Get Mystery Box with random crypto!

መለኪያችን ቤተክርስቲያናችን (በስምዐ ጽድቅ ኤልያስ) ብዙ ጊዜ በዚህ ማኅበራ | በትረማርያም አበባው Betremariam Abebaw

መለኪያችን ቤተክርስቲያናችን

(በስምዐ ጽድቅ ኤልያስ)

ብዙ ጊዜ በዚህ ማኅበራዊ ሚዲያው ላይም ሆነ ከእኅትና ወንድሞች ጋር ስንነጋገር የማስተውለው ደግሞም የሚያሳዝነኝ ነገር ለግለሰቦች የሚሰጥ ጭፍን ድጋፍና ተቃውሞ ነው።ተቃውሞም ሆነ ድጋፍ የራሱ ልክና መጠን አለው።አንዳንዱ ሰውማ ለአምልኮት ሩብ ጉዳይ የሆነ፣እና ወደ አምልኮት የተጠጋ ድጋፍ ነው የሚሰጠው።በዚህ ምክንያትም ያ የሚደግፈው ሰው የተነካ ሲመስለው ለምን እንደዚያ እንደተባለ እንኳ ሳያውቅ፣ለማጣራትም ፍላጎት ሳይኖረው ዘራፍ ይላል።ያንን የሚደግፈውን ሰው ነካ ያላቸውን አካላትም ለመስደብ፣ለማንኳሰስ፣ለማስጠላትና ለማጸየፍ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም።የማይናገረው ጸያፍና ክብረ ነክ ቃል የለም።ያለ የሌለውን የስድብ ውርጅብኝ ያወርድበታል።ሰይጣን ክፉ ነው።ይህንን ለሚያደርገው ሰው ለሃይማኖቱ እየተጋደለ እንደሆነ እንዲሰማው በማድረግ እሱ ራሱ እንኳ ሳያውቅ ነፍሱን ክፉኛ ያቆስልበታል።እንዲህ አይነት የተሰወሩ ኃጢአቶች ምን ያህል አደገኛ እንደሆኑ እና ውሎ አድሮ መጨረሻቸው እኛ ካሰብነው በተቃራኒው መንፈሳዊ ሕይወታችንን እንደሚጎዳው በዜና አበውና በቅዱሳት መጽሐፍት ተደጋግሞ ተገልጧል።ቢያንስ የአቡነ ሺኖዳን Diabolic Wars የሚለውን መጽሐፍ እንኳ ብናነበው መንፈሳዊ በሚመስሉ እና አንዳንዴም ልንጠረጥራቸው በማንችላቸው መንገዶች እንኳ ሰይጣን እንዴት እንደሚያጠምደን እንረዳለን።
አሁን አሁን ደግሞ በተደጋጋሚ ከማስተውላቸው ችግሮች አንዱ ሙሉውን የቤተክርስቲያን ትምህርት በአንድ ሰው ወይም መምህር የመለካት አባዜ ነው።
መምህሩን ወይም ሰውዬውን በቤተክርስቲያን ትምህርት እንለካለን እንጅ ቤተክርስቲያንን በሰው አንለካትም።በሰው ያልተሰራች የማይወሰነው የክርስቶስ ንጽሕት፣ቅድስት አካሉ ናትና።ከዚህ የተነሳ አንድን ሰው ወይም አካል የምንደግፈውም ወይም የምንቃወመውና የምንተቸው ከተገለጠው ኦርቶዶክሳዊ የቤተክርስቲያን እውነትና ትምህርት፣ከቅዱስ ትውፊትና ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ይሔዳል አይሔድም የሚለውን መርምረንና መዝነን ነው።በአጭሩ መለኪያችን ሐዋርያዊ የሆነው የቤተክርስቲያን ትውፊት፣ትምህርት እና ነገረ ድኅነት ነው።ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ ቃል ኪዳን በነገረ ድኅነት በሚለው ይህንን የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የነገረ ድኅነት ትምህርት መለኪያነት እንዲህ ሲል ይገልጸዋል።"