Get Mystery Box with random crypto!

_የሐዋርያት ሲኖዶስ ክፍል ፲_ #አብጥሊስ አብጥሊስ ፵፪:- ኤጲስ ቆጶስ ወይ | በትረማርያም አበባው Betremariam Abebaw

_የሐዋርያት ሲኖዶስ ክፍል ፲_
#አብጥሊስ
አብጥሊስ ፵፪:- ኤጲስ ቆጶስ ወይም ቄስ ወይም ዲያቆን ከአበደረው ዘንድ ወለድ ቢፈልግ ከመዓርጉ ይሻር።

አብጥሊስ ፶፪:- ከካህናት ወይም ከሕዝባውያን መካከል በሰው ላይ የተሳለቀ ወይም የሳቀ ቢኖር ይሻር። ከአጋጠመው ችግር ተነሥተህ ማንንም አትሳደብ።

አብጥሊስ ፶፭:- ኤጲስ ቆጶስ ወይም አገርን የሚያስተዳድር ከካህናት የተቸገረን ሰው በድብቅ ዐይቶ ለችግሩ የሚፈልገውን ባይሰጠው ችግሩንም ባይቀርፍለት ይሻር።

አብጥሊስ ፶፯:- ከምእመናን መካከል ዝሙት በማብዛት የወደቀ ካለ ይህም የዘወትር ልማድ ቢሆነው ወይም ግብረ ሰዶም የሚፈጽም ሰው ቢኖር ስለ ነፍሱና ስለ ንስሓው ልቅሶ ያብዛ። ከክህነት መዓርግ በየትኛውም አይሾም።

አብጥሊስ ፷፬:- በመዓርጉ ከመሾሙ በፊት ሁለት ያገባ ኤጲስ ቆጶስ ወይም ቄስ ወይም ዲያቆን ቢኖር ይሻር። የሾመውም ይሻር። የሾመው ኤጲስ ቆጶስ ለሹመት ያበቃው ግብሩን ሳያውቅ ከሆነ ግን የተሾመው ብቻ ይሻር።

አብጥሊስ ፷፮:- ከካህናት ወይም ከሕዝባውያን ከአይሁድ ጋር ጾማቸውን የሚጾም ፋሲካንም ከእነርሱ ጋር የሚያደርግ ወይም ከበዓላቸው ስጦታ ወይም ቂጣና የመሳሰለውን የተቀበለ ካህን ቢኖር ይሻር። ሕዝባዊ ከሆነ ከቤተክርስቲያን ይሰናበት።

አብጥሊስ ፷፰:- የቤተክርስቲያን የሆነ ንዋየ ቅድሳት ወይም የብር ዕቃ ማንም ወደቤቱ ወስዶ ሊጠቀምበት አይገባም።

አብጥሊስ ፸፪:- ሐሜት፣ ስድብ፣ ሽንገላ፣ መሳለቅ፣ የሰውን ስም ማጥፋት፣ ለራሳቸው በእነርሱ ዘንድ የሌለውን መልካም ዜና አግዝፎ መናገር ይህ ሁሉ እግዚአብሔርን የመሳደብ ምሳሌ ነው።

አብጥሊስ ፸፮:- ኤጲስ ቆጶስ ከመኳንንት ሥራ በምን ላይ አይሾም። ለሁለት ጌታ መገዛት የሚችል የለምና።

አብጥሊስ ፹:- ምእመናን እነዚህን (ቀጥለው ያሉትን) መጻሕፍት ይጠብቁ። ቁጥራቸውም 81 ነው።
፩ ኦሪት ዘፍጥረት
፪ ኦሪት ዘጸአት
፫ ኦሪት ዘኍልቍ
፬ ኦሪት ዘሌዋውያን
፭ ኦሪት ዘዳግም
፮ መጽሐፈ ኢያሱ
፯ መጽሐፈ ሩት
፰ መጽሐፈ ነገሥት (፬ቱ)
፱ መጽሐፈ ዕዝራ (፪ቱ)
፲ ትንቢተ ሶፎንያስ
፲፩ ትንቢተ ሚልክያስ
፲፪ ትንቢተ ሚኪያስ
፲፫ ትንቢተ ኢዩኤል
፲፬ መጽሐፈ መክብብ
፲፭ መጽሐፈ ኢዮብ
፲፮ መዝሙረ ዳዊት
፲፯ መጽሐፈ ምሳሌ
፲፰ መኃልየ መኃልይ
፲፱ ትንቢተ ዕንባቆም
፳ ትንቢተ ሆሴዕ
፳፩ ትንቢተ ዘካርያስ
፳፪ ትንቢተ ኢሳይያስ
፳፫ ትንቢተ ኤርምያስ
፳፬ ትንቢተ ሕዝቅኤል
፳፭ ትንቢተ ዳንኤል
፳፮ መጽሐፈ ጥበብ
፳፯ መጽሐፈ ዮዲት
፳፰ መጽሐፈ ሲራክ
፳፱ መጽሐፈ ኩፋሌ
፴ የማቴዎስ ወንጌል
፴፩ የማርቆስ ወንጌል
፴፪ የሉቃስ ወንጌል
፴፫ የዮሐንስ ወንጌል
፴፬ የሐዋርያት ሥራ
፴፭ የጴጥሮስ መልእክታት (፪)
፴፮ የዮሐንስ መልእክታት (፫)
፴፯ የያዕቆብ መልእክት
፴፰ የይሁዳ መልእክት
፴፱ የጳውሎስ መልእክታት (፲፬)
፵ ራእየ ዮሐንስ
፵፩ የቀሌምንጦስ መጻሕፍት
አብጥሊስ ፹፩:- ቅዱሳት መጻሕፍትን ከጠበቃችኋቸው ድኅነት ታገኙባቸዋላችሁ። በመካከላችሁ ሰላምና አንድነት ይሆናል። ባትጠብቋቸው ግን ይፈረድባችኋል።

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን
መ/ር በትረማርያም አበባው