Get Mystery Box with random crypto!

ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ቀዳማዊ በ1875ዓ.ም በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሰላሌ አውራጃ ፍቼ ከተማ ተወ | አትሮንስ ዘተዋህዶ-atronss zethewahdo

ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ቀዳማዊ በ1875ዓ.ም በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሰላሌ አውራጃ ፍቼ ከተማ ተወለዱ።ብፁዕነታቸው ጴጥሮስ የሚለውን ስመ ጵጵስና ከማግኘታቸው በፊት መምህር ኃይለማርያም ይባሉ ነበር።ወላጆቻቸውም በትምህርት እንዲያድጉ ልዩ ፍላጎት ስለነበራቸው ወደ ደብረ ሊባኖስ ወስደው ባህታዊ ተድላ ለተባሉ አባት ሰጧቸው።ከንባብ እስከ ቅኔ ያሉትን ትምህርቶች በዚያው አጠናቀቁ።የቅኔ ትምህርታቸውን ለማስፋፋት ወደ ዋሸራ ተሻገሩ፣በዚያም በመምህርነት ተመረቁ።የዜማውንም ትምህርት በሚገባ ለመማር ወደ ጎንደር ተጓዙ። እሱንም እንዳጠናቀቁ ወደ ወሎ ቦሩ ሜዳ በመሄድ ደግሞ ከመምህር አካለወልድ የመጽሐፍት ትርጓሜ ትምህርቶች ብሉያትን፣ ሐዲሳትን እና ሊቃውንትን በብቃት አጠናቀቁ።

በ1900 ዓ.ም በምስካበ ቅዱሳን በመሄድ ወንበር ዘረጉ።በዚያም ለዘጠኝ ዓመታት ያህል ቅኔና መጥሐፍትን አስተማሩ።በ1909ዓ.ም ወደ ደብረሊባኖስ ገዳም በመሔድ ምንኩስናን ተቀበሉ።ሥርዓተ ምንኩስናን ከተቀበሉ በኋላ በምሁር ኢየሱስ ገዳም፣በዝዋይ ደብረጽዮን ቅድስት ማርያም ገዳም በመምህርነት አገልግለዋል። በ1919 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ አበ ንስሐ ሆኑ።

ከአንድ ሺሕ ስድስት መቶ ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የራሷን ጳጳሳት ለመሾም ስትነሳ ከተመረጡት አምስት አባቶች መካከል አንዱ አቡነ ጴጥሮስ ነበሩ።በዚህም መሠረት ከሌሎች አባቶች ጋር ግንቦት 18 ቀን 1921 ዓ.ም በእስክንድርያው መንበረ ማርቆስ ቤተክርስቲያን መዓርገ ጵጵስና ተቀበሉ።ወደ አገራቸው ከተመለሱ በኋላም “አቡነ ጴጥሮስ ጳጳስ ዘምሥራቅ ኢትዮጵያ” ተብለው በያኔው መንዝና ወሎ ሀገረ ስብከት ተሾሙ።

1928 ፋሽስት ወደኢትዮጵያ በመጣ ጊዜ በመጀመሪያ ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር አርበኞቹ ለማበረታታት ተጓዙ። ከዚያም ከተመለሱ በኋላ ወደ ወደ ደብረሊባኖስ በመሄድ የመጣውን ችግር ያሥታግስ ዘንድ እየጸለዩ ለሀገርና ለነጻነት መሞትም ቅዱስ ተግባር መሆኑን በመስበክ ያተጓቸው ነበር።ይሁን እንጂ በሦስት በኩል እየተመራ የመጣው ጦር እል ባለማጥቃቱ ወደየመጣበት ሲመለስ ብፁዕነታቸው ግን “ብችል ጠላት በኢትዮጵያውን ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍ በቅርብ ርቀት የሚመለከተውን ሕዝብ በማትጋት በጠላት ላይ እንዲነሳ አደርገዋለሁ ካልሆነ እዚሁ እሞታለሁ” ብለው ከአርበኞች ተነጥለው በአዲስ አበባ ቀሩ። ጠላት በከተማዋ ባሰማራቸው ባንዳዎች ምክንያት እንደልባቸው መንቀሳቀስም አልቻሉም ነበርና እዚሁ ከተማ ተሰውሬ መኖር አልፈልግም ብለው ሐምሌ 22ቀን 1928 ዓ.ም በወቅቱ የኢጣሊያ እንደራሴ ለነበሩት ለራስ ኃይሉ እጃቸውን ሰጡ።ራስ ኃይሉም ወዲያው ለግራዚያኒ አሳልፈው ሰጧቸው።

ደራሲና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ "አቡነ ጴጥሮስ እንዴት ሞቱ" ሲል ሙሴ ፓይላክን ጠይቆአቸው እርስቸውም የሚክተለውን ተናግረዋል።
"አቡነ ጴጥሮስ የተገደሉ ዕለት እዚያው ነበርኩ። መጀመሪያ በእጃቸው ይዘውት የነበረውን መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ተሳለሙት። ቀጥለውም በያዙት መስቀል አማትበው ሕዝ ቡን ባረኩ፡፡ የኪሳቸውንም ሰዓት አውጥተው ካዩ በኋላ መልሰው ከኪሳቸው ክተቱት። ወዲያው ወታደሮች በሩምታ ተኩስው ገደሉ ዋቸው። ይህ እንደሆነ አስገድዶ ኮሎኔል ተመልካቹን ሕዝብ አጨብጭቡ ብሎ አዘዘና ተጨበጨበ።

ማታ ከአስገዳዩ ኮለኔል ጋር ተገናኝተን ስንጫወት 'በዚህ ቄስ መገደል አኮ ሕዝቡ ተደሰቷል' እለኝ እንዴት?' ብለው 'አላየህም ሲያጨበጭብ' አለኝ። እኔም 'ባታውቀው ነው እንጂ የሕዝቡ ባሕል ሲናደድም ያጤበጭባል' አልኩት። 'እንዴት?' ቢለኝ እጄን እያጨበጨብኩ አሳየሁት። እሱም አሳየኝ። ከዚህ በኋላ " የሆነው ቢሆን እኔ ትልቅ ማስታወሻ አግኝቼአለሁ" ብሎ አቡነ ጴጥሮስ ሲገደሉ ይዘውት የነበረውን መስቀልና መጽሐፍ ቅዱስ የኪስ ስዓታቸውን ጭምር አሳየኝ። መጽሐፍ ቅዱሱ መሐል ለመሐል በጥይት ተስንጥቋል።”ብለው ያዩትን መስክረዋል።

ጠላት ድል ተደርጎ ሀገራችን ነጻነቷን ከተቀዳጀች በኋላ የብፁዕነታቸውን አኩሪ ተግባር ትውልድ ሲያዘክርላቸው እንዲኖር መታሰቢያ ይሆናቸው ዘንድ በግርማዊ ቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት አሳሳቢነት ሐምሌ16 ቀን 1938 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ሐውልት ቆሞላቸዋል።
የሐቀኛው አባታችን በረከት ይደርብን!
ምንጭ:- ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያውያን፣