Get Mystery Box with random crypto!

'ልጅ ያላትን ሴት ማን ሊፈልጋት ይችላል እና በዚህ ምክንያት እሱን ላጣው ነው' እንባዬ ከየት መጣ | አትሮኖስ

"ልጅ ያላትን ሴት ማን ሊፈልጋት ይችላል እና በዚህ ምክንያት እሱን ላጣው ነው" እንባዬ ከየት መጣ ሳልለው ዱብ ዱብ አለ።

"እና የእውነትም ልጅ አለሽ ማለት ነው"

"አዎ አለችኝ"

"የት?.... እንዴት?... ማለቴ..." አይን አይኔን እያየ ቀበጣጠረ

ከውስጤ አንዳች ነገር ፈንቅሎ የወጣ እስከሚመስለኝ በሀይል ተናገርኩ"ዝርዝሩን አይደለም ላንተ ለራሴም ደግሜ አልነግረውም እና ለዮናታንም ቢሆን ንገረው በጣም የምወዳት ልጅ አለችኝ ግን ስለ ልጄ የት? እንዴት? ከማን ወለድሻት? የሚል ጥያቄ የሚጠይቀኝ ከሆነ አጠገቤ እንዳይደርስ ንገረው.... አንተም ብትሆን እንደዛው" በተቀመጠበት ትቼው እያለቀስኩ ወደ ዶርም ሄድኩ። በር ላይ ስደርስ የዶርም አጋሮቼ እንዳያውቁ እንባዬን ጠራርጌ ገባሁ። የለበስኩትን ቱታ በቀሚስ ቀይሬ ነጠላዬን አንስቼ ወደ ቤተክርስቲያን ሄድኩ። ገና የውጨኛው በር ላይ እንደደረስኩ እንባዬን ዘረገፍኩት

"ለምን አምላኬ...? ያለፈው ህመሜን ለምን እንድረሳው አታደርገኝም? ለምን ዛሬ እንደሆነ ሁሉ እንደፊልም አየዋለሁ? ዛሬም ከእንቅልፌ በርግጌ መነሳት ዛሬም ስለልጄ ሲጠይቁኝ ደስተኛ ሆኜ ስለሷ ከማውራት ይልቅ እሷ የተፈጠረችበትን አጋጣሚ መርገም..... አምላኬ እኔ ከአቅሜ በላይ ሆነብኝ... እንዴት ባደርግ ነው ትላንትናን ረስቼ ዛሬን መኖር የምችለው...." ረጅም ሰዓት በእንባ እና በእልህ ነገርኩት።

ብዙ አመታቶች ቢቆጠሩም ደስተኛ ቤተሰብ ቢኖረኝም ህልሜ የነበረውን ህክምና እየተማርኩ ቢሆንም የህይወቴ ግማሽ ስኬት ትላንቴን ሊያስረሳኝ አልቻለም። ልክ ዛሬ እንደሆነ ሁሉ ያስፈራኛል.... እንዴት ወንድ የተባለ ፍጡር ላፈቅር እንደቻልኩ ለኔ ጥያቄ ነው። ቢያንስ ግን ውስጤ ያለውን የትዝታ አውሬ እስካልቀሰቀሱብኝ ለሰዎች ሰላማዊና የተረጋጋሁ ሰው ነኝ።

ክላስ ረፍዶብኝ በፍጥነት እየተራመድኩ
"እንኳን ደስ አለሽ ህያብ በዛብህ.... እንኳን ደስ አለሽ" እርምጃዬን ገትቼ ወደኋላ ዞርኩ.... የትናዬት

"እባክሽ ክላስ ረፍዶብኛል" ፊቴን አዙሬ ልሄድ ስል

"ዮናታን ወደ አዲስ አበባ እንደተዘዋወረ ሰማሽ"አለችኝ። ክው ብዬ ቀረሁ

"ምን እያልሽ ነው" ይሄን ሁሉ ቀን ሊያገኘኝም ሆነ ሊያወራኝ ያልፈለገው ልጅ አላት ስለተባለ እንደሆነ ቢገባኝም እሱ የኔ እንደማይሆን ባስብም ከአይኔ እንዲርቅ ግን አልፈልግም

