Get Mystery Box with random crypto!

እንኩዋን ለታላቁ ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ የሰማዕትነት በዓል በሰላም አደረሳችሁ | ደረጀ እና የድንግል ማርያም ልጆች ግሩፕ ቻናል።

እንኩዋን ለታላቁ ሊቀ ሰማዕታት ቅዱስ ጊዮርጊስ ዓመታዊ የሰማዕትነት በዓል በሰላም አደረሳችሁ

ዐቢይ ወክቡር: ጊዮርጊስ: ሰርዌ አዕላፍ: ወመክብበ ሰማዕታት

=>መጽሐፈ ገድሉ እንደሚለው የሰማዕታት አለቃቸው: አንድም ሞገሳቸው ታላቅና ክቡር ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ7 ዓመታት ስቃይ በሁዋላ በዚህ ቀን ተሰይፏል:: ይሕስ ጥንተ ነገሩ እንደምን ነው ቢሉ:-

+ቅዱሱ የተወለደው ከአባቱ ዘረንቶስ (አንስጣስዮስ) እና ከእናቱ ቴዎብስታ የድሮው ፋርስ ግዛት ፍልስጥኤም (ልዳ) ውስጥ ነው:: የተባረኩ ወላጆቹ ክርስትናን ጠንቅቀው አስተምረውት አባቱ ይሞታል::

+ቅዱስ ጊዮርጊስ 20 ዓመት ሲሞላው የአባቱን ስልጣን እጅ ለማድረግ ሲሔድ የቢሩት (የአሁኗ ቤይሩት-ሊባኖስ) ሰዎች ዘንዶ (ደራጎን) ሲያመልኩ አገኛቸው:: እርሱ ግን የከተማውን ሕዝብ አስተምሮ: አሳምኖ: ደራጎኑንም በፈጣሪው ኃይል ገድሎ መንገዱን ቀጥሏል::

+ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ዱድያኖስና 70 ነገሥታት ዘንድ ሲደርስ ክርስቶስ ተክዶ ለጣዖት ይሠገድ ነበር:: በዚያች ሰዓት ድንግል እመቤታችን ወደ ሰማዕቱ መጥታ መከራውንና ክብሩን ነገረችው:: እርሱም በክርስቶስ ስም መሞት ምርጫው ነበርና ከእመቤታችን ተባርኮ ወደ ምስክርነት አደባባይ (ዐውደ ስምዕ) ደረሰ::

+ከዚያም ለተከታታይ 7 ዓመታት ብዙ ጸዋትወ መከራዎችን ተቀበለ:: 3 ጊዜ ሙቶ ተነሳ:: ከሰው ልጅ የተፈጥሮ ትዕግስት በላይ የሆነ ስቃይን ስለ ቀናች ሃይማኖት ሲል በመቀበሉ የሰማዕታት አለቃቸው: ፀሐይና የንጋት ኮከብ በሚል ይጠራል::
"ተውላጠ ጻማሁ ወሕማሙ:
ዘተለዐለ ሞገሰ ስሙ" እንዲል መጽሐፍ::

=>ቅዱስ ጊዮርጊስን ለዘመናት በብዙ ስቃያት ሲያስጨንቁት ኖረው በጽናቱ አሸነፋቸው:: 70 ነገሥታትን ከነ ሠራዊታቸው ከማሳፈሩ ባሻገርም በርካታ (በመቶ ሺ የሚቆጠሩ) አሕዛብን ማርኮ ለሰማዕትነት አበቃ::

+በዚህ የተበሳጨ ዱድያኖስም ኮከበ ፋርስ ቅዱስ ጊዮርጊስን እንዲቆራርጡት አዘዘ:: ወታደሮቹም ቅዱሱን ቆራርጠው: በብረት ምጣድ ላይ ጠበሱት:: ያለ ርሕራሔም አካሉን አሳረሩት:: ቀጥለውም ፈጭተው አመድ አደረጉት::

+በአካባቢው ወደ ነበረው ትልቅ ተራራ ጫፍ (ደብረ ይድራስ) ወጥተውም በነፋስ በተኑት::
"ሐረድዎ ወገመድዎ: ወዘረዉ ሥጋሁ ከመ ዓመድ" እንዲል:: (ምቅናይ)
+እነርሱ ይህንን ፈጽመው ዘወር ሲሉ ግን የቅዱሱ ዓጽም ባረፈባቸው ዛፎች: ቅጠሎችና ድንጋዮች ሁሉ "ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት" የሚል ጽሑፍ ተገኘ::

