Get Mystery Box with random crypto!

መልሶ ግንባታዉ እንዴት እየሄደ ነው? ነሐሴ 23 ቀን 2014 ዓ.ም አሸባሪዉ የትግራይ ወራሪ ቡ | በኩር ጋዜጣ Bekur Newspaper

መልሶ ግንባታዉ እንዴት እየሄደ ነው?

ነሐሴ 23 ቀን 2014 ዓ.ም
አሸባሪዉ የትግራይ ወራሪ ቡድን የከፈተውን ጦርነት ተከትሎ በአማራ ክልል በቁሳዊ ውድመት (በዋናነት ማኅበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት) ብቻ ከ292 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን በሺዎች የሚቆጠሩ አጥኝዎች የተሳተፉበት የጥናት ውጤት ያሳያል፤ የማኅበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ውድመት ደግሞ ሚሊዮኖችን ለከፋ አደጋ አጋልጧል። ለመሆኑ የወደሙ እና ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን ተቋማት መልሶ ለመገንባት ምን እየተሠራ ነው? ምንስ ታስቧል? የሚሉና ተያያዥ ጥያቄዎችን አንስተን የሚመለከታቸውን አካላት አነጋግረን ሐሳቡንም እንደሚከተለው ለንባብ አብቅተነዋል::

በአማራ ክልል በጦርነቱ የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት ጽ/ቤት ተቋቁሞ ከሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሥራ ገብቷል፤ ዶክተር አባተ ጌታሁን ደግሞ በአማራ ክልል በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ማቋቋም እና ግንባታ ፈንድ ጽ/ቤት ኃላፊ ናቸው። ዶክተር አባተ ከጥናት ቡድኑ የተገኘውን ውጤት ዋቢ አድርገው እንደተናገሩት በጦርነቱ ከሰብአዊ ጉዳቱ ባሻገር መጠነ ሰፊ ቁሳዊ ውድመት ደርሷል። በጥናቱ እንደተረጋገጠውም ከሰኔ ወር 2013 ዓ.ም እስከ ታህሳስ ወር 2014 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በነበረው ጦርነት በስምንት ዞኖች የሚገኙ 89 የአማራ ክልል ወረዳዎች (945 ቀበሌዎች) ጉዳት ደርሶባቸዋል::

ዶክተር አባተ እንዳብራሩት ጉዳቱን የሚያጠናው (ያጠናው) ቡድን ከአራት ሺህ አምስት መቶ በላይ አባላትን ያካተተ ነው፤ አባላቱም ዩኒቨርሲቲዎችን እና የፌደራል ተወካዮችን ጨምሮ ከተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ ናቸው። ይህ መሆኑም በጦርነቱ የደረሰውን ውድመት በትክክል ለማወቅ ያስቻለ ነው። በተካሄደው ጥናት እንደተረጋገጠውም ከ292 ቢሊዮን ብር በላይ ቁሳዊ ውድመት ደርሷል፤ ይህ የውድመት መጠን በወራሪዉ ቡድን ተይዘው የተለቀቁ ቦታዎችን የጉዳት መጠን ብቻ የሚያሳይ መሆኑን ዶክተር አባተ ተናግረዋል። የተወሰኑ የአማራ ክልል ወረዳዎች አሁንም ድረስ በጠላት ሥር እንዳሉ የሚታወቅ ሲሆን የደረሰው የውድመት መጠንም ከጠላት ነጻ ሲሆኑ በጥናት የሚታወቅ እንደሚሆንም ጠቁመዋል::

ዶክተር አባተ እንዳሉት ጦርነቱ ያደረሰው ውድመት በሦስት ዘርፎች የሚታይ ሲሆን እነዚህም ሰብአዊ፣ ሥነ ልቦናዊ እና ቁሳዊ ውድመት ናቸው። በጥናቱ መሠረትም በቁሳዊ ጉዳት ደረጃ ከ292 ቢሊዮን ብር በላይ ውድመት እንደደረሰ ቢታወቅም ውድመቱ ከዚህ በላይ ሊልቅ እንደሚችል ነው አሁናዊ ተጨማሪ መረጃዎችን በማንሳት ያስታወቁት። የቁሳዊ ጉዳቱ ደግሞ ከሃያ በላይ መሥሪያ ቤቶች ላይ ተከስቷል።

ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ከጥናት ቡድኑ በተጨማሪ የደረሰውን ውድመት እና ስለ ቀጣይ ተግባራት ጉዳት ከደረሰባቸው መሥሪያ ቤቶች ጋር እየሠሩ እንደሆነ ነው የተናገሩት:: በሌላ በኩል በጦርነቱ ሕይወታቸውን ካጡት ባሻገር 12 ሚሊዮን የሚጠጉ የአማራ ክልል ነዋሪዎች ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ ይህም የሥነ ልቦና ጉዳትን ያካትታል። በጥናቱ የተገኘውን የውድመት መጠን የዓለም ሕዝብ እንዲያውቀው ይደረጋል ብለዋል ዶክተር አባተ። ከድረ ገጽ ባሻገርም ለሕትመት በማብቃት በመጽሐፍ ተዘጋጅቶ ተደራሽ እንደሚሆንም ተናግረዋል::

