Get Mystery Box with random crypto!

አክስዮናዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው 1• በአክስዮን የሚመሰረተው ድርጅት አጠቃላይ መዋቅራዊ ገፅታ ምን | Development Bank of Ethiopia (DBE) : Training to Lease Financing

አክስዮናዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
1• በአክስዮን የሚመሰረተው ድርጅት አጠቃላይ መዋቅራዊ ገፅታ ምን ይመስላል?
2• በአክስዮን ለመስራት የሚደራጅ አጋር ከየት ይገኛል/እንዴት እንሰባሰብ?
3• ለመደራጀት ምን ያስፈልጋል?
4• ስንት ሼር መግዛት አዋጪ ነው?

በአክስዮን የሚመሰረተው ድርጅት አጠቃላይ መዋቅራዊ ገፅታ ምን ይመስላል?

በአክስዮን የሚመሰረት ድርጅት ከአሁን ቀደም ከልማት ባንክ ፕሬዚደንት ጋር በተረገው ቃለ ምልልስ እንደተብራራው በቦርድ እና በማኔጅመንት መዋቅር ተከፍሎ ይደራጃል፡፡ የቦርዱ አካል የፖሊሲ ሁኔታዎችን የሚይዝ ሲሆን ማኔጅመንቱ ደግሞ ኦፕሬሽን አካልን የሚይዝ ነው፡፡

የቦርድ መዋቅር፡ ከፍተኛ ሼር ያላቸው በቦርድ እንዲሳተፉ ሲደረግ ትንንሽ ሼር የያዙ ደግሞ እነሱን በሚወክሉ በቦርድ ውስጥ ቦታ ተሰጥቷቸው ይሰራሉ፡፡

የማኔጅመንት መዋቅር፡ ፕሮፌሽናል የሆኑ እንደፕሮፌሽናቸው ድርጅቱ የሚፈልገውን የሰው ሀይል ለሟሟላት በተለያዩ የስራ ክፍሎች ውስጥ (እንደ ፋይናንስ፣ ማርኬቲንግ እና ቴክኒክ የመሳሰሉት) ተቀጥረው ሊሰሩም ይችላሉ፡፡ ይህ ሁለት ዕድልን ይፈጥራላቸዋል አንደኛው እንደፕሮፌሽናቸው ተወዳድረው ተቀጥረው ሰራተኛ ሆነው ደምወዝ እንዲያገኙ ሲያስቻላቸው ሌላኛው ደግሞ ባላቸው ሼር አማካኝነት ባለአክስዮን /ሼርሆለደር/ ያደርጋቸዋል፡፡

በአክስዮን ለመስራት የሚደራጅ አጋር ከየት ይገኛል/እንዴት እንሰባሰብ?

 በአክስዮን ለመደራጀት የሚፈልጉ አካላት በራሳቸው ተሰባስበው/ግሩፕ ሆነው/ መጥተው ሊመሰርቱ ስለወጠኑት አክስዮን ድርጅት ምዝገባ ማከናወን ይችላሉ፡፡
 መሰባሰብ ያልቻሉና /ግሩፕ መፍጠር ያልቻሉ/ በግለሰብ ደረጃ መጥተው በባንኩ አማካኝነት ለመደራጀት ፍላጎት ያላቸው ሰዎች የአክስዮን መስራች አጋርን ለማግኘት ቀላል መንገድ ተፈጥሮላቸዋል፡፡ ይህም በአክስዮን ለመደራጀት የፈለገና የወሰነ ሰው በአካል በልማት ባንክ ቅርንጫፍ ቢሮዎች ቀርቦ ሲመዘገብ ከሚሞላቸው ነጥቦች ሁለቱ ሊሰማራ ያቀደውን ዘርፍ እና የሚገዛውን የአክስዮን ብዛት ያካትታል። አንደኛው ተመዝጋቢ ለመደራጀት በመረጠው ዘርፍ ሌሎችም የሚመርጡ እጩ አክስዮን መስራቾች ይኖራሉ። ስለዚህ በተመሳሳይ ዘርፍ መሰማራት የሚሹ አካላት ሊሰባሰቡ የሚችሉበት አንዱ አማራጭ ይህ ስለሆነ መደራጀት ከሚፈልግ ሰው የሚጠበቀው ለመሰማራት ያቀደበትን የኢንቨስትመንት ዘርፍ አስቀድሞ መርጦ በባንኩ ቅርንጫፍ በመሄድ ለዚሁ ጉዳይ በተዘጋጀው ፎርም ምዝገባ ማከናወን ነው።

ለመደራጀት ምን ያስፈልጋል?

