2022-08-23 17:53:14
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ከ149.8 ቢሊዮን ብር በላይ የፋይናንስ አቅርቦት ማድረጉ ተገለፀ።
===============
ይህ የተገለፀው ዛሬ ነሀሴ 17 ቀን 2014 ዓ.ም የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባብሪያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመሆን የሚያካሂደው የህዝብ ንቅናቄ እና የሀብት ማሰባሰብ መርሃ ግብር ማስጀመሪያ ዝግጅት ላይ ነው፡፡
በዝግጀቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ የግድቡ ሁለተኛ ተርባይን ሃይል ማመንጨት በመጀመሩና የሶስተኛ ዙር የውሃ ሙሌትም በስኬት በመጠናቀቁ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ የግድቡን ግንባታ ለዚህ ስኬት ላበቁ አካላት ሁሉም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ባንኩ የተጠናከረ የሀብት ማሰባሰብ ስራ በማከናወን መልሶ ለሃገራችን ልማትና ወሳኝ ለሆኑ ኘሮጀክቶች በማዋል ላይ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ አቤ፣ እ.ኤ.አ እስከ ሃምሌ 31 ቀን 2022 ድረስ ባንኩ ከሀይል ማመንጫ ስራዎች ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ካቀረበው ከ425.2 ቢሊዮን ብር በላይ ፋይናንስ ከ149.8 ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆነው ለታላቁ የህዳሴ ግድብ የዋለ መሆኑን ተናግረዋል።
ባንኩ ከሚያደርገው የፋይናንስ አቅርቦት በተጨማሪ በአገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ ከተከናወነ የቦንድ ሽያጭ እና በልገሳ በርካታ ገንዘብ በማሰባሰብ ለግድቡ ግንባታ እንዲውል ማድረጉንም ነው አቶ አቤ የገለፁት፡፡
ባንኩ በቅርቡ የ200 ሚሊዮን ብር ቦንድ በስሙ መግዛቱን ያስታወሱት አቶ አቤ፣ የባንኩ ሠራተኞችም ከ19.7 ሚሊዮን ብር በላይ ቦንድ በመግዛት ግንባታው እንዲፋጠን ማድረጋቸውን ገልፀዋል፡፡
አቶ አቤ ባንኩ ፕሮጀክቱ እስኪጠናቀቅ ከሀብት ማሰባሰብ ጀመሮ በሚጠበቅበት ሁሉ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠው፣ ባለድርሻ አካላት በሙሉ በጋራ እንዲሰሩ እና ታላቁን የህዳሴ ግድብ በየትኛውም መንገድ እንዲደግፉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በዝግጅቱ ላይ የተገኙት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ የግድቡ ግንባታ 87 ነጥብ 3 በመቶ መጠናቀቁን ገልፀው፣ ቀሪ ስራዎችን በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በእስካሁኑ የግንባታ ሂደት ከ175 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል ያሉት ኢንጂነር ክፍሌ፣ቀሪ ግባታውን ለማጠናቀቅም ከ55-60 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።
በመርሀ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሀብት በማሰባሰብ ሂደት ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ እየተወጡ ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት መካከል አንዱ እና ዋነኛው መሆኑ ተገልጿል፡፡
758 viewsedited 14:53