Get Mystery Box with random crypto!

ጠይሚቱ ልዕልት ባለሙሀባይቱ የሸኽ ሙሀባ ይመር ልጅ!! ÷÷÷÷÷÷÷÷÷÷÷÷÷÷÷÷ (ጋሻው የኋላሸት | ከመጻሕፍት ዓለም - Book shelf 📗📚📖

ጠይሚቱ ልዕልት
ባለሙሀባይቱ የሸኽ ሙሀባ ይመር ልጅ!!
÷÷÷÷÷÷÷÷÷÷÷÷÷÷÷÷
(ጋሻው የኋላሸት (ዘቢደር)

አየዋ… ልቤን በንሻጤ የሚንጣት እልፈ ነገረ ኪን በጎሰመኝ ልክ የነፍስያዬን ጣዕመ-ዜማ ላዜምልህ እየከጀልኩ የዘመኑ መንፈስ አስሮ ይለጉመኛል፡፡ አየህ ቀን ሲበላሽ እንዲህ ያደርጋል፡፡

እመዋ… የውበትን ትርታ ምት ልቀኝልሽ፣ ለዛ ያለውን የሚያንስፍስፍ የፍቅር ጨዋታ ላሰማሽ ውስጤ እየወደደ ጌዜው አንደበት ይነሳኛል፡፡ አየሽ ለስላሳዬዋ የሰው ጠይም እንጂ የጊዜ ጠይምነት አያምርም፡፡

የምወዳችኹ ሆይ እስቲ ዛሬ'ኳ በድፍረት ዘማሪ ልሳኔ ወደ እዝነ ልቦናችሁ የሥን ቅኝቱን ያስረቅርቅ፡፡ መቸስ የወደደ… ውዴታውን አምጦ መውለጃ አፍታ አያጣም!

ወዳጆቸ… ጦሳ ሲባል በጦስኝ፣ በአደስ፣ በጠጅ ሳር አበባ የተቀመመ ጥዑም መዓዛ ያለው አየር ካለሁበት ድረስ ነፍሶ ያውደኛል፡፡ ጦሳ እንደ ገልአድ ተራራ ለምስል ከሳች ስንኝ የተመቸ ነው፡፡ ጦሳ እንደ ኢቨረስት ውሃ የሚረጋበት፣ እንደ ብሶተኛ ሰው በሆዱ ባህር እልፍ ሚስጥር የፀነሰ ዝምታ ነው፡፡ እነደ ቄርሜሎስ ተራራ ሱባዔ ቢይዙበት ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ያገናኛል፡፡ ይህን ስንል ራስ ዳሽንን ማሳነሳችን አይደለም፡፡ የሶሎዳ ተራራን ማናናቃችን እንዳይመስላችሁ፡፡ ይልቅስ ትከሻ ለትከሻ እያደጋገፍናቸው ነው፡፡ ጦሳ እንኳን ላገር ቤቱ ለባህር ማዶ አምባዎችም የቅርብ ተጠሪ ወዳጅ ነው፡፡ አዎ ጦሳ ለዓይን ሳይሞላ ለልብ የደረሰ ሰራጺ ሚስጥር ነው፡፡ ከጦሳ ተራራ ግርጌ ደግሞ ገጻቸው ደም-ግባት ያጋተ ሸጋ ሸጋ ሳዱላዎች ቀን ተቀን ይፈልቁበታል፡፡ የውበት ዥረት በደርባባይቱ ወሎ ጉያ ይገማሸራል፡፡ ለነገሩ ወሎ የነመስቀለ ለክብራ፣ የነቴጌ መነን ሀገር አይደለ'ዴ ልባም እና ሸጋ መች ይጎድልበታል፡፡ የነዳና መስገጃ፣ የነላሊበላ መቀደሻ አይደል'ንዴ በምን ሒሳብ ኢማነኛና ባለኢልም ሊርቀው ከቶ!! ያጋምሳዎች አድባር፣ የራያዎች አዋይ፣ የየጁዎች መንበር፣ የላስታዎች መናገሻ ወሎ ምን ጎድሎባት ትታማለች? እንደው በደፈናው ከእያንዳንዱ የወሎ ደፍ የቁንጂና ሰብል አሽቷል፡፡ የነባህሩ ቃኘ ጎራ የሙሀባ አዝመራ አፍርቷል፡፡ ኸይርያዬን ይንሳኝ ስላቹሁ! ወሎ የልብ ምት፣ የግልገሎች ሙቀት ናት፡፡

