Get Mystery Box with random crypto!

_አነ ዘክርስቶስ_ ለአላዋቂ ፎገራ ዱሩ ነው እንዲሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን | በትረማርያም አበባው

_አነ ዘክርስቶስ_
ለአላዋቂ ፎገራ ዱሩ ነው እንዲሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ሳያውቁ በመሰለኝና በግምት ሲሳደቡ የሚውሉ ብዙ ናቸው። የቤተክርስቲያናችን አካሏ ራሱ ክርስቶስ ነው። የቤተክርስቲያን ትምህርቷ፣ ቅዳሴዋ፣ ማኅሌቷ፣ ትርጓሜዋ፣ ቅኔዋ፣ ዝማሬዋ፣ መዋሥእቷ ሁሉ ነገሯ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ማዕከል ያደረገ ነው። እርሱ የቤተክርስቲያን መሠረቷና አካሏ ነውና። ብዙ ሰው የእኔ ብሎ በሚያስበው ይመካል። የእኔ ዘመድ፣ የእኔ የትውልድ ስፍራ፣ የእኔ ክልል፣ የእኔ ሀገር፣ የእኔ አህጉር፣ የእኔ ንብረት፣ የእኔ መልክ፣ የእኔ ሰው፣ የእኔ መምህር፣ የእኔ ጳጳስ፣ የእኔ እውቀት ወዘተ ብሎ በሚያስበው ሲመካ ይስተዋላል። ነገር ግን ሁሉም ለሁለንተናችን ዋስትና አይሆኑም። ምክንያቱም እኒህ የጠቀስናቸው ሁሉ ፍጡራን ስለሆኑ ሕጸጽ አለባቸው። ሁሉም ደካሞች ናቸው። ለሰው ልጅ ለመኖሩ ምክንያት ፈጣሪያችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ብንወድቅ ያነሣን፣ እኛ ብንሞት ሞቶ ያዳነን እርሱ ነው። ብንራብ ሥጋውን ቆርሶ እንኩ ብሉ አለን። ብንጠማ ደሙን አፍስሶ እንኩ ጠጡ አለን። እኛ ክርስቲያኖች የምንመካው በክርስቶስ ነው። ከክርስቶስ ፍቅርም የሚለየን የለም። ቅዱስ ጳውሎስ መኑ የኀድገነ ፍቅሮ ለክርስቶስ ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል!? ረኀብኑ ረኀብ ነውን!? ተሰዶኑ መሰደድ ነውና!? መጥባሕትኑ ሾተል ነውን!? እያለ ይዘረዝራል። እኒህ ሁሉ ከክርስቶስ ፍቅር አይለዩንም። ክርስቲያኖች በዚህች ምድር ኖረውም በአኗኗራቸው ክርስቶስን ይሰብካሉ። ሞተውም በሞታቸው ክርስቶስን ይሰብካሉ። እመኒ ሐዮነ ለእግዚአብሔር ነሐዩ ብንኖር ለእግዚአብሔር እንኖራለን። እመኒ ሞትነ ለእግዚአብሔር ንመውት ብንሞትም ለእግዚአብሔር እንሞታለን።

ክርስቲያኖች አንድን ነገር የሚለኩት በኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ ነው። ኦርቶዶክሳዊው አስተምህሮ ደግሞ ከእግዚአብሔር የተገለጠ፣ በነቢያት የተነገረ፣ በክርስቶስ የተሰበከ፣ በሐዋርያት የተነገረ፣ በሊቃውንት የተመሠጠረ ነው። የክርስቲያኖች ሀገራቸው እውነት ናት። ንጉሣቸው ክርስቶስ ነው። ምግባቸው ፍቅር ነው። አኗኗራቸው በትሕትና ያሸበረቀ ነው። በወንዝ አይታጠሩም። ወንዜኛ፣ መንደረኛ፣ ጎጠኛ፣ ብሔርተኛ አይደሉም። ክርስቲያኖች ማንንም ሰው በእኩልነት ያያሉ። ከየትም ይወለድ ከየትም ይኑር ጻድቅን ያከብራሉ። ከየትም ይወለድ ከየትም ይኑር ኃጥእን ይገሥፃሉ። አሁን ዘረኝነት አይሎ ብዙው አእምሮውን አጥብቦ ሲታይ ከእውነት ምን ያህል እንዳፈነገጠ ያሳየናል። ሰው ወደ ሰውነቱ ሊመለስ ይገባዋል። በዘረኝነት ዓለም እየኖረ ራሱን በውሸት ባያኖር መልካም ነው። ዘረኛ ሰው ቅዱሳንን ሳይቀር በዘረኝነት እሳቤ ይመለከታል። በተወለዱበት ቦታ ብቻ ለማጠር ይሞክራል። ይሄ አሳዛኝ ነገር ነው። የቅዱሳን አለቃቸው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ ለዓለም ተሰቅሎ ዓለምን እንዳዳነ በዚህም ምክንያት መድኃኔዓለም እንደተባለ ሁሉ ቅዱሳንም አለቃቸውን አብነት አድርገው የጸለዩት ለዓለም ነው። በረከታቸውም በጸሎታቸው ለታመነ ሁሉ ነው። ስለዚህ ሰው ከታጠረበት የዘረኝነት አጥር ወጥቶ፣ ትምክህቱን በፍጡራን አገልጋዮች ላይ አድርጎ አነ ዘጳውሎስ አነ ዘአጵሎስ ማለቱን ትቶ አነ ዘክርስቶስ ማለት ይገባዋል። የሺ ፍልጥ ማሰሪያው ልጥ እንዲሉ ሐዋርያት ቢያስተምሩ ጸጋን የሚሰጥ ክርስቶስ ነውና። ጸጋዌ ጸጋ እግዚአብሔርን መውደድ የሚገለጠው ደግሞ ትእዛዛቱን በማክበር ነው።

አነ ዘክርስቶስ