Get Mystery Box with random crypto!

'በስንቱ' እንቃጠል ?! A Blasphemy on Masculinity or / and/ Vs Empo | ከመጻሕፍት ዓለም - Book shelf 📗📚📖

"በስንቱ" እንቃጠል ?!
A Blasphemy on Masculinity or / and/ Vs Empowering Feminism ?.
ቤ.ማ.ተ
-------------------------------
ምድረ ሐበሻ አባወራ ( በተለይ ዘመናዊው ) ከ "በስንቱ" ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ጋር እልህ የቀላቀለ ፍቅር ይዞታል።
( በጣም እርግጠኛ ነኝ!) ።

ምድረ ዘመናዊ አባት ከእያንዳንዱ የድራማው ክፍል በሗላ ለሰው የማይነግረው፣ ለራሱም በቅጡ የማይገባው ድብልቅልቅ ስሜት ይዞ "እየሳቀ" ( እንደ ፋንዲሻ ) ወደ መኝታው ይሔዳል።

በዛች ምሽት ግን የሚስቱ እና የሴት ልጆቹ "ሳቅ" ከሌላው ግዜ ለየት ይልበታል።

በማይካደው የተዋናዮቹ ድንቅ የትወና ብቃት እና በድራማው የተዋጣለት የዝግጅት ጥበብ ተዋዝቶ የሣቅ ጭንብል የሸፈነው ስሜቱ በሁለት ባልተረዳቸው ተቃራኒ ፅንፎች መሐል ይንዠዋዠዋል ።

ውሎ አድሮ ከኑሮ የውጣ ውረድ ወከባው ቆጥቦ ባስተረፋቸው ብጥስጣሽ የቡና ሰአቶቹ መሀል ሳይፈልግ ስለ "በስንቱ" ያሰላስላል ። የሚስቱ እና የሴት ልጁ የለበጣ ሳቅ ትዝ ይለዋል። በየሀሳቡ መሀል "እምምም በስንቱ ልቃጠል!" ይላል።

የገፀባህሪያቱን ወጥ የሆነ ባህሪ ሲያስብ፣ ተያይዞም ሊተላለፍ የታሰበውን መልእክት ሲጠረጥር የሆነ የተጠና ስውር ደባ ነገር ይሸተዋል።

የትውስታ ማሕደሩን ሲበረብር ግልፍ ግልፍ ለሚለው ስሜቱ የአመክንዮ ታኮ ሊሽጥለት ይታገላል።

፩-የበስንቱ ድራማ ወንድ ገፀባህሪያት በሙሉ ስለምን እንዲያ ተሳሉ? ።

፪-በድራማው ላይ "ወንድነትን" የወከሉ አባትነት፣ አያትነት ( ወንድ አያት) ፣ አጎትነት ፣ ወንድ ልጅነት እንዲሁም በየታሪኩ ገደምዳሜ ብልጭ የሚሉ ወንድ ገፀ ባህሪያት በሙሉ ስለምን እንዲያ በዘቀጠ እና ሀላፊነትን ሊሸከም በማይችል ስብእና ተሳሉ?
በአጋጣሚ ወይንስ... ?

፫-በተቃራነው በድራማው ውስጥ የተወከሉ "ሴትነትን" የሚወክሉ ገፀባህሪያት በሙሉ በአስተዋይ፣ አዋቂ እና ሀላፊነታቸውን በቅጡ መወጣት የተሳናቸውን ጅላጅል ተባእት ገፀ ባህርያትን እየተከታተሉ በማረም ( በማረቅ ) ስራ የተጠመዱ፣እንዲሁም "በባህላዊው" አባታዊ ስርአታችን
( patriarchal system) ላይ ሙድ በመያዝ ባተሌ በሆኑ እና ውስጥ ለውስጥ በደንብ የሚናበቡ "smart" ሆነው ተሳሉ?
በአጋጣሚ ወይንስ .....?

