Get Mystery Box with random crypto!

ማብራሪያ ከሚሹ በተለይ በአንዳንድ ሰልጣኞች ተደጋግመው ከሚነሱ ግርታ ካጠላባቸው ሀሳቦች በከፊል | Development Bank of Ethiopia (DBE) : Training to Lease Financing

ማብራሪያ ከሚሹ በተለይ በአንዳንድ ሰልጣኞች ተደጋግመው ከሚነሱ ግርታ ካጠላባቸው ሀሳቦች በከፊል

ማውጫ
ሀ፡
ከ500 ሺ እስከ 15 ሚ ካፒታል ብቻውን አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሽ ያደርጋል?
ለ፡ የአገልግሎት ክፍያ መሰላት የሚጀምረው ከመቼ ጀምሮ ነው?
ሐ ፡ የካፒታል ዕቃ ዋጋ በመጀመሪያው ውል ተገብቶ ከነበረው ስምምነት በልጦ ከመጣ ጠቅላላ የብድሩ መጠን እንዴት ይያዛል?
መ: ከላይኛው ጥያቄ ጋር በተያያዘ የስራ ማስኬጃ 20% መዋጮ ከለውጡ ጋር አብሮ ይሻሻላል?
ሠ:ወለድ አልባ የሊዝ ፋይናንሲንግ ማለት ከካፒታል ዕቃው ዋጋ ሌላ ምንም ክፍያ የለውም ማለት ነው?
ረ፡ የማምረቻ ማሽኖችን ከውጪ ሀገር ብቻ ነው መግዛት የሚቻለው?
ሰ፡ ለሚገዛው የካፒታል ዕቃ ኢንሹራንስ የሚገዛው ባንኩ ነው ወይስ ደንበኛው?
ሸ፡ የካፒታል ዕቃውን ሰርቪስ የማስደረግ/የማስጠገን ሀላፊነት የባንኩ ነው ወይስ የደንበኛው?
ቀ፡ ካሁን ቀደም በባንኩ ፋይናንስ ለተደረጉ ድርጅቶች ተጨማሪ ማስፋፊያ ይሰጣል?

ሀ፡ ከ500 ሺ እስከ 15 ሚ ካፒታል ብቻውን አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሽ ያደርጋል?

በተለይ በስራ ላይ ያሉ ድርጅቶች ጥያቄ ከ500 ሺ ያላነሰ ከ15 ሚ ያልበለጠ ካፒታል መኖሩ ብቻውን በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ ማእቀፍ ለሊዝ ፋይናንሲንግ ብቁ እንደሚያደርግ ይሰማቸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ግን በዚህ ማእቀፍ ውስጥ የሚስተናገዱ ድርጅቶች ሊዝ ፋይናንሲንግ የሚጠይቁበት ድርጅት ሊኖረው የሚገባው አጠቃላይ የሀብት ጣሪያ ገደብ አለው፣ ይህም 75 ሚሊዮን ብር ነው፣ ድርጅቱ ያለውን የስራ ማስኬጃ ጨምሮ (የዚህ 20 % 15 ሚሊዮን ብር/አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የካፒታል ጣሪያ፣ 80 % ደግሞ 60 ሚሊዮን ብር/ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በሊዝ ፋይናንሲንግ አገልግሎት የሚያገኙት የብድር ጣሪያ መስጠታቸውን ልብ ይሏል)። ድርጅቱ የሚያስተዳድረው የሀብት መጠን ከዚህ በላይ ነው ማለት 20 በመቶ እና 80 በመቶ ጣሪያዎች ይጣሳሉ እንደማለት ስለሆነ ድርጅቱ የሚስተናገድበት የፋይናንሲንግ አይነት በሊዝ ፋይናንሲንግ ሳይሆን በፕሮጀክት ፋይናንሲንግ ይሆናል ማለት ነው።

ለ: የአገልግሎት ክፍያ መሰላት የሚጀምረው ከመቼ ጀምሮ ነው?
የአገልግሎት ክፍያ መታሰብ የሚጀምረው ደንበኛው የካፒታል ዕቃውን መረከቡን የሚያረጋግጠውን የርክክብ ሰነድ ከባንኩ ጋር ከተፈራረመበት ቀን ጀምሮ ነው፡፡

ሐ፡ የካፒታል ዕቃ ዋጋ በደንበኛውና በባንኩ ስምምነት ከተደረገና ውል ከተገባ በኋላ በስምምነቱ መሰረት ከውጪ ሀገር የሚገዛው የካፒታል ዕቃ ግዢ ሲፈፀም በገንዘብ ምንዛሬ ለውጥ ምክንያት እንዲሁም ዕቃውን የደንበኛው የማምረቻ ቦታ ለማድረስ የሚከፈለው የማጓጓዣ፣ የተከላ ሥራ እና ተያያዥ ወጭዎች በመጀመሪያው ውል ተገብቶ ከነበረው ስምምነት በልጦ ከመጣ ጠቅላላ የብድሩ መጠን እንዴት ይያዛል?