 በአክስዮን የመደራጀት ውሳኔ ‘እስኪ ልሞክረው’ በሚል መንፈስ የተቃኘ መሆን አይኖርበትም፡፡ ይልቁንም በባለቤትነት ስሜትና አመለካከት ከሌሎች ባለራዕዮች ጋር በጋራ ድርጅታዊ ሁለንተና ፈጥሮ የገንዘብ አቅም ያለው ድርጅት ለማቋቋም እና ከልማት ባንክ ለሚቀርበው ሊዝ ፋይናንሲንግ የሚጠበቀውን መዋጮ አቅርበው የአገልግሎቱ ተጠቃሚ በመሆን በጋራ ለመስራትና ለማደግ ፅኑ ፍላጎትና አቋም ያስፈልጋል።
 በመቀጠል የሚሰማሩበትን ዘርፍ እና መግዛት የሚችሉትን ሼር መጠን መወሰንና በዚሁ አግባብ ሼር ለመግዛት የሚያስፈልገውን ገንዘብ ዝግጁ ማድረግ ነው፡፡ ዝቅተኛው የአክስዮን ድርሻ መጠን 5 ሲሆን የእያንዳንዱ ዋጋ 1000 ብር ነው:: ስለዚህ በጠቅላላው ቢያንስ ለትንሹ የሼር መጠን 5,000 ብር ማዘጋጀት እንደሚያስፈልግዎ ልብ ይሏል፡፡

ስንት ሼር መግዛት አዋጪ ነው? (እይታ፡ አጠቃላይ የአክስዮን ህግ)

(ይህ ፅሁፍ እዚህ መስፈሩ ለጠቅላላ ዕውቀት ታልሞ እንጂ የልማት ባንክን አሰራር በቀጥታ ስለሚውክል አይደለም)

ስንት ሼር መግዛት ጥሩ/አዋጪ እንደሚሆን በቁጥር ማስቀመጥ ምክንያታዊ ስላይደለ ጥያቄውን በምሳሌ መመልከቱ የተሻለ ገላጭ ይሆናል፡፡ በመጀመሪያ የሚመሰረተው ድርጅት ምን ያህል መነሻ ካፒታል እንዲኖረው ያስፈልጋል የሚለው ተቋማዊ ውሳኔ የሚፈልግና ዋናው ገንዘቡ/ካፒታሉ/ አስቀድሞ ተወስኖ በአክሲዮን የተከፋፈለ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ለቀለለ ገለፃ ሲባል ብቻ ይህንን የመነሻ ካፒታል መጠን በባንኩ የሊዝ ፋይናንሲንግ ፖሊሲ መሠረት በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች መደብ ውስጥ ለመካተት ሊዝ ፋይናንሲንግ ጠያቂው ድርጅት ሊኖረው የሚገባው የተመዘገበ ካፒታል ከ500,000 እስከ 15 ሚሊዮን መሆን አለበት ከሚለው መስፈርት ውስጥ ዝቅተኛውን 500ሺ እንደሆነ እናስብ፡፡

እንዲሁም አንድ በአክስዮን የሚደራጅ ድርጅት የሊዝ ፋይናንሲንግ ጥያቄ የሚያቀርብበት የፕሮጀክት አይነት አጠቃላይ ወጪ (የማሽኑን፣ ተያያዥ ወጪዎችን፣ እና ስራ ማስኬጃውን ጨምሮ) ብር 10 ሚሊዮን ቢሆን፣ የዚህን 10 ሚሊዮን ብር ሀያ በመቶ (20%)  የሚሆነውን ብር 2 ሚሊዮን የስራ ማስኬጃ መዋጮ መጠን እንደሆነ እንያዝ፡፡ ስለዚህ ድርጅቱ የሚያስፈልገው የመነሻ ካፒታል እና ከልማት ባንክ ለሚጠይቀው ሊዝ ፋይናንሲንግ የስራ ማስኬጃ መዋጮ በድምሩ 2.5 ሚሊዮን ብር በሚመሰረተው አክስዮን ድርጅት መሰብሰብ ያስፈልጋል ማለት ነው (በምን አግባብ የተከፈለ የድርጅቱ የመነሻ ካፒታል ይመዘገባል እንዴትስ ሀያ በመቶ መዋጮ ለታለመለት አላማ እንዲውል ይደረጋል የሚለው ህጉ በሚፈቅደው አግባብ እንደሚስተናገድ ታሳቢ ተደርጎ)፡፡ በዚህ መነሻ የሚከተሉትን ምሳሌዎች እንመልከት፡-