እንግዲህ ይህን ሁሉ የምዘባርቅባችሁ ስላንዲት የወሎ ልዕልት ለማዜም ነው፡፡ እሷስ የሀበሻ ምድር ጣፋጪ ድምጥ ናት፡፡ አዎ! የኢትዮጵ እንቆጵ ነች እሷ፡፡ ይህች ድምጸ መረዋ እዚች አቢሲኒያ ውስጥ በአማርኛ የሙዚቃ ሰገነት ላይ ንግስና የማያንሳት ልዕልት ነበረች፡፡ እሲ ልተዝታት፡፡ እሷ'ኳን ዘካሪ፣ አደግድጎ አስተዋሽ ሎሌ ብትፈልግ ከ'ኔ በላይ የሚራቀቁትን አታጣም ነበር፡፡ ልቤ ግን ለገዛ ራሱ ደስታ ይቺን የስለት ልጅ፣ ይቺን ገና በእናቷ ማህጸን ሳለች የነብይ ዓይን የፈሰራትን ደርባባ አወዳሽ ሁኛለሁ፡፡ ያ የምስራቁ ነገረ-ፈጅ ኦሾ ከስም ሁሉ ለአፍ የሚጣፍጥ ስም እያለ ጂብራን ኻህሊል ጂብራንን ያወሳል፡፡ እኛም ባገራችን የስም ባለጸጋዎች ነን፡፡ ሸግዬ! የተኳኳለ ግብሩን የሚሻረክ ስም በየእልፍኙ አናጣም ብንፈልግ፡፡ ግን ደሞ ዚነት ሙሀባ የሚሉት ሁለት ቃሎች ነፍስ አንደበት ቢኖራት ደጋግማ የምትጠራው ልብ አጥጋቢ ስም ነው፡፡

‹‹የንጋት ኮከብ›› እያለች ገና በንጋት እድሜዋ የጣዝማ ድምጧን ወለላ ያቋደሰችን ያች የጣዕም መለኪያ ልዕልት ሲያደምጧት ልብ ታለመልማለች፡፡ ‹‹አንድ ቡቃያ ልጅ በሚስጥር ወድጀ›› እያለች ስትብሰከሰክ በግርምት ታጠምዳለች፡፡ ‹‹ምን ይሻላል››ን ስታዜመው እልፉን ነገረ-ሕይወት በንቃት ዓይን ለመቃኘት ያነሳሳል፡፡ ‹‹ና ሽሽጌ›› እያለች ስትጣራ ትንፋሽ ታሳጣለች፡፡ ‹‹እንደው ከንበል ደፋ›› በሚል የውበት መወድሷ የሕይወት መልካም ገጽ ጋር ታላትማለች፡፡

ዚነት ሙሉ ኪነት፡፡ ዚነት ጠይም ውበት፡፡ ከሸኽ ሙሀባ ይመር አስራ ሶስት ልጆች ብቸኛዋ እንስት ናት፡፡ ወትሮም ልባም ሴት በወንዶች መሀል አማልክት ሁና መከሰት ተፈጥሯዊ ስሪቷ ነው፡፡ ባለሙሀባይቱ ዚነት ሙሀባ በዚያች በጦሳ ግርግጌ ከሚገኙ የገጠር መንደሮች መንጪታ በሀገራችን አድማስ ላይ የሚያጥበረብር ብርሃን ፈንጥቃለች፡፡ በእዝነ-ልቦና አፀድ የጸደቀች አበባ ሁናለች፡፡