የመዳን ትምህርት ወይም ነገረ ድኅነት የቤተክርስቲያን ትምህርት መሠረትና የማዕዘን ድንጋይ ነው።ማንኛውም አስተሳሰብ ፣አስተምህሮ እና ሐሳብ የሚመዘነውና የሚለካው በነገረ ድኅነት መሠረት ነው፣"[፩]።ስለሆነም የአንድ ሰው ትምህርት እና አስተሳሰብ ይዘትና አካሒድ በትውፊትና በቅዱሳት መጻሕፍት ከተቀበልነው የቤተክርስቲያን ሐዋርያዊ ትምህርት እየመዘንን እንጠቀማለን እንጅ እኛ የምንወደው ወይም የምንደግፈው ሰው ስለተናገረው ብቻ እንደእውነት ተቀብለን መሔድ አግባብ አይደለም።ፍጹም ተገቢም አይደለም።ከጭፍን ድጋፍና ተቃውሞ እስካልወጣን ድረስ የሰይጣን መጫወቻ መሆናችን የማይቀር ነገር ነው።
በአንድ ሰው ትምህርት፣ሀሳብ ወይም ጽሑፍ ላይ ከመጠን ያለፈ አለመደገፍን በተመለከተ በነገረ አበው ጥናትም ትምህርተ አበው እንዴት ይጠናል በሚለውና የአበውን ድርሳናት እንዴት እንጠቀም በሚለው በአንድ አባት ጽሑፍ ላይ ብቻ እንዳንንጠለጠልና እንዳንወሰን ከዚያ ተመስርቶም ወደ ተሳሳተ ድምዳሜ እንዳንደርስ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለብን ይመከራል።ግብጻዊው ሊቅ ያዕቆብ ማላቲ ይህንን ሲገልጹ እንዲህ ይላሉ። '' We must not rely on the writings of a single Father, because no one is capable of acknowledging the “truth” in its entirety. We only accept the opinion of a Father, if it is in harmony with the Bible and the church tradition." [፪]። የቀደምት አበውን ትምህርቶች፣ጽሑፎችና ድርሳናት፣ሀሳቦች እንኳ የምንመዝነውና የምንቀበለው ከቅድስት ቤተክርስቲያን ቅዱስ ትውፊትና ከቅዱስ መጽሐፍ ጋር እስከተስማማ ድረስ ብቻ ነው።
በፕሮቴስታንቱ ዓለም የምንመለከተው አንዱ መሠረታዊ ችግርም ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ እነሱ ወደ ሚፈልጓቸው የተወሰኑ ጥቅሶች ተገዥ የማድረግ፣አንዳንዴም ሌላው የሌለ ያህል በመቁጠር እነሱ ሀሳባቸውን ይደግፉልኛል ላሏቸው እና ለሃሳባቸው ይስማማሉ ላሏቸው ጥቅሶች መጽሐፍ ቅዱስን ማውረድና መመዘን ነው።በሌላ አነጋገር የአንድን ጥቅስ ትርጉም ለመረዳት ከአጠቃላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ሀሳብ አንጻር ከመመዘን ይልቅ መጽሐፉን ከዐሥር ለማይበልጡ ጥቅሶች ተገዥ የማድረግ አካሒድ አለ።The danger of Single verse ይሉታል።The danger of Single source ቢሉትም ያስሔዳል።ይህ አካሒድ መልኩን ቀይሮ በእኛም ዘንድ በሌላ ገጽ ተከስቷል።