የሚሉ ጥያቄዎች ይሞግቱታል ።

ለዘመናት የተከተልነውን ወንዳዊውን ስርአት (patriarchal system) ለመሞገት ከታሰበስ ያን ያክል እርቀት መሔድ ተገቢ ነው ወይ?።

ነባሩን እና ባህላዊውን አባታዊ ስርአታችንን ለመተቸት እና "በዘመናዊው" (ከምእራባውያኑ በተዋስነው ስርአት) "ሊያድግ ይገባዋል ፣ ትኩረት እና እውቅና ተነፍጎታል" የሚባልለትን እያደገ የመጣውን የሴቶችን ጉልህ ድርሻ ለማሳየትስ ተባእትነትን ( አባትነትን) ያን ያክል ማንጓጠጥ ተገቢ ነው ወይ?።

Betemariam Teshome (post)



(የልጥፉን ጥያቄ ሙሉ ለሙሉ ኮሜንቱ የመለሰ ባይሆንም የዘመናዊውን ትዳር ምን መምሰል እንዳለበት የራሷን ምልከታ አጋርታለች።)



አንድ ግልጽ መሆን ያለበት ነገር አለ፡፡ የለመድናቸው Gender roles እየተቀየሩ ነው፡፡ ሴቶችን ከሚስነት እና ከእናትነት አልፈው፤ ገቢ በሚያስገኙ የሙያ ስራዎች ላይ እየተሳተፉ ነው፡፡ መሳተፍ ብቻ አይደለም ከወንዱ የተሻለ ገቢ እያመጡ ነው፡፡ በትምህርት፣ በእውቀት፣ በልምድ የተቀሸረ የራሳቸው ሃሳብ ባለቤት እየሆኑ ነው፡፡ ወንዱ የፈለገውን ሃሳብ አምጥቶ ሊያራግፍባቸው የማይችሉ አይነት ስብዕና ባለቤት እየሆኑ ነው፡፡ ድህነት እና ምርጫ ማጣት ከሚጥልባቸው የጭቆና፣ የባርነት፣ የግርድና፣ የጥቃት ትዳር ማምለጥ የሚችሉበት አቅም በተለይም የኢኮኖሚ አቅም እየፈጠሩ ነው፡፡ እኚህን ሴቶች አግብተህ፣ እንደ አያትህ በበታችነት እና በተገዢነት፤ በንቀት እና ምንም አያውቁም አይነት ጨዋታ አእየተጫወትክ ልታኖራቸው አትችልም፡፡ አቅም የፈጠረች ሴት፤ የራሷ ድምጽ የሌላት፤ ሁሉን እሺ የምትል፣ እራሷን እላፊ ጎድታ ልጆቿን እና ባሏን የምትንከባከብ፣ ለቤተሰቧ ብላ ሁሉን ጥቃት፣ ሁሉን ውርደት፣ ሁሉን ጫና በዝምታ የምትሸከም ሚስት ልትሆን አትችልም፡፡ መታገል ትጀምራለች፡፡