"ህያብ ዮኒ እንደሚወድሽ ከኔ በላይ ማንም ሊያውቅ አይችልም። የኔ ይሆናል ብዬ ባንቺም ላይ በሌሎችም ላይ ብዙ ተንኮል ሰርቻለሁ... " ከአይኗ እንባ ኮለል ብሎ ወረደ

"ይቅርታ አድርጊልኝ ህያብ ከልቤ ነው ብዙ ነገር አድርጌሻለሁ። አንቺ እንኳን ለይተሽ ያላወቅሽውን ብዙ ነገር.... መምህር ውጤትሽን እንዲያበላሽ አልጋው ላይ ወድቂያለሁ... የዶርምሽን ልጆች ገንዘብ እየከፈልኩ እዚህ መሆንሽን እንድትጠይ አድርጊያለሁ... ይሄን ይሄን ብልሽ ጊዜ አይበቃኝም። እኔን ይቅር ባትይኝም ችግር የለውም ስለሚገባኝ ነው። እነሱን ግን ይቅር በያቸው ሁሉንም በደካማ ጎናቸው ይዣቸው ነው" ወደ ጎን ስታይ ከሷ እኩል ዞር ብዬ አየሁ ሁሉም ተደርድረው ቆመው ያዩኛል... አንደኛዋ መጥታ እግሬ ላይ ወደቀች ሌሎቹም ተከተሏት እነሱን አንስቼ ዞር ስል የትናዬት የለችም።

ኦ የትናዬት አልኩ ለራሴ አንደኛ አመት ላይ ሰርቻለሁ ያልኩት ኮርስ ውጤት ተበላሽቶብኝ ያየሁት መከራ ትዝ አለኝ።

ዶርሜ ውስጥስ ቢሆን አንዳቸው እንኳን ጓደኛ ሊያደርጉኝ ፈቃደኛ አልነበሩም በማደርገው በእያንዳንዱ ነገር ይሳለቁብኝ ነበር። ትንሽ ህይወት የምትባለው ትሻላለች። ትዝታ፣ ቤዛዊት እና ዝናሽ የነሱ ይለይ ነበር። እንደ ድንገት ተስቶኝ ከሎከር ውጪ እቃ ካስቀመጥኩ ወይም ሳልቆልፍ ከረሳሁ ወይ የሆነ ነገር ይጠፋል ወይም ደግሞ ቅባትና ሎሺኔ ግማሽ ደርሶ ነው የማገኘው... ኧረ ብዙ ብዙ ለመተኛት ካልሆነ ወደ ዶርም አልሄድም ነበር። የነሱ ይህን ያክል እኔን መግፋት ቢኒ ላይ እንድጣበቅ አደረገኝ። ቢኒ ለኔ ሁሉ ነገሬ ነው ጓደኛዬ ወንድሜ አማካሪዬ አስጠኝዬ... ቃል ከሚገልፀው በላይ እወደዋለሁ። ለሴት ጓደኛ እንኳን ለመንገር የሚከብዱ ነገሮችን ነግረዋለሁ አማክረዋለሁ። ከ1 ነገር በስተቀር ስለኔ ሁሉንም ያውቃል ከ1 ውሸት በስተቀር ምንም ዋሽቼው አላውቅም እሱም የትውልድ ሀገሬ አዲስ አበባ እንደሆነ ነው የነገርኩት ሁሉም ቢሆን የሚያውቁት ይህን ነው። በአጠቃላይ ቢኒ የማላውቀውን የወንድም ፍቅር ያወኩበት ልጅ ነው። ይሄን ሰሞን እሱም ጥፍት ብሏል ምናልባት ተቀይሞኝ ይሆናል ቢሆንም አልፈርድበትም ካለን ቅርበት አንፃር እንዴት አልነገረችኝም ሊል ይችላል።

"ይቅርታ ህያብ ከራሴ ጋር ትንሽ ግጭት ውስጥ ነበርኩ ለዛ ነው ካንቺም ከክላስም የጠፋሁት" የእውነት አናዶኝ ነበር

"አንተ ሰው ያስባል ይጨነቃል እንኳን አትልም ግቢውን ለቀህ የት ሄደህ ነው" ትንሽ ካቅማማ በኋላ

"ቤተሰብ ጋ" አለኝ

"የት ድሬዳዋ.... እዛ ነበርክ"

"አዎ"

