Get Mystery Box with random crypto!

ግንቦት 25/2015 ዓ.ም በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ 3ኛ ዙር አለም አቀፍ ኮንፍረንስ ተካሄደ። በም | Bule Hora University

ግንቦት 25/2015 ዓ.ም
በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ 3ኛ ዙር አለም አቀፍ ኮንፍረንስ ተካሄደ።

በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት በምርምርና ስርፀት ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት ‹‹አርብቶ አደርና የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም እንዴት ይቻላል?››በሚል ርዕስ በ25/09/2015 ዓ.ም 3ኛው ዙር አለም አቀፍ ኮንፈረንስ በዩኒቨርሲቲው ዋና ግቢ ኦዳ አዳራሽ ተካሂዷል::
በምርምር ኮንፍረንሱ ላይ የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፍቃዱ ወ/ማርያምን ጨምሮ ም/ፕሬዝዳንቶች፣የገዳ አባቶች፣የዩኒቨርሲቲው ምሁራን ፣አለም አቀፍ አጥኚዎች የትምህርት ባለሙያዎች፣ፖሊስ አርቃቂዎች፣ሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ ያሉ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት እና ሌሎችም ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
የኮንፍረንሱን አጀማመር በተመለከተ በአካባቢው ባህል መሠረት በአባገዳዎች ምርቃት የተጀመረ ሲሆን የዩኒቨርሲቲው የምርምር እና ስርፀት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፍፁም ደምሴ በዚህ ታላቅ ኮንፈረንስ ላይ ለተገኙት ተሣታፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት በማስተላለፍ የጥናትና ምርምሩ ዋና ዓላማ ሣይንሳዊና በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር በማበጀት የሰዎችን ኑሮ የተቃና እንዲሆን ማድረግ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
አቶ ፍፁም አያይዘውም ዩኒቨርሲቲው አራት ዋና ዋና የልህቀት ማዕከላትን መሠረት አደርጎ የሚሠራ መሆኑን በመጥቀስ በዛሬው ዕለት ለኮንፈረንሱ የተዘጋጀው ርዕስ ዩኒቨርሲቲው ትኩረት ሰጥቶ ከሚሰራባቸው ከግብርና ጋር የተገናኘ እና ወቅታዊ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በሌላ መልኩ በኮንፍረንሱ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የዩኒቨርሲቲው ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ዶ/ር ትንሣኤ ታምራት በተመሳሳይ መልኩ ዩኒቨርሲቲው በአራት ዋና ዋና የልህቀት ማዕከላት ማለትም በማዕድን፣በጤና፣በግብርና እና ሀገር በቀል ዕውቀትን መሠረት አደርጎ የሚሠራ መሆኑን በማስረዳት የአየር ንብረት ለውጡ በተለይም በጉጂና ቦረና አካባቢ እያደረሰ ያለው ተጽዕኖ ከባድ በመሆኑ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ትንሣኤ አያይዘውም ይህ በዓይነቱና በይዘቱ ልዩ በሆነው ኮንፍረንስ ላይ አርብቶ አደሩ የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም ተጠቃሚ በሚሆኑባቸው ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ መስራቱ አስፈላጊ መሆኑን በመጠቆም በዕለቱ የተጀመረው ኮንፍረንስ የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ እንዳልሆነ በመጥቀስ የተጋበዙት እንግዶችም ወደ መጡበት ሲመለሱ ይህኑንን አሠራር በማስፋት ለወደፊቱ የተጠናከረ ግንኙነት እንደሚፈጥር አስረድተዋል፡፡
በኮንፈረንሱ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፍቃዱ ወ/ማርያም የተገኙት እንግዶችን እና የኮንፈረንሱ አዘጋጆችን በማመስገን በምርምሩ ዙሪያ ኮንፈረንስ መደረጉ ሁለት ዋና ዋና ጠቃሜታዎች ማለትም በአሁኑ ሰዓት የአየር ንብረት ለውጥ እያደረሰ ያለውን ጉዳት የምንገነዘብበትና አዲስ መረጃ የምናገኝበት መሆኑን በመጠቆም በጋራ በመሥራት አርብቶ አደሩን በመደገፍ ተጠቃሚ መሆን በሚችልበት የመፍትሄ ሀሳቦች ዙሪያ ውይይት የሚደረግበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ዶ/ር ፍቃዱ ይህን መሰል ኮንፍረንሶች ላይ በመገኘት በጋራ መወያየቱ ጠቀሜታው ያለንንና ያጣናቸውን ነገሮች ለመለየት ከማስቻሉም በላይ በአሁኑ ሰዓት የአየር ንብረት ለውጡ በተለይ በአርብቶ አደሩ አካባቢ ምን ያክል ጉዳት እያደረሰ እንዳለ ለመረዳት የሚያስችል ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ አክለውም የምርምር ኮንፈረንስ መዘጋጀቱ ለማህብረሰቡ በተለያዩ ችግሮች ዙሪያ የመፍትሔ ሀሳቦችን በማጋራት ደረጃ የምሁራን ሚና ከፍተኛ መሆኑንም ተናግረዋል።
ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