ለመልሶ ግንባታዉ ምን እየተሠራ ነው?
ዶክተር አባተ እንዳብራሩት ጥናቱን መሠረት በማድረግ የደረሰውን ውድመት መልሶ ለመገንባት ወደ ሥራ ተገብቷል፤ ለስኬቱም ገለልተኛ ጽ/ቤት (በአማራ ክልል በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ማቋቋም እና ግንባታ ፈንድ ጽ/ቤት) ተቋቁሞ ከሐምሌ ወር 2014 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሥራ ተገብቷል። በዚህም የአምስት ዓመታት ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ትግበራ ለመግባት በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል::
ዶክተር አባተ እንዳሉትም ተቋማቱ መልሰው የሚገነቧቸውን ከተቋቋመው ጽ/ቤት ጋር በመናበብ የሀብት ብክነት እንዳይኖር ክትትል እና ቁጥጥር ይደረጋል። ከሁሉም ተቋማት ጋርም የጋራ ዕቅድ ተይዟል:: በጦርነቱ መጠነ ሰፊ ጉዳት ካስተናገዱ ተቋማት መካከል የትምህርት እና የጤና ተቋማት በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። ለአብነትም በአማራ ክልል በጦርነቱ ምክንያት ከአርባ በላይ ሆስፒታሎች እና ከአምስት መቶ በላይ ጤና ጣቢያዎች፣ በርካታ ጤና ኬላዎችን ጉዳት እንደደረሰባቸው ከአማራ ክልል ጤና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመላክታል::

በጤና ሚኒስቴር የጤና መሠረተ ልማት ዳይሬክተሩ ኢንጂነር ታደሰ የማነ እንዳሉት በሀገሪቱ ካሉት የጤና ተቋማት የሚበዙት የተሟላ መሠረተ ልማት የላቸውም፤ በጦርነቱ ምክንያት በርካታ የጤና ተቋማት መውደማቸው (መጎዳታቸው) ደግሞ ችግሩን አባብሶታል። በጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማት መልሶ መገንባት እና ደረጃ ማሻሻል የ2015 ዓ.ም ትኩረት መሆኑን ጠቁመዋል::

ኢንጂነር ታደሰ እንዳሉት ከላይ የተዘረዘሩት የአዲሱ በጀት ዓመት ትኩረቶች በሁለት ዙሮች (Phases) ይከናወናሉ፤ በጦርነቱ ከፍተኛ ውድመት የደረሰባቸው አማራ እና አፋር ክልሎች በመጀመሪያው ዙር የመልሶ ግንባታ ሥራ ይከናወንላቸዋል። ለዚህም የጉዳት መጠኑን በማወቅ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን የመለየት ሥራ መከናወኑን ተናግረዋል።

ለተግባሩ ከሁለት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ገልጸው ሦስት መቶ ያህል የጤና ተቋማትን ደረጃቸውን በጠበቀ መንገድ መልሶ ለመገንባት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል። መንግሥት፣ የዓለም ባንክ እና የአፍሪካ ልማት ባንክ ደግሞ ዋና የገንዘብ ምንጮች ናቸው::

በአማራ ክልል ጤና ቢሮ የጤና መሠረተ ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኢንጂነር ዘሩ በለጠ እንደተናገሩት በጦርነቱ ምክንያት ከአርባ በላይ ሆስፒታሎች፣ ከአምስት መቶ በላይ ጤና ጣቢያዎች፣ በርካታ ጤና ኬላዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ የጉዳት መጠኑም በጥናት ቡድኑ መለየቱን እና ለሚመለከተው ክፍል እንዲደርስ መደረጉን ተናግረዋል:: ይህ በእንዲህ እንዳለ ጉዳቱን መሠረት በማድረግ በቢሮዉ አቅም መከናወን የሚችሉትን በመሥራት ጉዳት የደረሰባቸው ብዙ የጤና ተቋማት ወደ ሥራ እንዲመለሱ ተደርገዋል። ከቢሮዉ አቅም በላይ የሆኑትን ደግሞ ለሚመለከተው በማሳወቅ ገንዘብ እየተፈላለገ ይገኛል። በዚህም መልካም ውጤት መገኘቱን ኢንጂነር ዘሩ ተናግረዋል።

ለአብነት ያነሱት ደግሞ በጤና ሚኒስቴር በኩል ቅድሚያ ተሰጥቶ እየተከናወነ ያለውን ተግባር ነው:: በተመሳሳይ ከአራት ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ውድመት እና ጉዳት እንደደረሰባቸው ሰሞኑን በወልድያ ከተማ ከተካሄደው ክልል አቀፍ የትምህርት ውይይት ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።

ከዚህ ውስጥም ከአንድ ሺህ በላዩ ሙሉ በሙሉ የወደሙ ናቸው። ከውድመቱ ጋር ተያይዞ ሁለት ሚሊዮን ያህን ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ መፈናቀላቸው ተነግሯል፤ ችግሩን መሠረት በማድረግ ተቋማቱ (የትምህርት ሚኒስቴርን ጨምሮ) ለመልሶ ግንባታዉ በትኩረት እየሠሩ እንደሚገኙ ተጠቁሟል::

በአማራ ክልል በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ማቋቋም እና ግንባታ ፈንድ ጽ/ቤት ኃላፊ ዶክተር አባተ ጌታሁን እንዳብራሩት መልሶ ግንባታዉ በተቋማት በኩል እየተሠራ ነው፤ ጽ/ቤቱም ከተቋማቱ ጋር በመነጋገር እየሠራ ይገኛል። ሁሉን አካታቹ ዕቅድ እንደተጠናቀቀም (በነሐሴ ወር 2014 ዓ.ም መጨረሻ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል) ሀብት የማፈላለግ ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል።