Get Mystery Box with random crypto!

   ማየት የተሣነው ሰው መንገዱን በራሱ እርምጃ ሊጓዘው እንደማይችል፤ እንዲሁ የአምላክን ቃልና ፈ | በማለዳ ንቁ ቁጥር ! ፪

   ማየት የተሣነው ሰው መንገዱን በራሱ እርምጃ ሊጓዘው እንደማይችል፤ እንዲሁ የአምላክን ቃልና ፈቃድ ከማየት እምቢ ያልነው እኛም፤ የኑሮ እጃችን መዳፉን ለዲያቢሎስ አሳልፎ በመስጠቱ፤ ሕይወታችን በጊዜ መንገድ ላይ ሲሄድ የሚገኘው ከእግዚአብሔር እየሸሸ ነው፡፡

   "ሰው" ሆኖ የመኖር ልክን በሥጋዊ ሚዛኖች ብቻ ለክቶ የሚሰፍር አመለካከት እንደ ጣዖት ሁለንተናችንን ስለገዛው፤ በኃጢኢት ቀናቶች ተሞልተው ያለፉት ዓመታቶቻችን እግዚአብሔርን ከማየት የተከለከለ ታሪክ በዕድሜያችን ላይ ስለማስቀመጣቸው ገና በደንብ አልተረዳንም፡፡

   እያንዳንዷ በኃጢአት ቆይታ ውስጥ ያለፈችው ደቂቃ የነፍስ ዓይናችንን በበደል ስለት እየደነቆለች መንፈሳዊ እይታችንን በመጉዳቷ፤ ዓለም ላይ በገሐድ ተጨብጦ ከሚታየው ጉዳይ ውጪ ሌላ አተያየት በፍጹም ሊኖረን አልቻለም፡፡ የዲያቢሎስ ሠራዊት ወደ ሰዎች ሕይወት ሲመጣ "ባላጋራ" ይሆን ዘንድ አለውና፤ እነርሱ ከሰማይ (ከእግዚአብሔር ከሆነው) የተለዩበትን ባሕሪይ ለኛ ሰብአዊ ባሕሪይ ከውስጥ በኩል በማጋራት፤ እነርሱ ብቻ ወደሚታያቸው የጥልቁ አድራሻ በዝግታ ይወስዱናል፡፡

   ይህንን ወደ ዘላለማዊ ጽልመት የሚገፋ የመናፍስት ኮሽታ አልባ አካሄድ በራሱ የግንዛቤ ችሎታ በመደገፍ መርምሮ ሊረዳ የማይችለው ሥጋችንም፤ የሕይወትን (ሰማያዊና ምድራዊ) ሙሉ ትርጉም ሲኖር በገበየው የእውቀት ልክ እየጠቀለለ፤ ረቂቁን መንፈሳዊ ጎን ሳያገኘው፥ የመኖር ዘመኑ እስኪያልቅ በአንድ ጎኑ ተንጋድዶ ይኖራል፡፡

   የሥጋው ዓለም ትውልድ ሃይማኖታዊ ሥነ ሕይወትን ከነአካቴው ትቶ የሚገኝበት በተለይ ይሄ ዘመን፤ ኃጢአት ምድርን በመላ የሸፈነ የሰዎች የጋራ ገጽታ እስኪሆን ድረስ በመናፍስት ጥልፍልፍ አሠራር እንደተቀደመ ለማረጋገጥ የዚህ ዘመን ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው፡፡ ስለዚህ ከኃጢአት ኋላ ረድፉን ጠብቆ ብቅ የሚለው ጨለማ ሁላችንን በሚያስብል የቁጥር ብዛት የውስጥ ዕውሮች አድርጎናል፡፡ ከዚህም በላይ አስቸጋሪና የመፍትሔ ውስብስነቱን በእጅጉ የሚጨምረው ጉዳይ ደግሞ፤ መድኃኒታችን "ዕውር ዕውርን ቢመራው ሁለቱም ከጉድጓድ ይወድቃሉ" ሲል ያስጠንቀቀበትን ቃል በውል ሳናጤነው፤ አንዳችን አንዳችንን እየመራን እጅ ለእጅ በመያያዝ በረጅም ሰልፍ ተቀጣጥለን የመጋመዳችን ጉዳይ ነው፡፡ (ወላጅ ልጆቹን፣ ወዳጅ ወዳጆቹን፣ አስኳላ ተማሪዎቹን፣ ከተማ ኗሪዎቹን፣ መንግሥት ዜጎቹን፣ .. የሚመራበት ሕግ፣ መመሪያ፣ ጽንሰ አሳብና ፍልስፍና መንፈሳዊ አዕማዶችንና የነፍስ መሥፈርቶችን መጠበቅ የማይችለው፥ ሥጋዊው አእምሮ የወለዳቸው ዕውር ሥርአቶች ናቸው)