ይህ አይነት ሁኔታ በሊዝ ፋይናንሲንግ አገልግሎት የሚከሰት ነው፣ ደንበኛውና ባንኩ ስምምነት በሚያደርጉበት ጊዜና ዕቃው ተገዝቶ እስኪመጣ ባለው ጊዜ ውስጥ የምንዛሬ ለውጥ የሚኖርበትና ተያያዥ ወጪዎችም የሚንሩበት እድል ሰፊ በመሆኑ። ስለዚህ የመጀመሪያ ውል ላይ የተጠቀሰው ገንዘብ ከግዢ በኋላ በተረጋገጠውና ልቆ በመጣው ወጪ/ገንዘብ ተተክቶ የብድሩ ውል ተሻሽሎ የሚዘጋጅና የሚፈረም ይሆናል፡፡

መ: ከላይኛው ጥያቄ ጋር በተያያዘ የሚነሳው ሌላ ጥያቄ የስራ ማስኬጃ 20% መዋጮ ከዋጋው ለውጥ በኃላ የደንበኛው መዋጮም አብሮ ይሻሻላል ወይስ መጀመሪያ በባንኩ በሚከፈተው ዝግ አካውንት ውስጥ ተቀማጭ በተደረገው መዋጮ ሂደቱ ይቀጥላል? የሚል ነው፡፡

መረዳት የሚኖርብን ጉዳይ 20፡80 የሚለውን የፋይናንሲንግ ስርአት ነው፡፡ የመዋጮው እሳቤ ባንኩ ለደንበኛው ህልሙን እውን ከሚያደርግለት ፕሮጀክት አጠቃላይ ወጪ ላይ 20% መዋጮ ከደንበኛው ያስፈልጋል ነው፡፡ ስለዚህ ደንበኛው በትክክል የፕሮጀክት ባለቤት የሆነበት የገንዘብ መጠን መጀመሪያ የተዋዋለው ሳይሆን በተግባር ከግዢ በኋላ ያለው ወጪ ነው፡፡ ስለሆነም የደንበኛው መዋጮ በሚሻሻለው አዲሱ ጠቅላላ ወጪ ልክ የሚሻሻልና በመጀመሪያውና በአዲሱ መዋጮ የሚኖረው ልዩነት ቀድሞ በማይንቀሳቀስ አካውንት ውስጥ ገቢ የተደረገው ብር ላይ ተጨምሮ ገቢ መደረግ አለበት።

እንደምሳሌ፣ በመጀመሪያ በተገባው ስምምነት መሰረት መዋጮው በዕቅድ ከተያዘው 10 ሚሊዮን ላይ የመዋጮው መጠን 2 ሚሊዮን የነበረ ቢሆን እና ከግዢ በኃላ የፕሮጀክቱ የተረጋገጠ ጠቅላላ ወጪ 11 ሚሊዮን ቢሆን የደንበኛው መዋጮ በሚሻሻለው ስምምነት መሠረት 2.2 ሚሊዮን ይሆናል ማለት ነው። ስለዚህ የብድሩ መጠን ከ10 ወደ 11 ሚ ሲያድግ የመዋጮው መጠንም በዚሁ አግባብ ከ2 ሚ ወደ 2.2 ሚ እንዲያድግ እና የደንበኛው መዋጮ ልዩነቱ ብር 200,000 ቀድሞ በተከፈተው ዝግ አካውንት ደንበኛው ገቢ የሚያደርግ ይሆናል ማለት ነው።

ሰ: ወለድ አልባ የሊዝ ፋይናንሲንግ ማለት ከካፒታል ዕቃው ዋጋ ሌላ ምንም አይነት ወለድም ሆነ ሌላ ክፍያ የለውም ማለት ነው?

በተለይ በአንዳንድ ሰልጣኖች በግልፅ ሲቀርብ የሚሰማው ጥያቄ ይህንን የሚጠቁም ነው፡፡ ወለድ አልባ የሊዝ ፋይናንሲንግ ማለት የሸሪዓ ህግን ተከትሎ አገልግሎት የሚሰጥበት የኪራይ አገልግሎት ማለት ነው፡፡ ይህ የፋይናንስ ስርአት ከብዙ መገለጫዎቹ በዋናነት ወለድን መክፈልም ሆነ መቀበል የሌለበት እና ትርፍና ኪሳራን መጋራትን መሠረት ያደረገ የፋይናንሲንግ አይነት ነው፡፡ ስለዚህ ምንም እንኳን ወለድ የሚታሰብበት የብድር አይነት ባይሆንም ምንም ክፍያ የለውም ማለትም አይደለም ከተከራዩ ጋር በሚደረግ ስምምነት ጥቅምን መጋራት በሚል መርህ ስለሚመራ፡፡

የዚህ ወለድ አልባ ፋይናንሲንግ አሰራር ባንኩ የካፒታሉን ዕቃ ገዝቶ ለተበዳሪው አስረክቦ የገዛበትን ገንዘብ ብቻ መልሶ የሚሰበስብበት አይደለም፡፡ ባንኩ የሸሪዓው ህግ በሚፈቅደው አግባብ በኢጃራ ሊዝ ፋይናንሲንግ መርህ መሠረት ለደንበኞቹ አገልግሎት የሚሰጥበት የፋይናንሲንግ አይነት ነው፡፡ በአብዛኛው ሀገራትና ባንኮች በስራ ላይ ከሚያውሉት ሁለቱ የኢጃራ አፈፃፀሞች ውስጥ ደንበኛው በኪራይ የሚጠቀምበትን የካፒታል ዕቃ ዋጋና የኪራይ ዋጋ በባንኩና በደንበኛው መካከል በሚደረግ ስምምነት መሠረት ለክፍያ በተሰጠው ጊዜ ውስጥ የተተመነውን የክፍያ ድርሻ እየከፈለ ዕቃዎቹን በኪራይ መልክ የሚጠቀምበት እና ባንኩም የኪራይ ውሉ ሲያበቃ ባለቤትነቱን የሚያስተላልፍበት አሰራር ነው የሚሆነው።