“Working mom” የሆነች ሚስት ያለችው እንደ በስንቱ ያለ ወንድ... የሚከተሉትን የማድረግ እድሉ የመነመነ ነው፡፡

በፈለገው ሰአት ልጅ ማስወለድ አይችልም፡፡ ልጅ መውለድ የጋራ ውሳኔ የሚፈልግ ነገር ይሆናል፡፡ ስገባ ስወጣ ጎንበስ ቀና በይልኝ፤ ልብሴን እጠቢ፣ እግሬን እጠቢ፣ ምግቤን ከሽኚ፤ ተነጠፊ ተዘርጊ ማለት አይችልም፡፡ እሷም ስትሰራ ውላ፣ ደክሟት ነው የምትገባው፡፡ የሚያዝንላት፣ የሚያግዛት፣ የሚንከባከባት ባል ትፈልጋለች፡፡ እኔ ሳልፈቅድልሽ ከቤት መውጣት አትችይም ማለት አይችልም፡፡ ስራው በራሱ ከቤት መውጣቷን ግዴታ ያደርገዋል፡፡ እኔ ሳልፈቅድልሽ ገንዘብ ማውጣት አትችይም ማለት አይችልም፡፡ ሰርታ የምታገኘው ገንዘብ ነው፤ ነጻነት ያስፈልጋታል፡፡ የሀይል ሚዛኑን ለማስጠበቅ በሚል ሲወጣ ሲገባ ሚስቱን መቀጥቀጥ አይችልም፡፡ የዛሬዋ ሚስት የባልነት እና የሚስትነት መብትና ግዴታን በቅጡ የተረዳች ስለሆነች ከቧላ ስድብን፣ ዱላን፣ ንቀትን፣ ማን አለብኝነትን በጸጋ አትቀበልም፡፡ የዛሬዋ ሚስት የምትወደው የሚወዳት፤ የምታከብረው የሚያከብራት፤ የምታምነው የሚያምናት፤ ዋጋ የምትከፍልለት ዋጋ የሚከፍልላት፤ የምትንከባከበው የሚንከባከባት፤ የምታደምጠው የሚያደምጣት፤ ባል ትፈልጋለች፡፡

ዘመናዊው ትዳር በሁሉም ነገር የጋራ ውይይት እና ውሳኔ ይፈልጋል፡፡ ከሁለቱም ወገን ፍቅርን፣ መከባበርን፣ መረዳዳትን፣ መተሳሰብን ይፈልጋል፡፡ እኔ ወንድ ስለሆኑኩ አእንዲህ ይደረግልኝ፤ ሴት ነሽ እንዲህ አድርጊ ብሎ የሚነሳ ክርክር ካለ... ውሃ አይቋጥርም፡፡ ግጭትን እንጂ ሰላምን አይፈጥርም፡፡ መናናቅን እንጂ መከባበርን አያጎለብትም፡፡

ሂሩት ሰራተኛም ሆናም... ከወንዱ አንጻር ሲታይ የቤቷን የእለት እለት አስተዳደር በመምራት የሚስተካከላት የለም፡፡ ቤትን በአግባቡ ማስተዳደር ለሴት የተሰጠ መክሊት እስኪመስል ድረስ... ወንዶቹ ላይ መዝረክረክ ይታያል፡፡ መሰልቸት ይታያል፡፡ መማረር ይታያል፡፡ለአንድ ሳምንት ፊልድ ብትሄድ የተከሰተውን ማየት ብቻ በቂ ነው፡፡ የሂሩት ቤተሰቦች ውስጥ ብንገባ፣ በጡረታ እድሜ የሚገኙት የሂሩት እና እና አባት .... ሴት በሚል የወል ስም ምግብ የሚያበስለው ማነው? ቤት የሚጸዳው ማነው? በሌላ በኩል ወንድ በሚል ማእረግ ቁጭ ብሎ የሚቀለበው ማነው? ሆዱ ሲሞላ ደግሞ ወጣ ብሎ ቢራ የሚጠጣ፣ ኳስ የሚያይ፣ ከሰው ጋር የሚገናኝ ማነው?

ወንዱ Bread winner ስለሆነ፣ ባህሉ ስለሚደግፈው፣ ሀይማኖቱ ስለሚደግፈው፣ ... የቤቱ ራስ፣ የሴቷ አዛዥ ተደርጎ የሚቆጠር፣ ውጭ ሰርቶ ሲመጣ ቤት ውስጥ የንጉስ አይነት መስተንግዶ የሚገባው፣ እረፍት የሚገባው፣ መፈራት፣ መከበር የሚገባው፣ ምርጥ ምርጡ ሁሉ ሊቀርብለት የሚገባው፣ እሱ የሚለው ብቻ የሚደመጥለት ... ካልሆነ ደግሞ ሚስቱን በመደብደብ ጭምር አባወራነቱን የሚያረጋግጥበት ትዳር ነው የለመድነው፡፡ በተለይም ሴቷ ሙሉ በሙሉ የኢኮኖሚ ጥገኛ የሆነችበት፣ የመደራደር አቅሟ ዝቅተኛ የሆነበት ትዳር ነው የለመድነው፡፡