+ወዲያው ግን ኃያል ሰማዕት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከተበተነበት ተነስቶ ወታደሮችን አገኛቸውና "በክርስቶስ እመኑ" ብሎ: አስደንቆ ወደ ሕይወት መራቸው:: 70ው ነገሥታት ግን አፈሩ::
+ከ7 ዓመታት መከራ በሁዋላም በዚሕች ቀን ከብዙ ተዓምራት ጋር ተሰይፎ ደም: ውሃና ወተት ከአንገቱ ፈሷል:: 7 አክሊላትም ወርደውለታል::

=>በ390ዎቹ አካባቢ (ሰማዕት ከሆነ ከጥቂት ዓመታት በሁዋላ) በዚያው በሃገሩ ደብር አንጸው: አጽሙን አፍልሠው ቀድሰዋታል::
+ቅዱሱ ሰማዕት ከሰማዕትነቱ በፊትም ሆነ በሁዋላ ተአምረኛ ነው:: በዘመኑ የክርስቲያኖችን ደም ሲያፈሱ ከነበሩ አራዊት (ነገሥታት) መካከል አንዱ የሆነው ዲዮቅልጢያኖስ ርጉም የ47 ሚሊየን ክርስቲያኖችን ደም አፍስሶ ነበርና ፈጣሪ ደመ ሰማዕታትን የሚበቀልበት ጊዜ ደረሰ::

+በ305 ዓ/ም አካባቢ አረመኔው ንጉሥ ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ተአምረኛነት ሰምቶ እንዲያፈርሱት ሠራዊት ላከ:: የሠራዊቱ አለቃም ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ገብቶ በቅዱስ ጊዮርጊስ ስዕል ላይ ተሳለቀ::

+ከፊቱ የነበረውን ቀንዲል በሰይፍ እመታለሁ ሲል ግን ቀንዲሉ ተገልብጦ መሐል አናቱን መታው:: እንደ እብድ ሆኖ ሞተ:: ሠራዊቱም ሰምቶ ወደ ንጉሡ ሸሸ:: ይሕን ሰምቶ የተበሳጨው ዲዮቅልጢያኖስ ግን ራሱ ሊያፈርሰው ሔደ:: ከቤተ ክርስቲያኑ በር ላይ ሲደርስ ሚካኤልና ገብርኤል ዐይኑን አጠፉት::

+እገባለሁ ሲል ቅዱስ ጊዮርጊስ ከላይ መረዋውን (ደወሉን) ለቀቀበት:: ራሱን ቢመታው ደነዘዘ:: የብዙ ቅዱሳንን ደም የጠጣው ርጉሙ ንጉሥም አብዶ ለ7 ዓመታት ፍርፋሪ ሲለምን ኑሮሰ ይጣን ከገደል ጫፍ ወርውሮ ገድሎታል::

=>አምላካችን እግዚአብሔር ከኃያሉ ሰማዕት ጽናትና ትእግስት: ከበረከቱም ይክፈለን::

=>ሚያዝያ 23 ቀን የሚከበሩ ዓመታዊ የቅዱሳን በዓላት=
1.ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊቀ ሰማዕታት
2.ቅዱስ ሮቆ ጻድቅ (በስሙ ለተማጸነ ከወባ በሽታ እንዲጠብቀው ጌታ ቃል ኪዳን ገብቶለታል)

=>ወርኀዊ በዓላት
1.ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት
2.ቅዱስ ሰሎሞን ንጉሠ እስራኤል
3.አባ ጢሞቴዎስ ገዳማዊ
4.አባ ሳሙኤል
5.አባ ስምዖን
6.አባ ገብርኤል

=>+"+ የሚበልጠውን ትንሳኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ:: ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ:: በድንጋይ ተወግረው ሞቱ:: ተፈተኑ: በመጋዝ ተሰነጠቁ: በሰይፍ ተገድለው ሞቱ:: ሁሉን እያጡ: መከራን እየተቀበሉ: እየተጨነቁ: የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ:: ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ: በዋሻና በምድር ጉድጉዋድ ተቅበዘበዙ:: +"+ (ዕብ. 11:35-38)

✞✞✞ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ✞✞✞
     ✞✞✞ወወላዲቱ ድንግል ✞✞✞
     ✞✞✞ ወለመስቀሉ ክቡር ✞✞✞