ም1፡- ይህ ድርጅት ዝቅተኛና ከፍተኛ አክሲዮን ገዢ ሊኖረው እንደሚችል ይታመናል፡፡ ለምሳሌያችን መጀመሪያ እንዲሆን ግን ዝቅተኛ የአክሲዮን ድርሻ ገዢ ብቻ እንዳለ እናስብ፡፡ ስለዚህ በዝቅተኛው 5 የአክስዮን ድርሻ መጠን እያንዳንዱ አክስዮን 1ሺ ብር ሲሰላ በአጠቃላይ 5,000 ብር በአንድ ባለአክስዮን ተዋጣ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የሚፈለገውን ገንዘብ ለማመንጨት በጠቅላላው 500 ባለ አክስዮኖች በጋራ መደራጀት ይኖርባቸዋል እንደማለት ነው (500 ሰው መደራጀት ይችላል ለማለት ግን አይደለም ስንት ሰው መደራጀት ይችላል የሚለው ገና በባንኩ የሚወሰን ስለሆነ)፡፡

ም2፡- በሌላኛው መንገድ ስሌቱን ብንከውነውና ከፍተኛው የተገዛ የሼር መጠን 100ፍሬ እንደሆነ ይህም ማለት በአንድ ባለአክስዮን የ100ሺ ብር አክስዮን እንደተገዛ ብናስብ ድርጅቱን ለመመስረት በጠቅላላው 25 ባለአክስዮኖች መደራጀት ይኖርባቸዋል እንደማለት ነው፡፡

ም3፡- ምሳሌያችንን ተደራሽ ለማድረግ ከላይ የተቀመጠውን ከፍተኛ የአክስዮን ድርሻ መጠን/ገንዘብ አማካኝ 50 የአክስዮን ድርሻ ወይም 50,000 ብር ብለን ብናሰላው የሚፈለገውን መነሻ ካፒታልና ሀያ በመቶ መዋጮ መጠን ድምር ለማመንጨት 50 ባለአክስዮኖች መደራጀት ይኖርባቸዋል እንደማለት ነው፡፡

ስለዚህ ስንት አክስዮን አንድ ባለአክስዮን ቢገዛ ጥሩ/አዋጪ ነው የሚለው ጥያቄ ከሌላ እይታ ምላሾችን ማግኘት የሚችል ሆኖ ከጥያቄያችን እና ከምሳሌያችን አንፃር ስንመለከተው ግን በአክስዮን ለመደራጀት ከብዙ ምክንያች መሀል በነዚህ በሶስቱ ሃሳቦች ዙሪያም ያጠነጥናል:-

1. በአክስዮን ለመደራጀት የወሰኑ ባለአክስዮን እጩዎች በምን ያህል መቶኛ የድርጅቱን ባለቤትነት መያዝ ይፈልጋሉ (ምክንያቱም በአክስዮን ድርሻቸው ልክ በድርጅቱ ላይ ባለቤትነት ሊኖራቸው መቻሉ)
2.  የተጣራ ዓመታዊ ትርፍ የሚከፋፈለው ባለአክሲዮኖቹ ባሉአቸው አክሲዮኖች መጠን ልክ ሊሆን መቻሉ  (የተጣራ ትርፍ በምን ሁኔታ ይከፋፈል የሚለው ውሳኔ በማኅበሩ ባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ የሚተላለፍ ሆኖ)
3. ባለአክስዮኖች አክስዮን ለመግዛት ባላቸው የገንዘብ አቅም ላይ የተወሰነ መሆኑ፡፡