__ጦማር ዘጴጥሮስ__ ቁጥር ፬:- ለጥምቀት በዋጋ መማለጃ የተቀበለ የተሻረና የተወገዘ ነው። | በትረማርያም አበባው Betremariam Abebaw
__ጦማር ዘጴጥሮስ__
ቁጥር ፬:- ለጥምቀት በዋጋ መማለጃ የተቀበለ የተሻረና የተወገዘ ነው።
√
ቁጥር ፭:- ልጄ ሆይ የክህነትን ስጦታና የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ በገንዘብ አትሽጥ። በክህነት ላይ አትነግድ።
√
ቁጥር ፮:- በክህነት መማለጃ የሰጠም የተቀበለም ክህነት የለውም።
√
ቁጥር ፯:- የበደለህን በየሰባቱ ሰባ ጊዜ ይቅር በለው።
√
ቁጥር ፰:- ከኃጢአቱ ንስሓ የሚገባን ተቀበለው የበደለውንም ይቅር በለው። በእጅህም አንሣው ገሥጸውም። የታመሙትን ጎብኝ፣ የተራቡትን አብላ፣ የተጠሙትን አርካ፣ የተራቆቱትን አልብስ፣ ወደታሠሩትም ሂድ።
√
ቁጥር ፱:- ከእግዚአብሔር ቅዱሳት መጻሕፍትን ስማ።
√
ቁጥር ፲፩:- አባት እናት ለሌለው እራራለት። በራስህ ላይ ለሰይጣን መንገድ አትስጥ።
√
ቁጥር ፲፫:- ችግረኛ ካህን ካየህ ከተቀበልከው ገንዘብ እርዳው።
√
ቁጥር ፲፬:- ለአብያተ ክርስቲያናት፣ ለአድባራትና ለገዳማት ግንባታ ራስህን አትጋ።
√
ቁጥር ፲፯:- ችግረኛን ከቤትህ በር ላይ አታባረው። ቸል ቸል አትበለው። አትናቀው። አታቃለው። ከአንተ ጋርም በማዕድህ እንዲቀመጥ አድርገው።
√
ቁጥር ፲፱:- ምእመናንን ለመጥቀም ካልሆነ በስተቀር ወርቅና ብር አትሰብስብ።
√
ቁጥር ፳-፳፩:- ለምእመናን ልጆች ሰላምን አብዛ። ልጄ አረጋውያንን አክብራቸው። ነገራቸውንም ስማቸው። ገሥፀው ንገረው እንጂ በኃጢአቱ ምክንያት በሰው ላይ አትሳለቅ። እግዚአብሔርን ወደ መፍራትም በየዋህነት መልሰው።
√
ቁጥር ፳፪:- ቀጥተኛ በሆነ ነገር ነገሥታትን እዘዛቸው። በመጥፎ ሥራቸው ውቀሳቸው። ቁርባን መቁረብ ጥፋትን ይከላከላል።
√
ቁጥር ፳፫:- በ3ኛው፣ በ7ኛው፣ በ12ኛው፣ በ30ኛው፣ በ40ኛው፣ በ60ኛው ቀን ሙታንን አስቧቸው። ልጄ ሆይ የተጠመቀ ኃጢአተኛ ነፍሱ በሞተ በ40ኛው ቀን ከክርስቶስ ፊት እንደምትቀርብ እወቅ። እንደ ሥራውም ይከፈለዋል።
√
ቁጥር ፳፬:- ምእመናን የመለኮትን የተቀደሱ መጻሕፍት ለመስማት በእግራቸው ይቁሙ። ለመጠመቅ የሚፈልግን ሰው በውኃ ከመጠመቁ በፊት የደስታ ቅባት ቀባው። ከተጠመቀ በኋላ ደግሞ ቅብዐ ሜሮን ቀባው።
√
ቁጥር ፳፱-፴:- ያልተጠመቀ ሰው ያረደውን አይብሉ። የአይሁድን ቂጣ አትብሉ። ከእነርሱ ጋር አትጋቡ።
√
ቁጥር ፴፪:- አማኝ ሆይ መተኛት በፈለግህ ጊዜ ፊትህን አማትብ። ከሰማዕታት አፅም ተባረክ።
√
ቁጥር ፴፫:- ካህን ሆይ ከንጹሕ ስንዴ በቀር በመሥዋዕቱ ላይ ስብና ሥጋ አታቅርብ። በመሠውያው ላይም አታስቀምጥ። ከወይን ፍሬ በስተቀርም ከጠጅ መሥዋዕት አትሥራ። የስንዴ እሸት በደረሰ ጊዜ የተለቀመ ይሁን።
√
ቁጥር ፴፭:- የፋሲካ በዓል ከሁሉም በዓላት ይበልጣል። ይከብራልም። ከደስታ በስተቀር ሐዘን አይደረግበትም።
√
ቁጥር ፴፮:- በቅዳሴ ጊዜ ሙታንን ሁልጊዜ አስታውሱ። እጅግ ይጠቅማቸዋልና።
√
ቁጥር ፴፯:- ከቂጣ በዓል በኋላ በሚውለው እሑድ የፋሲካን በዓል አክብሩ።
√
ቁጥር ፵፬:- የሕጉን ታቦት ሁሉ ባርክ። በእግዚአብሔር ማኅተም አትመው። በምትባርከው ጊዜ ሰባት ቀሳውስት ከአንተ ጋር ይኑሩ። ክህነትን ለመስጠትም በቅብዐ ሜሮን አትም። እንዲሁም ንጉሥን ለማንገሥ አትም።
√
ቁጥር ፶፩:- ከሊቀ ካህናት ሳያገኝ ክህነትን ነጥቆ የወሰደ ሰው ቢኖር ከእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ይሰናበት።
√
ቁጥር ፶፪:- በሰንበታትና በበዓላት የዮሐንስን ወንጌል በመሠውያው ላይ ያንብቡ። እርሱ የመለኮትን ምሥጢር የሚናገር ነውና።
√
ቁጥር ፶፫:- በሁሉም ቤተ መቅደስ ውስጥ ሁለት መሠውያ ይኑር። አንዱ ከቦታ ወደቦታ የሚንቀሳቀስ፣ ሁለተኛው ከቦታው የማያነቃንቁት ይሁን።
√
ቁጥር ፶፯:- ሕዝባዊ ካህንን ቢሰድበው ወይም ቢረግመው እግዚአብሔር ከሚመለክባቸው አገሮችና ከቤተክርስቲያኑ ይሰደድ።
√
ቁጥር ፷:- ከምእመናን ኃጢአቱ የበዛ ሰው ቢኖርና እንዲወገድለት ቢፈልግ ኃጢአቱን ለካህን እና የእግዚአብሔርን መጻሕፍት ለሚያውቁ ሊቃውንት ይግለጣት።
√
ቁጥር ፷፪:- የክህነት ልብስ ከሌሎች ሕዝባውያን ልብሶች የተለየ ይሁን። ልብሱ ከመጠምጠሚያው በስተቀር ሰፊ ይሆን ዘንድ ይገባል።
√
ቁጥር ፷፬:- ካህን ቀን መዝሙረ ዳዊትን ያንብብ፣ ሌሊት ደግሞ የነቢያትን ምስጋና ያንብብ።
√
ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን
መ/ር በትረማርያም አበባው