Get Mystery Box with random crypto!

'የዞናችን ትምህርት ስብራቶችና የመዉጫ መንገዶች' በሚል መሪ ሀሳብ የምክክር መድረክ ተደረገ == | Debre Markos University /ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ

"የዞናችን ትምህርት ስብራቶችና የመዉጫ መንገዶች" በሚል መሪ ሀሳብ የምክክር መድረክ ተደረገ
==============
ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፣ ጥቅምት 19/2015 ዓ.ም (ህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ) የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ እና የምስ/ጎጃም ዞን ትምህርት መመሪያ በጋራ በመተባበር የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ትምህርት ቢሮ ም/ቢሮ ኃላፊዎች ፣ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ፣ ምክትል ፕሬዚደንቶችና ልዩ ልዩ የስራ ኃላፊዎች ፣ የምስ/ጎ ዞን የብልፅግና ጽ/ቤት ኃላፊ ፣ የምስ/ጎ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ፣ የወረዳ አስተዳዳሪዎች፣ የወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊዎች ፣ ሱፐር ቨይዘሮች ፣ ርዕሳነ መምህራን ፣ በየደረጃው የሚገኙ የመምህራን ማህበር ስራ አስፈፃሚዎች እና የትምህርት ባለሙያዎችን ያካተተ ውይይት ጥቅምት 18 ቀን 2015 ዓ.ም በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ቀኝ ጌታ ዮፍታሄ ንጉሴ አዳራሽ ውስጥ ተካሂዷል።

የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የምስ/ጎጃም ዞን ትም/መመሪያ ሀላፊ አቶ ጌታሁን ፈንቴ በመልዕክታቸው እንደገለፁት የምስ/ጎጃም ዞን የዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች በተለይ የተወሰኑ የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ያሳዩት ህገ_ወጥ ስነ_ምግባር ዞኑን ጥላሸት የቀባና ትዝብት ላይ የጣለ ተግባር ነው። ለአብነት ደጀን፡ እናርጅ እናዉጋ እና የሸበል በረታ የተወሰኑ ተፈታኝ ተማሪዎች ፈተናውን ጥለው ሂደዋል። በተጨማሪም አንዳንድ ተፈታኞኝ ጎበዝ ተማሪዎችን በማስፈራራት ለመኮረጅ በመሞክሩም በዪኒቨርስቲው አመራሮች እና በፈታኞች ጥረት እደከሸፈ ገልጸዋል። ሀሳባቸዉን ሲያጠቃልሉም በዞኑ በፈተናው ውቅት ችግሮች ቢፈጠሩም የተፈጠሩ ችግሮችን ቶሎ መፍትሄ በመስጠት ፈተናው ተጠናቅቋል ብለዋል።

የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የምስ/ጎጃም ዞን የብልጽግና ፖርቲ ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ ዋለ አባተ ደግሞ የ2014 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና የተፈጠሩት ችግሮች የትምህርት ስርዓታችን ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ቁልጭ አድርጎ ያሳዬ ነዉ ያሉ ሲሆን የተፈጠረዉን ስብራት በዘለቄታዊነት ለመፍታት በየደረጃው ያሉት ባለድርሻ አካላት የተሰጣቸውን ሃላፊነት በአግባቡ ሊውጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የደ/ማርቆስ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚደንት ታፈረ መላኩ (ዶ/ር) በበኩላቸው የደ/ማርቆስ ዩኒቨርስቲ አመራሮች እና የግቢው ማህበረሰብ ተፈታኝ ተማሪዎችን ለመቀበል ያደረግነው ቅድመ ዝግጅት ጠንካራ አንደነበር ገልጸዉ የተወሰኑ ተፈታኞች ያሳዩት ስነምግባር የጎደለው ድርጊት ግን እንዳሳዘናቸውና ገልፀዋል። እነዚህ ስነ ምግባር የጎደላቸው ተማሪዎች እረብሻና ግርግር በመፍጠር ፈተናውን ለማስተጎጓል ቢሞክሩም የዪኒቨርስቲው አመራር ችግሩን በመቆጣጠር ሌሎች ተፈታኞች ተረጋግተዉ እንዲፈተኑ ከፍተኛ እርብርብ በማድረግ ፈተናዉ እንዲጠናቀቅ ሆኗል ብለዋል።

