Get Mystery Box with random crypto!

-----------------ክፍል ፭---------------- #ሃይማኖተ #አበው #ዘዲዮናስዮስ ምዕ | በትረማርያም አበባው Betremariam Abebaw

-----------------ክፍል ፭----------------
#ሃይማኖተ #አበው #ዘዲዮናስዮስ
ምዕራፍ ፲:-የዲዮናስዮስ ታሪኩ እንዲህ ነው። በግሪክ አቴንስ የፍልስፍና መምህር ነበረ። የፍልስፍናውን ትምህርት እያስተማረ ሳለ በዕለተ ዓርብ ጌታ ሲሰቀል ፀሐይ ስትጨልም ጨረቃ ደም ስትሆን ከዋክብት ሲረግፉ ምድር ስትነዋወጥ አየ። ይህ ሁሉ የተደረገ በዓለም ሁሉ ነበርና። ወነሥአ አርስጣላበ ዘውእቱ መዳልወ አልባብ። እንደፀሐይ ዓለሙን
ሁሉ በሚያሳይ መነጽር ሲመለከት ጌታ በቀራንዮ በመስቀል ተሰቅሎ በመስቀሉ ራስ እልመክኑን ወረደ ኀበ እሊኣሁ ወእሊኣሁ ሰቀልዎ የሚል ጽሑፍ ተጽፎ ያያል። በዚህ ጊዜ ዲዮናስዮስ ከዙፋኑ ወርዶ አለቀሰ። ፍልስፍና የሚያስተምራቸው ደቀመዛሙርቱም አባታችን ነገሩ ምንድን ነው ንገረን አሉት። ኅቡዕ አምላክ ሰው ሆነ ወገኖቹ አናምንም ብለው ሰቀሉት ይህ ተአምራት የተደረገ በዚህ ምክንያት ነው አላቸው። ወዲያው በብረት ሰሌዳ ዘመኑን፣ ወሩን፣ ዕለቱን ሰዓቱን ቀርጸው አኖሩት። ይህ በሆነ በ14ኛው ዓመት ጳውሎስ ወደ አቴንስ ሄዶ ስለጌታ አስተማረ። ስለ ስቅለቱም አስተማረ። ይህን ጊዜ ዲዮናስዮስ የጻፈው ዕለት ጳውሎስ ከነገረው ጋር አንድ ሆኖ አገኘው። አምኖ ተጠመቀ። ቅዱስ ጳውሎስም የአርዮስ ፋጎስ ኤጲስ ቆጶስ አድርጎ ሾመው። አርዮስ ፋጎስ አቴና ውስጥ ያለች ቦታ ናት። አርዮስ ፋጎስ ማለት የፍርድ ቦታ፣ የሊቃውንት መሰብሰቢያ፣ የጥበብ ቦታ ማለት ነው።


+√ ወደፈጣሪ እንጸልይ። ይህን ጊዜ ከአምላካውያት መጻሕፍት ምሥጢር ይገለጥልናል።

+√ ፍጥረታትን ሁሉ ካለመኖር ወደ መኖር ያመጡ የፈጠሩ ሥላሴ ናቸው። ፍጥረትን ሁሉ የሚያኖሩና የሚመግቡ የሚያስተዳድሩ ሥላሴ ናቸው።

+√ እግዚአብሔርን የሚያመልኩ የሚያመሰግኑ ምእመናን አማልክት ዘበጸጋ ይባላሉ።

+√ ሥላሴ በገጽ፣ በመልክ፣ በአካል ሦስት ሲሆኑ በመለኮት አንድ ናቸው። እኒህም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ይባላሉ።

+√ የወልድ ከአብ መወለድ የመንፈስ ቅዱስ ከአብ መሥረጽ ይደነቃል እንጂ አይነገርም። (ከሰው አእምሮ በላይ ነው ለማለት ነው። አብ የወልድ ቃልነት የመንፈስ ቅዱስ እስትንፋስነት ሳይለየው ወልድን መንፈስ ቅዱስን አስገኘ ማለት ለሕሊና ረቂቅ ነውና)።

+√ በአባቱ ፈቃድ በመንፈስ ቅዱስም ፈቃድ ወልድ ሰው ሆነ (ሥጋን ተዋሐደ) ከድንግል ማርያምም በድንቅ ምሥጢር ተወለደ። ይህ ሲሆን ከመለኮቱ አልጎደለም።


----ሃይማኖተ አበው ዘአግናጥዮስ---
#ምዕራፍ #፲፩
አግናጥዮስ ለባሴ እግዚአብሔር እየተባለም ይጠራል። ሦስተኛው የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳስ ነው። የቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ ተማሪ ነው። ጌታ ትሕትናን ለሐዋርያት ያስተማረበት ብላቴና ነው።

+√ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ወልድ በድንግል ማኅፀን ተጸነሰ።

+√ አብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ፣ ወልድም በአብ በመንፈስቅዱስ፣ መንፈስ ቅዱስም በአብ በወልድ እንዳለ እናምናለን። አብ ወልድን መንፈስ ቅዱስን አይሆንም። ወልድም መንፈስ ቅዱስን አብን አይሆንም። መንፈስቅዱስም አብን ወልድን አይሆንም።

+√ ለሥላሴ አንዲት አገዛዝ፣ አንዲት ፈቃድ፣ አንዲት ኃይል፣ አንዲት መንግሥት፣ አንዲት ምክር፣ አለቻቸው። በአንድ ምስጋና ይመሰገናሉ።

+√ መለኮት ሦስትነት ከእርሱ የሚገኝ አንድ ብርሃን ነው። አንድም ከሦስትነት የሚገኝ አንድ ብርሃን ነው። በዓለሙ ሁሉ ምሉእ ነው።

+√ ክርስቶስ ሰው እንደመሆኑ በሥጋ እንደታመመ በመለኮቱ እንዳልታመመ እናምናለን።

+√ ሰው ከነፍስና ከሥጋ የተገኘ አንድ እንደሆነ ሁሉ ኢየሱስም ከቃል እና ከሥጋ የተገኘ አንድ አካል አንድ ባሕርይ ነው።

+√ መለኮት ሞት የምትል ከሆነ ሥሉስ ቅዱስ ሞቱ ያሰኛልና አይባልም። (መለኮት በሥጋ ሞተ ግን ይባላል)።

+√ ኢየሱስ ክርስቶስ ነፍስ የለውም በነፍሱ ምትክ መለኮት ነው የሚሉ ከኃድያን ክርስቶስ በወንጌል ነፍሴ ተከዘች ባለው ቃል ይረታሉ።

#ምዕራፍ #፲፪
+√ ኢየሱስ ክርስቶስ ምትሐት እንዳልሆነ ለማጠየቅ በእውነት በላ በእውነት ተሰቀለ በእውነት ታመመ። ምትሐት ግን አይታመምም።

+√ ከተዋሕዶ በኋላ አንዱን ክርስቶስ ሁለት አካል ሁለት ባሕርይ የሚሉ ከሰቀሉት አይሁድ ጋር ይቆጠራሉ።

ክፍል ፮ ይቀጥላል።