Get Mystery Box with random crypto!

5 ሰው ተገደለ 18 ቤት ተቃጠለ በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር አምስት ሰዎች ሲገደሉ 18 ቤቶች መ | Ayu Zehabesha-Official (አዩ ዘሀበሻ)

5 ሰው ተገደለ 18 ቤት ተቃጠለ
በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር አምስት ሰዎች ሲገደሉ 18 ቤቶች መቃጠላቸውን ተገልጾአል።

ሟቾቹ አራት ወንዶች እና አንድ ውሃ ስትቀዳ ነበር የተባለች ሕጻን መሆናቸው ተገልጿል።

በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ ወረዳ አጎና በተባለ ‘የቀበሌ ከተማ’ ባለፈው ሰኞ ሚያዚያ 7/2016 በፋኖ እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል የተካሄደ ግጭትን ተከትሎ፤ ነዋሪዎች መገደላቸውን እና በርካታ ቤቶች መቃጠላቸውን የተጎጂ ቤተሰቦች እና የዐይን እማኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጋይንት፣ ሞጃ፣ እስቴ እና ስማዳ ለተባሉ የደቡብ ጎንደር ወረዳዎች ማዕከል ናት በተባለችው አጎና የፋኖ ሀይሎች እና የመንግሥት ኃይሎች “በአጋጣሚ መንገድ ላይ ተገናኝተው” የተኩስ ልውውጥ ማድረጋቸውን ተከትሎ ጥቃቱ መፈጸሙን ነዋሪዎች ገልጸዋል።

ከእስቴ ወረዳ የመጡ ናቸው የተባሉ የፋኖ ታጣቂዎች እና ወደ ጋይንት ወረዳ በመጓዝ ላይ ነበሩ የተባሉ የመንግሥት ኃይሎች መጋጨታቸውን ተከትሎ፤ በንጹሃን ሰዎች እና በቤቶች ላይ ጥቃቱ መፈጸሙን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ሰኞ ሚያዚያ 7/2016 ጠዋት 3 ሰዓት አካባቢ ግድያው እንደተፈጸመ የተናገሩ አንድ የአካባቢው ነዋሪ፤ “በተኩስ ልውውጡ የመንግሥት ኃይሎች ጉዳት ስለደረሰባቸው ጥቃቱን እንደፈጸሙ” ተናግረዋል።

አንድ የአጎና ነዋሪ “በአጋጣሚ የመኪና መንገድ ላይ እና መንደር ላይ ያገኟቸውን ንጹሃን አንድ ሴት እና አራት ወንዶችን ነው የመቷቸው” ሲሉ ስለ ጥቃቱ ተናግረዋል።

“ከረምቡላ ቤት፣ ፑል ቤት ያሉትን እየከፈቱ እዚያ የሚጫወቱትን ነው ጨፍጭፈዋቸው የሄዱት” ያሉ ሌላ ነዋሪ ድግሞ፤ ይህ ሲሆን “የፋኖ ኃይሎች በቦታው አልነበሩም” ብለዋል።

በጥቃቱ የ22 ዓመት ወንድማቸው እንደተገደለባቸው ለቢቢሲ የተናገሩ አንድ የሃይማኖት አባት፤ ታናሽ ወንድማቸው ተደብቆ ከነበረበት ፑል ቤት ከሦስት ጓደኞቹ ጋር መገደሉን ተናግረዋል።

ወንድማቸው ከመሞቱ በፊት “ነፍሱ” ላይ ደርሼ ነበር ያሉት ይኚህ ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉ ነዋሪ፤ ጤና ጣቢያ ማድረስ ባለመቻላቸው ወደ ቤታቸው ወስደው የህክምና እርዳታ ቢደረግለትም ሕይወቱ እንዳለፈ ተናግረዋል።

ሟቾቹ አራት ወንዶች እና አንድ ውሃ ስትቀዳ ነበር የተባለች ሕጻን እንደሆኑም የሃይማኖት አባት የሆኑት ነዋሪ ተናግረዋል።

የሁሉም ሟቾች ቀብር በማግሥቱ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ 6 ሰዓት ላይ ‘አጎና ማሪያም’ ቤተ-ክርስቲያን እንደተፈጸመ የሃይማኖት አባቱ ተናግረዋል።

የሰላማዊ ሠዎቹን ግድያ የመከላከያ ሠራዊት አባላት እንደፈጸሙት የተናገሩት ነዋሪዎች፤ ጥቃት ፈጻሚዎችን በደንብ ልብሳቸው እና በሚያሽከረክሯቸው መኪኖች መለየት እንደቻሉ ገልጸዋል።

ለግድያው ምክንያት ፋኖን ትደግፋላችሁ የሚል እንደሆነ የተናገሩ አንድ ነዋሪ፤ “እናንተ ባትኖሩ ፋኖ አይኖርም ነበር” በሚል ጥቃቱ እንደተፈጸመ ተናግረዋል።

የመንግሥት ኃይሎች ከተማዋን ጥለው ወጥተው [ከጋይንት መስመር] ሲመለሱ ከሰዓት በኋላ ሰንዝረውታል በተባለ ጥቃት፤ 18 ቤቶች መቃጠላቸውንም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።

ቢቢሲ በአካባቢው የተቃጠሉ ናቸው የተባሉ ቤቶችን የሚያሳይ ቪዲዮ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያገኘ ቢሆንም፣ ስለትክክለኛነታቸው ግን ማረጋገጥ አለመቻሉን ገልጿል።

የአካባቢው ማኅበረሰብ ድጋፍ እያደረገላቸው እንደሆነ የተናገሩት ነዋሪዎች፤ ቤቶቹ ‘በጋዝ እና ላይተር’ እንደተቃጠሉ ተናግረዋል።

በስጋት የተሸበበው የአካባቢው ነዋሪ ከዚህ ቀደምም ተመሳሳይ ጥቃት በመድረሱ አካባቢውን ለቆ በተለይም ወደ ገጠር “እየተሰደደ” መሆኑን ነዋሪዎች ገልጸዋል።

የፌደራል መንግሥት ኢመደበኛ ያላቸውን ታጣቂዎች ትጥቅ ለማስፈታት መወሰኑን ተከትሎ በአማራ ክልል የተከሰተው አለመረጋጋት በተለያዩ የክልሉ ክፍሎች ውስጥ ከተስፋፋ አንድ ዓመት ሊሞላው ተቃርቧል።
ቢቢሲ
Join @ayuzehabeshaofficial