2022-07-14 14:34:14
የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የካፍ መመዘኛ መስፈርትን ባሟላ መልኩ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ መሪዎች ትኩረት እንዲሰጡት አቶ ኢሳያስ ጅራ ጠየቁ።
የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የአመራር ቁርጠኝነት ከታከለበት የካፍ መመዘኛ መስፈርትን ባሟላ መልኩ በፍጥነት መጠናቀቅ የሚችል መኾኑን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጅራ ገለጹ፡፡
ባለፉት 15 ዓመታት የሀገሪቱን እግር ኳስ ወደ አንድ ደረጃ ከፍ ሊያደርጉ የሚችሉ ግዙፍ ስታዲየሞች ግንባታ በተለያዩ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ቢጀመሩም አንዳቸውም መጠናቀቅ አልቻሉም።
ለዓመታት ዓለም አቀፍ ውድድሮችን ሲያስተናግድ የነበረው አንድ ለእናቱ የሚባለው የአዲስ አበባ ስታዲየም ከሶስት ዓመት በፊት በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን እገዳ እንደተጣለበት ይታወሳል፡፡
የስታዲየሙን መታገድ ተከትሎ ባሕር ዳር ስታዲየም በጊዜያዊነት ዓለም አቀፍ ጨዋታ ሲያስተናግድ ቢቆይም የካፍ መመዘኛ መስፈርትን ሙሉ በሙሉ ባለሟሟላቱ ከጥቅምት 2014 ዓም አንስቶ ተመሳሳይ እገዳ ተጥሎበታል።
ይህን ተከትሎም የኢትዮጵያ ብሄራዊ እግር ኳስ ቡድንበ ጨዋታዎችን በመረጠው ሀገር እያደረገ ነው።
የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ እንዳሉት በሀገሪቱ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም አለመኖር የተጨዋቾችንና ደጋፊዎችን ስሜት አለፍ ሲልም የኢኮኖሚ አቅምን የሚጎዳ ነው።
በዚህም ብሄራዊ ቡድኑ በሜዳው የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች በሌላ ሀገር እንዲጫወት በመገደዱ ፌዴሬሽኑ ለተጨማሪ ወጪ እየተዳረገ ነው ብለዋል።
በቅርቡ የአማራ ክልል መንግስት የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየምን ግንባታ ለማጠናቀቅ ተጨማሪ በጀት በመመደብ ግንባታው እንዲቀጥል መፍቀዱ አስደሳች መሆኑን ተናግረዋል።
የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በሀገሪቱ በጅምር ላይ ከሚገኙ ሌሎች ስታዲየሞች አንጻር የአመራር ቁርጠኝነት ከታከለበት በፍጥነት ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት የሚችል መኾኑንም ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ኢሳያስ ገለጻ እንደ ሀገር በጅምር ላይ የሚገኙ ስታዲየሞች የዲዛይን ችግር ያለባቸውና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ አለመሆናቸውን ተናግረዋል።
በተለይም ቪአይፒና መደበኛ ትኬት የሚቆርጡ ሰዎች መግቢያ ተመሳሳይ መሆን፣ ጋዜጠኞች ስራቸውን የሚሰሩበት የተመቸ ቦታ አለመኖር፣የተጨዋቾች መኪና የሚገባበት ምቹ መንገድ አለመኖር ክፍተት መሆኑን ነው ያነሱት።
ፌደሬሽኑ ስታዲየሞቹ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲሰሩ በሚደረገው ርብርብ የበኩሉን የቴክኒክ ድጋፍ ይሰጣል ብለዋል። ኢዜአ እንደዘገበው በዚህም ቀጣዩን የአፍሪካ ዋንጫ በምታዘጋጀው ኮቲዲቩዋር የሚገኙ ስታዲየሞችን በመጎብኘት ልምድና ተሞክሮ እንዲወስዱ ከተለያዩ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ ባለሙያዎች ወደ ሀገሪቱ እንደሚላኩ አቶ ኢሳያስ ተናግረዋል።
አዳዲስ መረጃዎች እንዲደርሶ ቻናላችንን ይቀላቀሉ
https://t.me/Daily_News_Ethiopian
https://www.facebook.com/DNEEthiopia
667 viewsedited 11:34