   ማየት የማይችልን ሰው ሊመራ የሚችለው ግለሰብ ዓይናማ መሆን እንዲገባው ምንም አያወላዳም፡፡ ወደ ርዕሳችን ጨዋታ ዓረፍተ ነገሩን ስንቀላቅለው፤ የነፍስ ዕውርነትን ሊፈውስልን የሚችለው ብቸኛው መድኃኒት የእግዚአብሔር ብርሃን ነው እንላለን፡፡ ነፍስን የሚያሳውራት ጨለማ ደግሞ ኃጢአትን ተከትሎ ይመጣል ተባብለናል፡፡ በዚህ መሠረት ስንቀጥል የእግዚአብሔር ብርሃን ብለን የተጠራነው ኃይል ኃጢአትን ከሥሩ ነቅሎ በመገርስስ ጥቁር መጋረጃውን ሊቀድበት ይገባል ማለት ነው፡፡

   ይሄን የውስጥ ዕውርነትን በመዳሰስ የሚፈውስ መለኮታዊ መዳፍ ክርስትናችን ንስሐ ስትል ትጠራዋለች፡፡

   የእግዚአብሔርን ፍጹም ቸርነት ተስፋ አድርገው ንስሐ የሚገቡ ምዕመናን፤ ጌታ ከመንደሩ ለይቶ አውጥቶ የዳበሰውን ዕውር ሰው ይመስላሉ፡፡ ምክንያቱም "ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን" ኢየሱስ ክርስቶስ በምሕረት እጁ ዳስሷቸው፤ አጥርቶ ከማየት የጋረዳቸውን የዓለም፣ የሥጋና የክፉ መንፈስ ጨለማ ይገፍፉታልና፡፡ (የዮሐንስ ወንጌል 1፥9)

   ንስሐ ስንገባ፤ ለዓመፅ ሥራችን ክፍያ ሊሆን ተጠቅራሞ የነበረው የሞት ገንዘብ በመንፈስ ቅዱስ እሳት አመድ እስኪሆን ይቃጠላል፡፡ በዚህ ጊዜ ዙሪያችንን ከብቦ የዘጋው የዲያቢሎስ ጨለማ በእግዚአብሔር የይቅርታ ጸዳል ስለሚሸነፍ፤ ከቅርብም ከሩቅም ሳይቀር ሁሉን መመልከት ይቻለናል፡፡ ዳዊትም የሚመክረን ይሄንኑ ነው፦ "ወደ እርሱ ቅረቡ (ንስሐ ግቡ) [ከዛ] ያበራላችሁማል (ጨለማው ይገለጥላችኋል)፥ ፊታችሁም አያፍርም።" (መዝሙረ ዳዊት 34፥5)

   ስለ ንስሐ የተለያየ ትምህርት የተማሩ አማኞች፤ በቃል ጥሪ የተቀበሉትን የንስሐ ድምፅ ወደ ተግባር ሥጋ መግለጥ ሲቸገሩ ይስተዋላል፡፡ በእርግጠኝነት ክርስቲያኖች በብዛት ካደመጧቸው ስብከቶች መካከል የአንደኝነቱን ደረጃ የሚይይዘው "ንስሐ ግቡ" የሚለው ስብከት ነው፡፡ ሆኖም የትምህርቱ ተደጋጋሚነት ከመለመድ ርቆ የተሻገረ አመርቂ ውጤት አላመጣም፡፡ ስለዚህ ጉዳይ አያሌ አመንክዮቶችን በየዘርፍ በየዘርፉ በመደርደር ጥልቅ ትንታኔ ሊሰጥበት እንዲገባ ቢታወቅም፤ በጽሑፋችን ማዕከላዊ አሳብነት አንድን መሠረታዊና መነሻ ምክንያት ለማስቀመጥ እንሞክር፡፡ ዮሐንስም ይረዳናል፦

"ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፥ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም" (የዮሐንስ ወንጌል 3፥20)

   በመግቢያችን እንዳወጋነው የእግዚአብሔር ብርሃን ወደ መላእክት ባሕሪይ በደረሰ ጊዜ፤ ዓመፀኛው መንፈስና ሠራዊቱ ከክሕደትና ከትምክህታቸው ባለመመለሳቸው በመረጡት ጽልመት ውስጥ ተውጠው ቀርተዋል፡፡ በሌላ አባባል የጨለማ ግብር የሚሰኘው ክፋት፣ ምቀኝነት፣ ሁከትና ጥላቻው ጥሟቸዋል፡፡ ታማኙ መልአክ "በያለንበት ጸንተን እንጠብቅ" ሲል ያስተላለፈውን የብርታት መልእክት እነርሱም ሳይሰሙት አልቀረም፡፡ ልቦናቸው ኃጢአትን ከማጠንጠንና ከማፈለቅ በጭራሽ የሚታጎል አይነት አይደለም፡፡ እንደው ተሳስተው ጽድቅና እውነትን አያስቡም፡፡

    ይሄ የመናፍስቱ ወደ ግራ ዘሞ የመጥመም ባሕሪይ በሰዎች ሕልውና ውስጥ ደባል ሆኖ ሲገባ፤ በሰዎቹ እንደ ሰዎቹ ሆኖ ይገለጣል፡፡ መንፈሱን "ባላጋራ" ብለን እንደጠራነው እንዳትረሳ! ዲያቢሎስ በመጀመሪያ ወደ ሰዎች ራሱን አጋርቶ፤ በመቀጠል እርሱን ወደ ሰዎች እንደሚያጋራ ልብ በል፡፡ ጉዳዩ መንፈሳዊ ነው፡፡ ማለት እርሱ ወደ ሰው፥ ሰው ወደ እርሱ የሚያያዝበት ሰንሰለት ረቂቅ በሆኑት በጠባይ፣ በአሳብ፣ በፍላጎት፣ በስሜት፣ በእውቀት፣ በእንዲህ .. እንዲህ መልኩ የሚገለጽ እንደሆነ ማስተዋል ይኖርብሃል፡፡

   ስለዚህ .. ሰዎች ለንስሐ ከሚሰጡት ሰብአዊ አረዳድ ጀርባ ሰፊ ጥናት ያልተደረገበት የመናፍስት ሽሽት እንደሚኖር ከተጨዋወትናቸው አሳቦች አንጻር መጠቅለል እንችላለን፡፡ ወንጌላዊው እንደተናገረው፤ ንስሐ የኃጢአትን ጨለማ የሚገልጥ የእግዚአብሔር ብርሃን በመሆኑ፤ ጨለማን ጎሬያቸው አድርገው ለክፋት ተልዕኮአቸው የሚያደፍጡት ክፉ መናፍስት መኖሪያቸው በቀላሉ ላለማስፈረስ ወጥረው መታገላቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ ይህንን የመናፍስቱን ድብቅ ትግል ለመረዳት፤ ከራሳችን ጀምሮ በእምነት ታዛ ሥር እንኖራለን የሚሉ ሰዎችን ሁሉ "በኃጢአት ተይዞ እንደመሞት ያለ ከባድ ዕዳ ከፊታችሁ ሳለ፥ ንስሐ ስለምን አትገቡም?" ተብለው ሲጠየቁ በሚሰጡት ምላሽ ተንተርሰን፤ የክፉዎቹን ስልታዊ ሴራና በባሕሪይ ያለ ግፊት ልናስተውለው እንችል ይሆናል፡፡

ወደ ሥጋና ደሙ መጓዛችንን እንቀጥላለን. . .
#ጸባኦት_ይከተላችሁ
@bemaledanek