Get Mystery Box with random crypto!

.  በብዙ መልኩ፣ የክርስቶስን ክብር አበላሽቷል” (T.H.L. Parker , Portrait of C | አስተምህሮተ 🔱ክርስትና

.  በብዙ መልኩ፣ የክርስቶስን ክብር አበላሽቷል” (T.H.L. Parker , Portrait of Calvin Paperback, Desiring God, 2009, 113)። በወቅቱ የፓፓው ሥልጣን ከቃሉ በላይ እንደሆነ ተድርጎ ቤተ ክርስቲያን በታወረችበት ወቅት፣ ካልቪን በነፍሱ በመወራረድ፣ ቤተ ክርስቲያን በቅዱስ ቃሉ የበላይነት ሥልጣን ሥር መሆኗን አጥብቆ ሞግቷል፦

“የቅዱሳት መጻሕፍት ሥልጣን ምንጭ የእግዚአብሔር መንፈስ እንጂ ሰው አይደለም . . .  ሰው ሁሉ (ፓፓውንና ካህናቱን ጨምሮ) ለእግዚአብሔር ቃል ሥልጣን ተገዢ ናቸው . . . ቅዱሱ ቃሉ በሰው ሥልጣ ሥር አይደለም፤ ይልቁንም የቤተ ክርስቲያን ሕልውና መሠረቱ ቃሉ ነው፤ ። (Institutes, 1.7.2)።

ይህም ጽኑ አቋም፣ 25 ዓመት በአገልግሎት የሚቀደመው የሉተርም ነበር። ሉተር ቅዱስ አውጐስጢኖስን በመጠቀስ፣ "ቅዱሳት መጻሕፍት፣ ሕጸጽም ሆነ ግድፈት የሌለባቸው የእግዚአብሔር እስትንፋሳዊ ቃል መሆናቸውን አጥብቄ በማመን ይዤአለሁ" ሲል መስክሯል፤ ዋጋም ከፍሏል። (What Luther Says: An Anthology, ed. Ewald M. Plass [St. Louis: Concordia, 1959], 1:87)

የካልቪን 28 ዓመታት የአገልግሎት ሕይወት ቀላል አልነበረም። በብዙ መከራ የታሸ ነበር። መዝሙር 124፣ በተለይም፣ "ረድኤታችን ሰማይንና ምድርን በሠራ በእግዚአብሔር ስም ነው" የሚለው የልቡ ጥቅስ ነበረ። ባለቤቱ ኢደሌት (Idelette)፣ ባሏን በወረርሽኝ ሳቢያ ያጣች የሁለት ልጆች ባልቴት ነበረች። ከካልቪን ጋር ወደ አስር ዓመታት ያህል አብረው የኖሩ ሲሆን፣ በዙ መከራም አሳልፈዋል። የመጀመሪያ ልጃቸው የሁለት ሳምንት ሕፃን ሳለ ሞቶባቸዋል። ስለ ልብ ስብራቱም እንዲህ በሎ ጽፏል፦

“ጌታ በሐዘን ጅራፍ ልቤን ያቈሰለው አስኪመስለኝ ድረስ የልጄ ሞት አጥንቴ ውስጥ ዘልቈ ገብቷል። ይሁን እንጂ እርሱ ራሱ ሰማያዊ አባት ስለሆነ ልጅ ማጣት ምን ማለት እንደሆነ ይገባዋል፤ የእርሱም ፈቃድ ፍጹም፣ ለልጃችንም የተሻለውን ያውቃል በማለት በፍጹም ሉዓላዊነቱ ተጽናናሁ።” (T. H. L. Parker, Portrait of Calvin,  [SCM Press; 1st Edition, January 1, 1954, reprinted by Desiring God, 2009], 79)።

በተከታታይ የወለዷቸው ሁለት ልጆች በጨቅላ ዕድሜያቸው፣ በመጨረሻም ኢደሌት ራሷ በወረርሽኝ ወይንም በሳንባ ነቀርሳ ምክንያት ሞታበታለች። ባለቤቱን በማጣቱ ስላለፈበትና ከድባቴ ጋር ስላታገለው የልብ ሐዝን እንዲሁ ብሏል፦

