Get Mystery Box with random crypto!

አሮራ (ግማሽ ልቤን እና ግማሽ ነፍሴን ያመኛል) ምዕራፍ _6 መንግስቱ አሁን የተሰጠው ክፍል አይደ | አትሮኖስ

አሮራ
(ግማሽ ልቤን እና ግማሽ ነፍሴን ያመኛል)
ምዕራፍ _6
መንግስቱ አሁን የተሰጠው ክፍል አይደለም ሶስት አመት ከቆየበት የታፈገ የእስር ቤት ክፍል ይቅርና ቀድሞም በሰላሙ ጊዜ የራሱ የሆነ የተከበረ ስራ እያለው ከሚኖርበት ክፍል በጣም የተሻለና በውበትም በምቾትም የደመቀ ነው፡፡የአልጋው ጥራት፤ጠረጳዛው፤ ወንበሮቹ…ቁምሳጥኑ አንድ ዘመናዊ ወንደላጤ ቢኖሩት የሚመኛቸው ነገሮች ሁሉ የተሞሉለት ነው፡፡ከተቀመጠበት ተነሳና ወደ ሻወር ቤት አመራ፡፡ከፍቶ ገባ …ልዩ ነው፡፡ልብሱን አወላለቀና ወደመሀከል ተጠግቶ ውሀውን ከላይ ለቀቀው…..እስር ቤት ሻወር እንዴት እንደሚወስዱ ትዝ አለው…..መአት ወንዶች አንድ ላይ ይጠቀጠቁና ውሀው ከላይ ይለቀቃል… የአንዱ ጭቅቅት ተፈናጥሮ አንዱ ሰውነት ላይ እየተረጨ..አንዱ የሌላውን እርቃን ገላ እየጎበኛ ምቾት በሚነሳ መንገድ ይታጠባሉ፡፡
ያንንን እያሰበ ታጠበና  ፎጣ አገልድሞ ወደመኝታ ቤቱ ተመለሰ ፡፡ሰውነቱን አደራረቀና ልብስ ለመቀየር አሮጌ ሻንጣውን ከፈተ፡፡የተሻለ ያለውን ልብስ በመምረጥ ላይ ሳለ አጎቱ ቁም ሳጥኑ ውስጥ ልብስ አለልህ ያለው ትዝ አለው፡፡ሻንጣውን ባለበት ተወና እራቁቱን ወደ  ቁም ሳጥኑ አመራ፡ደረሰና ከፈተው፡፡መለስተኛ ቡቲክ ሊያስከፍት የሚችል ብዛትና ጥራት ያላቸው ልብሶች ተጠቅጥቀውበታል፡፡ሶስት የተለያየ ቀለም ያላቸው  ሙሉ ሱፎች ፤ከአምስት የሚበልጡ ጅንስ ሱሪዎች ሌሎች ሁለት ካኪ ሱሬዎች፤ ሸሚዞች፤ ፓክአውቶች ፤ፓንቶች እና ካልሲዎች ሳይቀሩ ተገዝተውለታል፡፡ቁም ሳጥኑ ጎን ያለው ወንበር ላይ ቁጭ አለ፡፡
‹‹ይሄ ሰውዬ ከእኔ ምንድነው የሚፈልገው…?››ሲል ጠየቀ፡፡አጎቱ ለእሱ ከፍተኛ እቅድ እንዳለው እርግጠኛ ነው፡፡ከለበለዚያ እንዲህ ድንገት ከተደበቀበትና ከተሸሸገበት ብቅ ብሎ ተወዳጅ አባት፤ ተናፋቂ ታላቅ ወንድም አይነት ገፀ ባህሪ ተላብሶ አይጫወትም ነበር…ዝም ብሎ አንድ ጅንስ ሱሪ አንድ ሸሚዝና አንድ ቀለል አያለ ጃኬት መረጠና ወደአልጋው ተመለሰ…፡፡ሁሉንም በየተራ ለበሰ፡፡ ወደሻወር ቤት ተመለሰና እራሱን በመስታወት ተመለከተ፡፡ የተወሰነ ቅባት እጅ ላይ አደረጋና ፀጉሩን እና ፊቱን  አባበሰ፡፡
‹‹አሁን እስኪ ወደ አዲሶቹ ተናፋቂ ዘመዶቼ ልሂድ ››አለና ወደውጭ መራመድ እንደጀመረ አጎቱ ለልጆቹ ምትሰጠው ስጦታ ነው ብሎ ጠረጴዛው ላይ ያስቀመጠለትን የስጦታ እቃ ትዝ አለው..ወደኃላ ተመለሰና አነሳቸው፡፡
‹‹አጎቴ አንተ እኔ ላይ ቆንጆ እቅድ ሊኖርህ እንደሚችል ጠንካራ ጥርጣሬ አለኝ..ግን እንዳትሸወድ እኔም በቅርብ ቀን አስበህ እራሱ የማታውቀውን እቅድ አወጣልሀለሁ፡፡ከአመታት በፊት ከአባቴ የወሰድከውን ሀብት ፤ ሰላም እና ጤና በጠቅላላ ከነወለዱ እረከብሀለው፡፡››ይሄንን በውስጡ እያሰላሰለ ሳሎን ሲደርስ የሳሎኑ ጠረጴዛ በምግብ ተሞልቶ ዙሪያውን በሰዎች ተከቦ  የእሱን መምጣት በናፍቆት ሲጠብቁ ደረሰ፡፡ከዛ ድግሱም ሆነ የአቀባበል ዝግጅቱ እስከምሽት የዘለቀና የተለየ ነበር፡፡
/////
በማግስቱ ጥዋት ከቁርስ በኃላ አጎቱ ይዞት ወጣ ፤ለሰላሳ ደቂቃ ዝምታ ያጠላበት ጉዞ ከተጓዙ በኃላ አንድ ግዙፍ ባለሶስት ወለል ገስትሀውስ ግቢ ውስጥ ይዞት ገባ፡፡መኪናዋን አቆሙና ግራውንድ ላይ ወዳለ አንድ ክፍል ይዞት ገባ….ለገስት ሀውሱ እንደቢሮ ሚያገለግል መሆኑን ክፍሉ ውስጥ ያሉትን እቃዎችን አይቶ መረዳት ይቻላል፡፡አጎትዬው የለበሰውን ጃኬት አወለቀና ማንጠልጠያው ላይ ሰቅሎ ጠረጴዛውን ዞሮ ግዙፉ ተሸከርካሪ ወንበር ላይ እየተቀመጠ እሱን ፊት ለፊት ያለ ወንበር ላይ እዲቀመጥ አዘዘው፡፡
‹‹እንግዲህ ይሄ የእኛ ገስት ሀውስ ነው፡፡በኃላ ልጀቹ ሁሉንም ክፍልም ሆነ  አጠቃላይ ግቢውን ያስጎበኙሀል....

ይቀጥላል......
    ሀሳብ አስተያየታችሁን 
@Tsiyon_awit አድርሱኝ
   ቻናላችንን ይቀላቀሉ
@itsmetsiyearsemalj
@itsmetsiyearsemalj