Get Mystery Box with random crypto!

በሺህ ዘጠኝ መቶ ሰባ ሰባት ዓ/ም ? የአማርኛ ሙዚቃ ንግሰ ነገስቱ ጥላሁን ገሰሰ አዲስ አልበሙን | ከመጻሕፍት ዓለም - Book shelf 📗📚📖

በሺህ ዘጠኝ መቶ ሰባ ሰባት ዓ/ም ? የአማርኛ ሙዚቃ ንግሰ ነገስቱ ጥላሁን ገሰሰ አዲስ አልበሙን ከለቀቀ ገና የአንድ ሰንበት ዕድሜ ላይ ነበረ፡፡ ይሀ ሲሆን የሙሀባ ይመር ልጅ ዚነት ሙሀባ የመጀመሪያ አልበሟ ለብርሃን ሲበቃ በጥላሁን እንደሚዋጥ ሳይታለም የተፈታ ጉዳይ ሆነ፡፡ ለጊዜው የተባ ተስፋ አልነበረም፣ ውቅያኖሱ ባህሪቱን የሚውጣት ይመስል ነበር፡፡ ግን ባህሪቱ ውቅያኖስ ሆነች፡፡ ለቅጽበት እንኳ ልትደበዝዝ ዕድል አልጠመመባትም፡፡ የተፈራው አልሆነም፡፡

ስጋት የሆነው ጥላሁን በፈገግታ የሚታቀፍ ውበት እንጅ ዚነትን ሰልቅጦ የሚያጠፋ እሳተ ገሞራ እንዲሆን የሙዚቃ አማልክቱ ላሎ አልፈቀደም፡፡ ልጁ ኩርማን ጋፋ ላሎም ቢሆን ለጠይሟ እመቤት አዳልቶ በአውሎ ዘንግ ላይ የምትውለበለብ ሰንደቅ አደረጋት እንጂ አሳልፎ ለቀባሪ አልሰጣትም፡፡ እናቷ አርፋ ቀድሞ ለተደገሰ ለሙዚቃ ድግስ በቃሏ የምትገኘዋ ዚነት በማራቶን ሙዚቃ ቤት በኩል ነገሰች፡፡ ሕይወት የራሷ ሕግና ስርዓት አላት፤ ዘመንም የራሱን ጀግና ይፈጥራል ማለት እንዲህ ነው፡፡ በዘመኑ የህዝብ ለህዝብ ኮንሰርትን አሰናድተው (ባልሳሳት) የአማርኛ ሙዚቃ ልዑሎችና አበጋዞች በዓለም ዙሪያ ቀድሞ በሀገራችን ለተከሰተው ድርቅ እርዳታ ላረጉ ሀገራት ምስጋና ለማቅረብ በሙዚቃ ድግስ ሲዟዟሩ የሀበሻ ምድር ከዚነት ሙሀባ አንደበት ጣዝማ ሲዝቅ ነበር፡፡ እነዚያ ፊውታራሪዎች ከበጎ ተግባራቸው መልስ አገር ቤት ሲገቡ ግን ያልተገመተ ክስተት ጋር ተፋጠጡ፡፡ አዎ…. አንዲት ጠይም ልዕልት የመዲናይቱን ጭፈራ ቤቶች አጥልቅልቃዋለች፡፡ በየሸክላ ማጫወቻው ዚነት ሙሃባ ይሏት ሸጋ የወሎ ለዛዋ ባጣፈጠው ድምጧ ተስረቀረቀችበት፡፡ አውራጃው ሁሉ ስሟ ናኘ፡፡ አልበሟ ካገር ባህር ማዶ ተሻግሮ ተደመጠ፡፡ ያኔ ታዲያ የህዝብ ለህዝብ ቄሳሮችን ‹‹ከየት የመጣች ተኣምር ነች!›› አሰኝታለች፡፡ በቦረከና ወንዝ ዳር ያደገችው ያች እንቡጥ አበባ ገና በልጅነት በሰርግና በማህበረሰባዊ በዓሎች ላይ የጀመረችው የሙዚቃ ሕይወት እንዲህ ሀገር አቀፍ ጣዕም ለመሆን አበቃት፡፡ ይህ እንግዲህ ኩርማን የዚነት ሙሀባ ዜና መዋእል ነው!!

ከውዴታ በመነጨ ቅን ስሜት ተከተበ፡፡
የሳትኩት በአፈ ሊቃውንት ይታረምልኝ!!

ጋሻው የኋላሸት (ዘቢደር)