“መሞቷ [በእግዚአብሔር ሉዓላዊ ፈቃድ] የተወሰነ ቢሆንም፣ ድኽነትን ብቻ ሳይሆን ሞቴን ለመጋራት ፈቃደኛ የሆነችውን የሕይወት አጋሬን በማጣቴ ጥልቅ ሐዘን ክፉኛ አስቆዝሞኛል።” (Parker, Portrait of Calvin, 80)

በዚህ ሁሉ የልብ ስብራት ውስጥ፣ ልቡን በእግዚአብሔር አምላኩ ያበረታ የተሐድሶ መሪ ነበር፤ ትጉህና መስቀል-ተኮር። በሁለት ሳምንት ውስጥ 10 ጊዜ (እሁድ ቀን ብቻ ሁለት ጊዜ) እንዲሁም በሳምንት ሦስት ቀን ነገረ-መለኮት ያስተምር ነበር። ከዮሐንስ ራእይ በስተቀር በአዲስ ኪዳን መጻሕፍት፤ በአምስቱም ኦሪቶች፣ በመጽሐፈ ኢያሱ፣ በመዝሙረ ዳዊትና በኢሳይያስ ላይ ማብራሪያ ጽፏል።

ይህን ሁሉ ይባትል የነበረው፣ በጄኔቭ የቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን መጋቢነቱ በተጨማሪ ነበር። በየቤቱ የታመሙትን፣ የተቸገሩትን፣ የተጨነቁትን፣ ወላጅ አልባዎችንና ችግረኛ ባልቴቶችን በታማኝነት ይጐበኝ ነበር። በቂ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት፤ በኩላሊት፣ በጨጓራ ቁስል፣ በሆድ ድርቀትና ተመሳሳይ ጤና መታወክና እንቅልፍ በማጣት ይሰቃይ ነበር። ይኽን ሁሉ መከራ በትዕግሥት ይቀበል የነበረው፣ በተገኘበት ማንም ሰው እንዲገድለው ቀዳማዊ ፍራንሲስ ያወጀበትን የሞት ዐዋጀ እያወቀ ነበር።

እንደ ጳውሎስ “በሕይወት ለመኖር እንኳ ተስፋ እስከምንቈርጥ ድረስ ከዐቅማችን በላይ የሆነ ጽኑ መከራ ደርሶብን ነበር። በርግጥም የሞት ፍርድ እንደ ተፈረደብን ይሰማን ነበር፤” (2ቆር 1፡ 8-9) ያለባቸው ብዙ ሞትን የተመኘባቸው የጨለማ ወቅቶች አሳልፏል። ይሁን እንጂ፣  ብድራቱን ትኩር አድርጐ ዘላለምን በማሰብና በእግዚአብሔር ሉዓላዊነት ላይ በመደገፍ በታማኘነት የክርስቶስን ወንጌል አገልግሏል።  - “የራሴ ጌታ እንዳልሆንሁ አውቃለሁ፤ ልቤን እውነተኛ መስዋዕት በማድረግ ለጌታዬ አሳልፌ ሰጥቻለሁ . . . ፈቃዴንና መከራዎቼን በሙሉ ለእግዚአብሔር አስገዝቼአለሁ።” በማለት!  (Portrait of Calvin, 74-75)። ሲሞትም፣ መቃብሩ ስም የለሽ እንዲሆን በትሕትና ተማጥኗል - ክርስቶስ በእርሱ ካደረገው ሥራ በስተቀር ስሙ እንዲዘከር አልፈለገምና።

“ጌታ ሆይ፤ በእውነት ለወንጌልህ እንድንኖርና ታማኝ ባለዐደራዎች እንድንሆን ጸጋህን አብዛልን።” አሜን!

ግርማ በቀለ (ዶ/ር)

ከ ነገረ ወንጌላውያን
https://t.me/negere_evangelical