ይህም ከላይ እንደተገለጸው በተወሰኑ መምህራንና ሰዎች ልክ የቤተክርስቲያንን ትምህርት የመስፋት አዝማሚያ ነው።አንድ መምህር ወይም አጥማቂ፣ወይም ባሕታዊ ነኝ ባይ ላይ ከልክ ያለፈ መደገፍና ያ ሰው የተናገረውን ሁሉ እንደ ብቸኛ እውነት የመቁጠር ክፉ ደዌ ከተጠናወተን ቆይቷል።በዚህ ምክንያት ሰዎቹ ከቤተክርስቲያን በላይ እስከመታየት ደርሰዋል ወይም ተከታዮቻቸው አድርሰዋቸዋል።
ወደ እኛ ወቅታዊ ጉዳይ ስመጣ ብዙ ሰው የየራሱ መመህር ያዘጋጀበት ዘመን ነው።ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ አብርሆት ሆኖ የተናገረው በእኛ ዘመን ግልጥ ሆኖ ይታያል።'ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሱበት ዘመን ይመጣልና [...] እንደ ገዛ ምኞታቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ያከማቻሉና።እውነትንም ከመስማት ጆሮዎቻቸውን ይመልሳሉ፣ወደ ተረትም ፈቀቅ ይላሉ'[፫]። መምህራኑን ከቤተክርስቲያን ፣በቤተክርስቲያን በኩል ያገኘናቸው መሆኑንና ቤተክርስቲያን የሰጠችን መሆኑን ረስተን የአንድ መምህር ፣አባት፣ባሕታዊ አድናቂ፣ደጋፊና ቲፎዞ ሆነን የምንቀር ትቂቶች አይደለንም።እውነት ለመናገር የእኛ ድንቁርና የተመቻቸው ትቂት የማይባሉ 'መምህራን':'ባሕታዊያን'
እና 'አጥማቂያን' እንደፈለጋቸው የሚጋልቡንም የእኛ ከቤተክርስቲያን ትምህርት ይልቅ ግለሰብ ላይ መንጠልጠላችን ስለተመቻቸው ነው።ቅዱስ ጳውሎስ 'ሁልጊዜ እየተማሩ እውነትን ወደ ማወቅ ሊደርሱ ከቶ የማይችሉ'[፬] ሲል እንደገለጸው ሁል ጊዜ እንማራለን ብንልም እውነቱን ከሐሰት፣ልክ የሆነውን ካልሆነው፣ሰማያዊውን ከምድራዊው፣ሥጋዊውን ከመንፈሳዊው ለመለየት እንኳ የማንችል አድሮ ቃሪያ መሆናችን እጅጉን ያሳዝናል።ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ ስለ መምህር ግርማ ከበደ ምሥክርነት በሰጠበትና ኦርቶዶክስያ በሚለው መጽሐፍ መቅድም ላይ ይህንን እውነቱን ከሐሰት መለየት ያለመቻል ጽኑ ሕመማችንን ልብ ድረስ ሰቅስቆ በሚገባ አገላለጽ እንዲህ ሲል ይገልጸዋል።ከጽሑፌ ርዕስ ጋር በቀጥታ የማይሔድ ቢኖርም እንዳለ ልጥቀሰው።ዓላማው የእኛ እውነትን ከሐሰት መለየት አለመቻል ምን ያህል ጎጅና አደገኛ እንደሆነ ለማሳዬት ጭምር ስለሆነ።የብርሃኑ ቃል እንዲህ ይነበባል።''በእኛ ዘመን ነገሮችን እጅግ ከባድ ካደረጉብን ነገሮች አንዱ ተጠርጎና ታጥቦ የተደፋ ያህል ፈሊጥ ወይም መለየት ከትውልዱ በእጅጉ መሰወሩ ነው። የእኛ ዘመን አጥማቂዎች፣ ቅብዐ ቅዱስ ቀቢዎች፣ ትንቢት ተነግሮናል፣ እገሌ ይመጣል፣ እገሊም መጥቷል የሚሉት ሰዎች የበዙት ፈሊጥ ስለጠፋ ነው። እንኳን ይህ ከመንፈስ የሆነው ቀርቶ