Get Mystery Box with random crypto!

አቡነ ጴጥሮስ ከተያዙበት ጊዜ ጀምሮ በጠላት የጥይት እሩምታ እስከተገደሉበት ጊዜ ድረስ የነበረውን | አትሮንስ ዘተዋህዶ-atronss zethewahdo

አቡነ ጴጥሮስ ከተያዙበት ጊዜ ጀምሮ በጠላት የጥይት እሩምታ እስከተገደሉበት ጊዜ ድረስ የነበረውን ሂደት 'ኮርየር ዴላሴራ' (corriere della sera) የተባለው ጋዜጣ ወኪል እና የምሥራቅ አፍሪካ ዜና መዋዕል አዘጋጅ የነበረው 'ፖጃሌ' የተባለ ጋዜጠኛ እ.ኤ.አ. ሰኔ 15 ቀን 1936 ዓም አዲስ አበባ በነበረ ጊዜ ሂደቱን ባየውና በተመለከተው መንገድ እንደሚከተለው ጽሑፍ አቅርቦ ነበር:-

"ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ቁመታቸው ረዘም ፊታቸውም ዘለግ ያለና መልካቸው ጠየም ያለ ዐዋቂነታቸውና ትሕትናቸው ከገጻቸው የሚነበብ ሲሆን በዚህ ጊዜ ለብሰውት የነበረው ልብሰ ጵጵስና ጥቁር ካባ ያውም በጭቃ የተበከለ ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ወደ ችሎት ቀረቡ፡፡ ለፍርድም የተሠየሙት ዳኞች ሦስት ሲሆኑ እነዚህም ጣሊያኖችና የጦር ሹማምንት ናቸው፡፡ የመካከለኛው ዳኛ ኮሎኔል ነበር፡፡ የቀረበባቸውም ወንጀል 'ሕዝብ ቀስቅሰዋል፣ ራስዎም ዐምፀዋል፣ ሌሎችንም አንዲያምፁ አድርገዋል' የሚል ነበር፡፡ ዳኛውም 'ካህናቱም ሆኑ የቤተ ከህነት ባለሥልጣኖች ሊዳኛውም 'ካህናቱም ሆኑ የቤተ ከህነት ባለሥልጣኖች ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ቄርሎስም የኢጣሊያንን መንግሥት ገዢነት አምነው አሜን ብለው ሲቀበሉ አርስዎ ለምን ዐመፁ፣ ለምን ብቻዎን አፈንጋጭ ሆኑ?' ሲል ጠየቃቸው ፡፡
አቡነ ጴጥሮስም የሚከተለውን መልስ መለሱ...

“አቡነ ቄርሎስ ግብፃዊ ናቸው፣ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የሚገዳቸው ነገር የለም፡፡ አኔ ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ሐላፊነትም ያለብኝ የቤተ ከርስቲያን አባት ነኝ፡፡ ስለዚህ ስለ ሀገሬና ስለ ቤተ ከርስቲያኔ አቆረቆራለሁ፡፡ ከዚህ በቀር ለእናንተ ችሎት የማቀርበው ነገር የለኝም፡፡ ለፈጣረዬ ብቻ የምናገረውን አናገራለሁ፡፡ እኔን ለመግደል እንደወሰናችሁ ዐውቃለሁ፡፡ ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ፡፡ ግን ተከታዮቼን አትንኩ” አሉ፡፡
ይህንንም ብለው በጥይት ተደብድበው ሲገደሉ እንዲያይ ተጋብዞ ለተሰበሰበው ሕዝብ የሚከተለውን ሕያው መልእከት አስተላለፉ፡፡

''አረማዊ የሆነው የፋሺስት መንግሥት ቤተክርስቲያንን ለማቃጠል፣ ሕዝበ ክርስቲያንን ለመግደል፣ ሃይማኖትን ለማጥፋት፣ ታሪካችንን ለማበላሸት የመጣ ነው፡ እንጂ በጎ ለመሥራት፣ እውነተኛ ፍርድ ለመስጠት ስላልመጣ ለዚህ ለግፈኛ አትገዙ፡፡ ስለ ውድ ሀገራችሁ፣ ስለ ቀናች ሃይማኖታችሁ ተከላከሉ።ነጸነታችሁን ከሚረክስ ሙታቹህ ስማችሁ ሲቀደስ ታላቅ ዋጋ ያለው ክብር ታገኛላችሁ። የኢትዮጵያ ህዝብ ለዚህ ለጠላት እንዳይገዛ አውግዣለሁ፤ የኢትዮጵያ መሬት ጠላትን ብትቀበል የተረገመች ትሁን። በፈጣሪየ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተገዘተች ትሁን።''
ጋዜጠኛው ይቀጥላል

“እኒህ ጳጳስ ሐቀኛ ነበሩ። ነገር ግን ለኢጣሊያ ለጋስዮን ታዝዞ የመጣው አስተርጓሚ ዳኞች የሚሉትን ብቻ ከማስተርጎም በቀር ጳጳሱ የሚናገሩትን ሃቀኛ ንግግር አላስተረጎመም፡፡ እኔ እንኳን የሰማሁት በአዲስ አበበ ለሠላሳ ዓመት የኖረው የእቴጌ ሆቴል ኃላፊ የነበረው የግሪክ ዜጋ ማንድራኮስ አጠገቢ ተቀምጦ ስለ ነበር የተናገሩትን ሁሉ ስለ ገለጠልኝ ነው፡፡ እኔ እንደ ሰማሁት ፍርዱን ለመስማት በብዛት የተስበስቡት ጣሊያኖችና ታዝዞ የወጣው የአዲስ አበበ ሕዝብ ሐቀኛ የሆነውን ንግግራቸውን ቢሰማ ኖሮ ልባቸው ይነካ ነበር"። ሞት የተፈረደባቸው ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በችሎት ፊት ለብዙ ሰዓታት ቆመው ስለዋሉና ደክሟቸው ስለነበር ለመቀመጥ ፈልገው ዳኛውን በትሕትናና በፈገግታ ጠየቁት። እንዲቀመጡም ፈቀደላቸው፣በመጨረሻም የሞታቸው ፍርድ ከተነበበ በኋላ የፈረዱባቸውን ዳኞች ጸልየው በመስቀላቸው ባረኳቸው።ብፁዕነታቸው እስከ መቃብር አፋፍ ድረስ የፍርሃትና የድንጋጤ ምልክት ያይደለ ከልብ ፍጹም ቆራጥነት ይታይባቸው ነበር።”
ምንጭ፡ ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያውያን