Get Mystery Box with random crypto!

#የአማኞች.ጋሻ #ክፍል.61 #ማስጠንቀቂያ ማስጠንቀቂያ በተለያዩ ሊቃውንት አንደበት የ | የአማኞች ጋሻ

#የአማኞች.ጋሻ
#ክፍል.61

#ማስጠንቀቂያ
ማስጠንቀቂያ







በተለያዩ ሊቃውንት አንደበት የአላህን ባህሪያት ማፋረስ ክህደትን (ኩፍርን) መፈፀም እንደሆነ የሚያስገነዝቡ ጥቅል ፍርዶችን መስፈርቶች ሳይሟሉ በቀጥታ በግለሰቦች ላይ ተፈፃሚ ማድረግ አይፈቀድም! ምክንያቱም በጥቅል ገለፃ “ይህንን የሰራ ካፊር ይሆናል!” ሲባል በዋነኝነት የሚፈለገው ተግባሩ የክህደት ተግባር (ኩፍር) እንደሆነ ማመላከት እንጂ ይህንን በየትኛውም ምክንያት የተገበረ ሁሉ ያለ ቅድመ-ሁኔታ ከኢስላም ይሰናበታል ማለት አይደለምና!



አሁንም ሸይኹ'ል-ኢስላም ኢብኑ ተይሚይ-ያህ እንዲህ ይላሉ፦

"...እንደነዚያ መሃይማንና መሰሎቻቸው ያልሉ ግለሰቦችን በተመለከተ አንዳቸው ነብያትን የተፃረረ መሆኑ የሚገለፅበት መለኮታዊ ማስረጃ ከፀናበት በኋላ ካልሆነ በቀር ከከሃዲያን እንደሚመደብ በመፍረድ በ"ኩፍር" ወደ መፈረጅ ማምራት አይፈቀድም! - ንግግሩ ያለምንም ጥርጥር የክህደት ንግግር ቢሆን እንኳ! ከፊል ቢድዓዎች ከከፊሉ የባሱ ከመሆናቸውና ከፊል የቢድዓህ አራማጆች ከፊሎቹ ዘንድ የሌለ (የተሻለ) እምነት ያላቸው ከመሆናቸው ጋር ይህ ገለፃ ማንኛውንም ግለሰብ በከሃዲነት መፈረጅን የተመለከተ ነው!




እናም ማንም ሰው ከሙስሊሞች አንዱ ቢሳሳት እንኳ ማስረጃው ፀንቶ እስኪደርሰውና እውነተኛው መንገድ እስኪገለጥለት ድረስ በከሃዲነት የመፈረጅ መብት የለውም! አማኝነቱ በርግጠኝነት የፀደቀ ሰው ይህ (አማኝነቱ) በጥርጣሬ አይወገድም፤ ይልቁንም ማስረጃው ከፀናበትና ውዥንብሩ ከፀዳለት በኋላ እንጂ አይወገድም!»(1 )
ይህንን ሚዛናዊ የአህሉ’ስ-ሱን-ናህ አካሄድ የሚፃረር ፅንፈኛ አቋም የሚያንፀባርቁት ግለሰቦችና ቡድኖች ዋነኛ ስህተት ሁለት እርከኖች አሉት፦




አንደኛው፦ ጥፋት ያልሆኑ ነገሮችን እንደጥፋት በመቁጠር፣ ወይም ጥፋት ቢሆኑ እንኳ ለክህደት ጭራሽ የማያበቁ ጉዳዮችን በማጋነን በክህደት መፈረጅ ሲሆን፤
ሁለተኛው፦ የኩፍር ወይም የሽርክ መገለጫዎችን የፈፀሙ ግለሰቦችን ወይም ቡድኖችን መስፈርቶች መሟላታቸውንና የብይኑን ተፈፃሚነት የሚያግዱ ምክንያቶች አለመኖራቸውን ሳያረጋግጡ በቀጥታ በከሃዲነት መፈረጅ ነው።




አንድ የኩፍር አቋም ያንፀባረቀ ግለሰብ በከሃዲነት እንዳይፈረጅ ሊያግዱ ከሚችሉ ምክንያቶች መካከል አለማወቅ፣ መሳሳት፣ መገደድና የመሳሰሉት ይገኛሉ።
ብዙ የቢድዓህ ጎጠኞች ሁለቱንም የስህተት እርከኖች በመፈፀም ህዝበ-ሙስሊሙን ሲያውኩና ሲከፋፍሉ እንደኖሩ የሚያረጋግጡ እማኞች በታሪክ ማህደር የሰፈሩ ሲሆን በነባራዊው ሂደት አንዳንዶቹ ዘንድ በተጨባጭ የምናየው የ“ተክፊር” ግንፍልተኝነትም በቂ መስካሪ ነው!(2 ) የሚደንቀው ግን ከላይ ያሳለፍነው የአህሉ’ስ-ሱን-ናህ ሚዛናዊ ብይን በተለያዩ ፅሁፎቻቸው ከመብራራቱ ጋር እነርሱን በተቃራኒው የተክፊር ጥማት ያለባቸው አድርጎ ለመሳል የሚደረገው ያላሰለሰ መፍጨርጨር ነው፤ የማንን ለማን?!







#መዝጊያ

#እንግዲህ አንባቢ ሆይ!