ወሎ የትሕትና ምግባረ-ቤት ናት፡፡ ወሎ የመተናነስ አስኳል፣ የመከባበር ሉል ናት፡፡ ወሎ መታበይን የምትጸየፍ፣ ወዴታን ማተቧ ያደረገች ያይናማዎች ምኩራብ ናት፡፡ ስለዚህ ነው የወሎ ልዑላን በያደባባዩ እዩን እዩን የማያበዙት፡፡ ስለዚህ ነው የወሎ ሁረል ዐይኖች ከታዋቂዎች ይልቅ ለአዋቂዎች ያሚያዳሉት፡፡ ወሎ የእብሪትን እብጠት፣ የሸፍጥን ቡግንጅ፣ የንቀትን ላህጪ ከጡሀራ ልቧ ጠራርጋ ያስወገደች የቅዱስ መንፈስ ማደሪያ ናት፡፡ ስለዚህ ነው ልጆቿ ፀሓይ ግዙፍ ሳሉ እንደ ኮከብ አንሰው የሚታዩት፡፡ ወሎ ዝቅ በማለት ውስጥ ለላቀው ከፍታ የምትታደም ናት፡፡ ወሎነት ደግሞ አንድ ሆኖ ሁሉንም መሆን ነው፡፡ ሁሉን ሆኖ በአንድነት መሰየም ነው፡፡ ወሎ እመ ብዙሀን ናት፡፡ ትራራለች፡፡ ስለዚህ ነው ማንም የሚወዳት፡፡ ወሎ አቅፋ ታከብራለች እንጅ ገፍትራ አትጥልም፡፡ ወሎ አፍቅራ ታገዝፋለች እንጅ ጠልታ አታኮሰምንም፡፡ ለዚህም ነው ከቅኝቶቿ ዜማ የጨለፈ፣ ሰነ-ቃሏን የጨለፈ ሁሉ ስሙ በኸይር ሀውዛ የሚጠመቀው፡፡ ዚነት የወሎ ውጤት ናት፡፡ ዘለስ ያለች ናት በትግስት፡፡

የዚነት ሙሀባ ወላጆች ሴት ልጅ ተርበው ሴት አማልክት ተሰጥተዋል፡፡ ዚነት የተጸነሰችበት አብራክ በወንዶች ጋጋታ ቢሞላም ደርዘን ወንድ የምታስንቅ አንዲት ፍሬ ልዕልት ሲያሸት ግን በዓይናማዎች እይታ ስር ውሏል፡፡ ‹‹ይህቺ ልጅ ስሟ በሰፊው አድማስ ላይ ይናኛል›› የተባለላት ናት ገና በአባቷ ወገብ ስር ሳለች፡፡ ይህች ያይን ማረፊያ እንቁ ተወልዳ የተነገረላትን ትንቢት በገሃድ ለመግለጥ ዕድሜ አልፈጀባትም፡፡ ገና በለጋነት ወቅቷ የላሊበላን የባህል ቡድን ለመቀላቀል፣ የወሎ ባህል አምባ ውስጥ ንግስተ ንግስት ለመሆን በብርሃን ፍጥነት ነበር የተምዘገዘገችው፡፡ ግጥምና ዜማዎችን ከማንም ቀድማ ቀብ የማድረግ ጸጋዋ ድንቅ ነበር፡፡ የአዘፋፈኗ አገረኛ ለዛ እዝን ጠላፊ ነበር፡፡ ጠይሚቱ ልዕልት ብትወዛወዝ የባህር ዌቭ፣ ብትዘፍን የማዕበል ዳንስ ነበረች፡፡

ዚነት ሙሀባ… ቀረብ ሲሏት በውበት ሙሀባ የምትጠልፈው የስህበት እሳቷ በፍቅር የተለከፈባት በሽጉጥ እስኪስታት ድረስ የተፈቀረች የደስ ደስ ያላት ጠይም እንኮዬ ናት፡፡ ገና በልጅነት እድሜዋ በቤተሰብ የታጨላትን የማታውቀውን ባል እቢኝ አሻፈረኝ ብላ እጅ መንሻ የወርቅ ጥሎሹን ያስመለሰች ልባም እንስት ናት፡፡ ፈገግታ የማይርቃት፣ የፍካት ወጋገኗ የሚጋባ ፍልቅልቅ የቁንጅና ሙዳይ ነበረች ስትወሳ፡፡ ገና በአፍላ ዕድሜዋ፣ የብርሃኗ ወጋገን ባልደበዘዘበት ቀትር ባጭር የቀረችው ዚነት ሰው መውደድ ያለስስት የተቸራት ነበረች ይላሉ አብሯ አደጎቿ፡፡ በስራዋና በዝናዋ ኩራትና ተኣቢዮ የማይነካት ልባም መሆኗ ዛሬም ይመሰከርላታል፡፡ ግልጽና ከሁሉም ጋር ተላማጅ በመሆኗ በልብ ትታማለች።

የነመሐመድ አቦል ሀገር ኢልምና ሙሀባ በግፍ ተችሮታል፡፡ የነአሰፋ አባተ፣ የነማሪቱ ለገሰ ቀየ ዜማና የኪን ሜሮን ነጥፎበት አያውቅም፡፡ የነሙሉጌታ ተስፋዬ አድባር ደም ግባታም ስንኝ ተዝቆ አይጎድልበትም፡፡እነሆ ዛሬም በተተኪዎቹ እያበበ ነው!