Get Mystery Box with random crypto!

ሳስቼልህ እኮ ነው!! ➤ይድረስ የፍቅር ደብዳቤ ለምወድህ ለልጄ ከኔ ከሰማዮ አባትህ:- ልጄ ሆ | Christian Mezmur - ክርስቲያን መዝሙር

ሳስቼልህ እኮ ነው!!


➤ይድረስ የፍቅር ደብዳቤ ለምወድህ ለልጄ ከኔ ከሰማዮ አባትህ:-

ልጄ ሆይ: ምነው ምርር አልክብኝሳ? የዘገየሁብህ መሰለህ አይደል? አንዳንዴም ጨርሶ ያንተ ነገር እንደማያሳስበኝ መስሎ ተሰማህ አይደል? ስለምን ግር አለህ? ለምንስ ግራ ተጋባህብኝ?

በል እስቲ ስማኝ አሁን! ፀሎትህን እኮ አንዷንም ሳትቀር ሰምቻታለሁ ውስጥህ ያለው መሻትህንም በደምብ አውቀዋለሁ! በፊቴ ደፋ ቀና ማለትህም ከኔ አልተሰወረም! ግና ሳስቼልህ እኮ ነው ትንሽ ዝም ያልኩህ - ተጠንቅቄልህ እኮ ነው ለጥቂት ጊዜ ፊቴን ካንተ የሰወርኩብህ!

ልጄ ሆይ ላንተም ሳሳሁ ለወንድሞችህም ሳሳሁ! አንተም አሳሳህኝ ነገ ልታገለግላቸው ያሉት ግልገሎችና ጠቦቶቼም አሳሱኝ!

➤ምን መሰለህ?

ሲጀመር አንተ በህይወት መቀጠል የምትችለው እኔን እስካላጣኸኝ ብቻ ነው! እስትንፋስህ እኔ ነኝ! ህይወትህ እኔ ነኝ! የማንነትህ ምንጭ የሁለንተናህ መገኛ እኔ ነኝ! የማስፈልግህ እኔና እኔ ብቻ እንጂ አንተ ያስፈልጉኛል ብለህ የዘረዘርካቸውና የነገርከኝ ነገሮች ሁሉ አይደሉም!

አየህ እኔ ራሴን ልሰጥህ መንፈሴን ላፈስልህ ህልውናዬን ልጨምርልህ ስፈልግ በመጀመሪያ እኔን የሚጋርድብህን ሌላውን ነገር ሁሉ ከፊትህ ገለል አደርጋለሁ -ለጥቂት ጊዜም ቢሆን! የህይወት እንጀራህ እኔና እኔ ብቻ እንደሆንኩ ልክ ስንግባባ እኔን በምንም ነገር እንደማትቀይረኝ ስታመንብህ በዚያው ልክ አንተ የጠየካቸውን ትርፍራፊ በረከቶች ሁሉ መሸከም እስኪያቅትህ ድረስ እለቅልሃለሁ! እስቲ መጀመሪያ እደግልኝ ልጄ! እስቲ ምራቅህን ዋጥ አርግልኝ!

ሲቀጥል ደግሞ ሌላ ክርክርም አለኝ ካንተ ከልጄ ጋር!

ትንሽ ስባርክህ ትንሽ ፀጋዬን ስገልጥብህ ትንሽ ወጣ ወጣ ሳረግህ ቁልል እምትለው ነገርሳ?! ለመቆለልማ ብቆለል ሚያምርብኝ እኔ አልነበርኩ? አንተን ለማዳን ስል ክብሬን ዙፋኔን ከአብ ጋር መተካከሌን እርግፍ አርጌ ጥዬ የመጣሁት! መለኮትነትን ቁጭ አርጌያት የባሪያን መልክ ይዤ ራሴን ባዶ አርጌ የወረድኩት! ደሞ ዝቅ ብዬ የሚሸጠኝን እግር ያጠብኩት! ይሄ ሁሉ አንድም ፍቅር ግድ ብሎኝ ነው አንድም ትህትና ላስተምርህ እኮ ነው! ልጄ ሆይ እኔ እኮ መለኮት ነኝ አንተ ደግሞ አፈር! ለኔ ያልከበደኝ ታዲያ ላንተ እንዴት በዚህ ልክ ከበደህ?

እእእ........አንድ ሌላም ልጨምርልህ መቼም ሁሉን ዛሬውኑ እናውራው ካልን አንተም ይበዛብሃል! በየትኛው አቅምህስ ትችለዋለህ?

በቀደም ለት ልጆቼን ምከርልኝ ገስፅልኝ ስልህ ምን ሆነህ ነው ግን እንዳይሞቱ እንዳይተርፉ እንዳይበሉ(በ-ጠበቅ ብሎ) እንዳይዘሩ(ዘ-ጠበቅ ብሎ) አርገህ ጭፍጭፍ ያደረክብኝ? ምነው ልጄ? ምንም ቢሆን እኮ በስንት ጣር አምጬ ደሜን ጠብ አርጌ የወለድኳቸው ልጆቼ ናቸው!! ደሞ እኮ ከጥፋታቸው ተርፈው ልቦና ገዝተው ወደእኔ ወደአባታቸው ይመለሱልኛል ብዬ አይኔ ክርትት ክርትት እያለ እየጠበቅኳቸውም አይደል? በኔ ቅንዓት መቅናትህን ወድጄልሃለሁ! እውነትን አለመሸቃቀጥህ አስደስቶኛል: በየውሃት መንፈስ ማቅናትን ብትጨምርበት ደግሞ አንዳንዶች ከልክ በሚያልፍ ሃዘን ተውጠው ለጠላት እራት እንዳይሆኑብኝ ትጠብቃቸዋለህ! በል በሚቀጥለው እሷን ነገርህንም አስተካክልልኝ!

እስቲ እድግ በልልኝና ምራቅህን ዋጥ አርግልኝና ስክን በልልኝና ደግ ርህሩህ ልበ ሰፊ ሁንልኝና ደሞ ጠቢብ ልከኛ አስተዋይ ሁንልኝና ----ኦኦኦ ከሁሉ በላይ ደግሞ እውነትን ሳትለቅ ፍቅርን አብዝተህ እንደልብስ ልበስልኝና እንደመታጠቂያ ታጠቅልኝና ከርሞ ተመልሼ ስመጣ የልጄን የኢየሱስን መልክ ባንተ ላይ ላየው እናፍቃለሁ! የበረከቱ ነገር አያሳስብህ! እሷ ኢምንት ናት!!


ዶ/ር ላሊ -
Share Share Share
@KALTUBE
@KALTUBE
@KALTUBE