የአማኞች ጋሻ

1- እውነታው ግልፅ ነው! አላህ ለራሱ በቁርኣኑ ወይም በመልዕክተኛው አንደበት ያፀደቀውን ሁሉ ያለ ማመሳሰልና ያለ ትርጉም ማጣመም እንቀበላለን፤ ለርሱ ልቅና በሚገባ መልኩ የባህሪያቱን ጥቅል መልዕክት እናረጋግጣለን። ይህ ነው የነብያትና የተከታዮቻቸው ጎዳና! ይህ ነው ውዝግብን የሚፈታው ቀላሉ የመፍትሄ አካሄድ!




2- ሁል ጊዜም ቢሆን የነብያት ተከታዮች የሚጓዙበት መንገድ በህሊና ሰላምና በልቦና ስክነት የታጀበ ነው! ተፃራሪው ደግሞ በንትርክና በጥርጣሬ የተወሳሰበ ነው።
3- በአንዳንድ ሁኔታዎች የጥመት አቀንቃኞች በርዕሱ ላይ የሚያንፀባርቁት ትክክለኛ አቋም ካልለ ቀድሞውኑ በቁርኣንና በሐዲሥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሰፈረና የእውነት ተከታዮች ዘንድ የታወቀ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም፤ ስለዚህ ከነርሱ የሚከጀል አዲስ እውነታ የለም። እውነትን ከገጠሙባቸው ውጭ ያሉ ንግግሮቻቸው ደግሞ የቁርኣንም ይሁን ሌሎች አእምሯዊ መረጃዎች ላይ የተመረኮዙ አይደሉም፤ ሆኖም የሐቅ ተከታዮችን የሚጋፈጡባቸው ስልቶች በአብዛኛው ከሚከተሉት አራት ምድቦች አይወጡም፦








ሀ- አዳዲስ የቢድዓህ ፈሊጦችን መፈልሰፍና እነርሱን እንደ መመዘኛ ማቅረብ፤ ለ- ፅኑ እውነታዎች ላይ ማጠራጠሪያ ጥናቶችን ማቅረብ፤ ሐ- እነ “እገሌ”ን በጭፍን መከተል፤(1)



መ- እውነተኞችን በሀሰት ለማጥላላት መቅጠፍ! ይህንን አስተዋዮች አያጡትም!

---

(1) አላህ እንዲህ ይላል፦
 «ከጌታችሁ ዘንድ ወደናንተ የወረደውን ተከተሉ፤ ከርሱ ውጭ ሌሎች ረዳቶችን አትከተሉ!»[አል-አዕራፍ 3]


#ሶስት.ምክሮች


1ኛ- ትክክለኛውን ጎዳና ለሳቱ አላህ እንዲህ ይላል፦
 «“እኔ የምገስፃችሁ በአንዲት ነገር ብቻ ነው!” በላቸው! ፡- ለአላህ ብላችሁ ሁለት ሁለት ሆናችሁና ለየብቻ ተነስታችሁ ከዚያ እንድታስተውሉ!..»[ሰበእ 46]




ያስተውሉ! ተጨባጩ ዓለም እንደሚመሰክረው ብዙ ሰዎች በተሰበሰቡበት አጋጣሚ እውነታን አጣርቶ የሚያሳይ ውይይት መፈፀም እጅግ አስቸጋሪ ነው - በተለይ በእምነት ጉዳይ ላይ! ምክንያቱም በአብዛኛው ንፁህ እሳቤን የሚያደፈርሱና ጭፍን ወገንተኝነትን የሚቀሰቅሱ ሁኔታዎች መንፀባረቃቸው አይቀርምና! በአንቀፁ ላይ እንደተመለከተው ሁለት ሆነው አንዱ የደረሰበትን እውነታ ለሌላው በማቅረብ በቅንነት መወያየት ለአስተውሎት አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል! ለብቻው የሆነም ሰው ባልተረበሸ ልቦና መረጃዎችን የማገናዘብ እድል ይኖረዋል።(3 )




ከዚህ ጋር አላህ ቀጥተኛውን መንገድ እንዲመራን መማፀን ሊዘነጋ የሚችል ጉዳይ አይደለም!




(1) “መጅሙዑ’ል-ፈታዋ” (12/500-501)

(2) “አሕባሾች” ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ይሆናሉ! በርካታ ዑለማዎችን ጨምሮ ብዙዎችን ያለ አግባብ በከሃዲነት (በካፊርነት) እንዲፈርጁ ምክንያት የሆኗቸውን ግድፈቶች ከነእርማቶቻቸው በአጭሩ ለመቃኘት “ፊርቀቱ’ል- አሕባሽ” የተሰኘውን ጥናታዊ ፅሁፍ ከ(2/645) ጀምሮ ይመልከቱ።

3 ) “አል-በሕሩ’ል-ሙሒጥ” (ተፍሲር አቢ ሐይ-ያን) (7/290-291) ይመልከቱ።


ኢንሻአላህ ይቀጥላል.......
በተወዳጅ የሱና ኡስታዞቻችን የተፃፉ መፅሐፎች ለማግኘት፡፡

ሌሎችንም የተውሒድ ዕውቀት ለመሠብሠብ join


በ telegram

t.me/sadamnassirr s.


በዋትሳት

https://chat.whatsapp.com/Dyebl8aTWjmDeTcIBrdoC3