የአማራ ክልል ትም/ቢሮ ም/ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙላዉ አበበ በዚህ ወሳኝ ስዓት እንደዚህ ያለ ውይይት እንዲዘጋጅ የተባበሩትን የምስራቅ ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያንና የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲን አመስግነው በክልሉ ፈተናው ከተሰጠባቸው ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ መቅደላ አምባ ፣ በደ/ማ እና በደብረ ታቦር ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የተፈጠረው ነገር የሚያስቆጭና ወደራሳችን ብቻ እንድንመለከት የሚያደርግ ነገር መሆኑን ጠቁመዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ "Paradymshift in Education" በሚል ርዕሰ ቁልፍ መልዕክት ያስተላለፉት በመቅደላ አምባ ዩኒቨርስቲ በም/ፕሬዝዳንት ማዕረግ የመካነ ሰላም ካምፓስ ዋና ዳይሬክተር ሽበሺ አለባቸው (ዶ/ር ) ሲሆኑ በመልከዕክታቸውም የተሰበረው አሁናዊ የተማሪዎቻችን ሁኔታ የሚያሳየው በህፃናት ላይ ስራዎችን ባለመስራታችን የመጣ ችግር መሆኑን ገልፀው ይሄ ችግር እንዲቀለበስ ካስፈለገ ህፃናት ላይ ትኩረት ሰጥተን መስራት እንደሚገባን በአንክሮት አብራርተዋል።

"የምስ/ጎጃም ዞን ትምህርት ስብራቶች እና የመዉጫ መንገዶች" በሚል የምስ/ጎጃም ዞን ትምህርት መምሪያ ሃላፊ አቶ ጌታሁን ፈንቴ ሰፊ ይዘት ያለው ፅሑፍ ያቀረቡ ሲሆን በትምህርት ጥራት ላይ ያንዥበቡና ጥላ ያጠሉ ሳንካዎችን በዝርዝር ለታዳሚውቹ አቅርበዋል።

በሌላ በኩል የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና አፈጻጸም ግብረ መልስና ትዝብት በሚል የደ/ማ ዩኒቨርስቲ አካደሚክ ጉዳዮች ኤክዚኪዩቲቭ ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር በለጠ ያዕቆብ ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን ለማስፈፀም ከመነሻ እስከ ፍፃሜ ያደረገውን እንቅስቃሴና በመፈተናው ሂደትም ወቅት የገጠሙ ችግሮችን በዝርዝር አቅርበዋል።

በባ/ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር ፣ ተመራማሪና ደራሲ እንዲሁም በአሁኑ ስዓት በክልላችን እየገጠሙን ያሉ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅፋቶችን ለመቀልበስ በሚያስችል መልኩ ማህበረሰብን እያነቁ የሚገኙት የሻምበል አጉማሴ (ዶ/ር) "ታላቅ ህዝብን ወደ ቀደመ ክብሩ መመለሻ የትምህርት አብርሆት" በሚል ርዕስ ፅሑፍ አቅርበዋል። ባቀረቡት ፅሑፍም በክልላችን ብሎም በሀገራችን እየተስተዋሉ ያሉ መዛነፎች ፣ መንስኤዎችና መፍትሄዎችን በተጨባጭ ምሳሌዎችና ማብራሪያዎች አስደግፈው ታዳሚዎችን በሚያዝናና እና ቁምነገር በሚያስጨብጥ መልኩ አቅርበዋል።

በቀረቡት የመወያያ ፅሑፎች ላይም ሰፊ ውይይቶችና አስተያየቶች ከታዳሚዎቹ የተሰጡ ሲሆን በትምህርት ጥራት ላይ የገጠመን ፈተና ከባድ መሆኑን እና ይህንን ችግርም ለመፍታት መገፋፋትን በመተው በጋራ መስራት እንደሚገባም በሁሉም የውይይቱ ታዳሚዎች ዘንድ መግባባት ላይ ተደርሷል።

በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የተሻለ አፈጻጸም ያስመዘገቡ ወረዳዎች፣ከተማ አስተዳደሮችና ትምህርት ጽ/ቤቶች እውቅና በመስጠት እና ዶክተር ሻምበል አጉማሴን ደግሞ ልዩ ተሸላሚ በማድረግ የውይይቱ ፍፃሜ ሆኗል።