው አቶ ነብዩ ደመሴ የፋይናንስ ሪፖርት አቅርበዋል። አቶ ነብዩ በገለፃቸው ፌዴሬሽኑ በበጀት ዓመቱ 235,783,534.50 ከተለያዩ የገቢ ምንጮች ገቢ አድርጎ 252,805,711.33 ወጪ መደረጉን ይፋ አድርገዋል። የውጪ ኦዲት ሪፖርትም ቀርቧል።

በጉባኤው የአፋር እግርኳስ ፌዴሬሽን እንደ አጀንዳ ያቀረበውና ተወካዩ አቶ ዓሊሚራ መሐመድ በተወዳዳሪነት ይያዙልኝ ባለው መሠረት ግለሰቡ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል። በተጨማሪም ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አዲሱ የጉባኤው አባል እንዲሆን የቀረበው ጥያቄ በሙሉ ድምፅ ፀድቋል።

በመጨረሻም የወቅቱ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ለጉባኤው አባላት እግርኳሱ እንዲያድግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሥራዎችን እንዲሰሩ አደራ ብለው የመዝጊያ ንግግራቸውን አድርገው የዛሬው ጉባኤ ተገባዷል።

በነገው ዕለት የፕሬዝዳንት እና የሥራ-አስፈፃሚ ኮሚቴ ምርጫ የሚደረግ ይሆናል።

EFF

@diresoccer