"ምነው ቤት ሰላም አይደሉም እንዴ"

"አይ ሰላም ናቸው። አሁን ለጠፋሁበት ራት በመጋበዝ እቀጣለሁ" ፈገግ እያለ እጁን ዘረጋልኝ

"ቅጣቱንማ የምወስነው እኔ ነኝ" ተንደርድሬ እቅፉ ውስጥ ገባሁ "የምር ናፍቀኸኝ ነበር ቢኒ ወንድሜ"

"እኔም ናፍቀሽኝ ነበር...
ተማሪማ ከዚህ የበለጠ ሊቀጣ አይችልም ሀሀሀሀ"

ቶሎ ቶሎ ለባብሼ ከዶርም ልወጣ ስል
"እንዲህ አምሮብሽ ወዴት ነው" አለችኝ ቤዛ። ዝም ብያት ልሄድ አልኩና እንደታረቅን ትዝ ሲለኝ "እራት ቀጠሮ አለብኝ ከተባልኩት ሰዓት አርፍጃለሁ" ፊቴን አዙሬ ልወጣ ስል

"ቆይ ቆይ እና እራት ተጋብዘሽ ነው እንደዚህ የለበሽው ነይ ሂዊ እኛ እናልብሳት" ወደኔ መጣችና ቦርሳዬን ተቀብላ ካስቀመጠችው በኋላ ልብስ እያነሰች ማማረጥ ጀመረች "ኧረ ቤዚ ረፍዶብኛል ደግሞኮ ፍቅረኛዬን ላገኝ አልሄድ ቢኒ እኮ ነው" ችኩል ብያለሁ ምክንያቱም ቢኒ ሲያስጠብቁት አይወድም

"ቢሆንም ፏ ዝንጥ ብለሽ ነው መሄድ ያለብሽ" በጥቂት ደቂቃ ውስጥ ሌላ ሰው አስመሰሉኝ ራሴን በመስታወት ውስጥ ሳየው አምሮብኛል።

"አሁን መሄድ ትችያለሽ ሰላም ተመለሽ" ህይወት ጉንጬን ሳም አደረገችኝና በር ከፍታ አስወጣችኝ። ለኔ አዲስ ሰዎች ነው የሆኑብኝ ግን ከልባቸው እንደሆነ በደንብ ያስታውቃል።

"ይቅርታ ቢኒ ከወጣሁ በኋላ እኮ እነ ህይወት እንደዚ ለብሰሽ አትሄጂም ብለውኝ"

"ችግር የለውም ውዷ ብዙም አላስጠበቅሽኝም" ተያይዘን ከግቢ ወጣን በየጥጋጥጉ እንዲሁም በደንበኞች ጠረጴዛ ላይ የተቀመጡት የሻማ መብራቶች ለሆቴሉ ልዩ ውበት አጎናፅፈውታል። በአድናቆት ዙሪያ ገባውን እያየሁ አንድ አስተናጋጅ ወደኛ መጣና ለየት ብሎ ወደተዘጋጀ ጠረጴዛ እየመራ ወሰደን.... ከተቀመጥን በኋላ

"አንተ ምንድነው ነገሩን ሁሉ ሮማንስ አደረከው እኮ የምር ግራ እያጋባህኝ ነው ትልቅ ሆቴል መግባታችን ሲያስገርመኝ ጭራሽ.." የማወራውን ነገር ችላ ብሎ

"እባክህን ሜኑ አምጣልን" ግራ ገብቶኝ ዝም ብዬ አያየሁት ሜኑ እጄ ላይ አረፈ ተቀብዬ ስገልጠው የምታምር ትንሽዬ ቀይ አበባ ውስጡ ቁጭ ብላለች። ቀና ብዬ አስተናጋጁን አየሁት ቅልቅ ድንጋጤ.... አበባዋን አንስቶ አጠገቤ ብርክክ አለ

"ህያብ ያለፈ ታሪክሽ ምንም ይሁን ምን አንቺን ከማፍቀር ሊያቆመኝ አይችልም። የኔ ቆንጆ የፍቅር ጓደኛዬ ትሆኛለሽ?"

"ዮኒ.." ተርበተበትኩ... ቢኒን ዞር ብዬ ሳየው ፈገግ ብሎ እያዬን ነው.....

ይቀጥላል