Get Mystery Box with random crypto!

#ህያብ ፡ ፡ #ክፍል_ሁለት ፡ ፡ #ድርሰት_ኤርሚ 'አቤት ህያብ' አለኝ ዶክተሩ ካቀረቀረበት | አትሮኖስ

#ህያብ


#ክፍል_ሁለት


#ድርሰት_ኤርሚ

"አቤት ህያብ" አለኝ ዶክተሩ ካቀረቀረበት ቀና ብሎ ካየኝ በኋላ

'ማስወረድ እፈልጋለሁ' አልኩት

"ምን" የሚል ድምፅ ሰምቼ ስዞር እናቴ ከኋላዬ ቆማለች።

"ምንድነው የምታወሪው እ... ማን ፈቅዶልሽ ነው የምታስወርጂው.... ምን ስልጣንስ ኖሮሽ ነው የእግዜርን ፍጡር የምትገይው......" ወደኔ የበለጠ እየተጠጋች የቁጣ ናዳ አወረደችብኝ። እናቴ በአካባቢው እያለች ከአንደበቴ ይህንን ቃል ማውጣት አልነበረብኝም።
.......
ከውርጃ ጋር ተያይዞ በጣም መጥፎ ትዝታ አለባት። ልጅ እያለሁ ትርሲት የምትባል የዘመዳችን ልጅ አብራን ትኖር ነበር። ታናሽም ታላቅም ስለሌለኝ እንደ እህቴ ነበር የማያት እሷም ሲበዛ ታቀብጠኝ ነበር። በትምህርቷ በጣም ጎበዝ ነበረች። ታዲያ ከጊዜ በኋላ ውጤቷ እያሽቆለቆለ መጣ። መምህሮቿ ቤታችን ድረስ መጥተው እናቴን አናገሯት እማዬ ደነገጠች..... ትርሱ ከሄደችበት ስትመለስ ቁጭ አድርጋ አወራቻት መከረቻት ግን ለውጥ አልነበረውም የባሰ ትምህርት ቤት እያለች ሌላ ቦታ እንደምትውል ተደረሰባት.... እናቴ ይህን ስትሰማ በጣም ተቆጣቻት።
......
የሆነኛው ቀን ላይ መልዕክተኛ መጥቶ ትርሲት ታማ ሆስፒታል መግባቷን ነገሩን እናቴ እየሮጠች ሄደች። ወደቤት ይዛ የተመለሰችው ግን አስከሬን ነበር።
.......
ትንሽ ካደኩ በኋላ እናቴን ጠይቄ እንደተረዳሁት ከሆነ ትርሲት ከአንድ የከተማችን ነጋዴ ጋር የፍቅር ግንኙነት ትጀምራለች። ሁሉ ነገሯን ትታ ነበር ክንፍ ያለችለት .... ግንኙነታቸው በሱ ጎትጓችነት ወደ አልጋ ላይ ጨዋታ ይሸጋገራል.... በዚህ መሀልም ትርሲት አረገዘች። ማርገዟን ስታውቅ ሁሉንም ነገር ዘርዝራ ለጓደኛዋ ከነገረቻት በኋላ ምክሯን ጠየቀቻት
"ስለሚወድሽ ያገባሻል እንዳረገዝሽለት ንገሪው" አለቻት።

በማግስቱ ወደ ፊት የሚኖራቸውን የደስታ ህይወት እያሰበች በፈገግታ የደመቀ ፊቷን ይዛ ወደ ነጋዴው ፍቅረኛዋ ጋ ሄደች። እንዳረገዘችለት ስትነግረው

" ከማናባሽ አርግዘሽ መጥተሽ ነው አረገዝኩልህ የምትይው" አላት።
ከሱ ውጪ ወንድ እንደማታውቅ ያውቃል ግን ሊሰማት አልፈለገም። ትርሲት ለሱ የሆነ ሰዓት ላይ ተጠቅሞባት እንደሚጥላት እቃ ነበረች።
አይንሽን ማዬት አልፈልግም ከነ ዲቃላሽ ገደል ግቢ ብሎ አባረራት..... ለሳምንታት ተስፋ ሳይቆርጡ እሷም ጓደኛዋም ለመኑት.... ጭራሽ አይኑን ወደ ጓደኛዋ ማዞር ጀመረ ነገሩ ሲገባቸው እሱን እርግፍ አድርገው ትተው ሌላ መፍትሄ መፈለግ ጀመሩ እናም ማስወረድ በሚለው ተስማሙ። የትርሲት ጓደኛ ቤተሰቦቿ ወደገጠሩ ስለሚርቁ ቤት ተከራይተውላት ነው ትምህርቷን የምትማረው.... እናም ለእቅዳቸው ተስማሚ የሷ ቤት ስለሆነ ትርሲት እማዬን ለፈተና ለማጥናት ጓደኛዬ ጋር ልደር ብላ አስፈቀደቻት። እማዬም ምናልባት አብረው ሲያጠኑ ውጤቷ ይሻሻላል ብላ ስላሰበች አልተቃወመቻትም።
.......
ጓደኛዋ ቤተሰቦቿ ካሉበት ገጠር ለውርጃ ይጠቀሙታል ያለችውን መድኃኒት ሰጠቻት እናም ግጥም አድርጋ ጠጣችው። ለትንሽ ጊዜ ሁሉም ሰላም ነበር ሌሊት ላይ ግን ከበድ ባለ ሁኔታ ደም ይፈሳት ጀመር። ልጁ እየወረደ ነው ብለው ስላሰቡ የሚሆነውን በዝምታ ጠበቁ..... ከሰአታት በኋላ ግን ትርሲት እየደከመች መጣች። ጓደኛዋ የአከራዮቿን ቤት አንኳኩታ እርዳታ ጠየቀች እናም ወደ ሆስፒታል ተወሰደች ግን አርፍደው ነበር። ትርሲት ብዙም ሳትቆይ አሸለበች ።

አይደለም እኔ ልጇ ማንም ላሶርድ ቢላት ኡ ኡ እንደምትል አላጣሁትም ግን.......

"እማዬ በዘመናዊ መንገድ እኮ ነው በሀኪም" አልኳት

"አይሆንም ብያለሁ አይሆንም..." ጮኸችብኝ.... ንግግራችንን ሲሰማ የነበረው ዶክተር ተነስቶ አጠገባችን መጣና አረጋግቶ ወንበር ላይ ካስቀመጠን በኋላ

"ህያብ ከማስወረድ ውጪ ሌላ አማራጭ የለም ብለሽ ታስቢያለሽ" አለኝ።

"አዎ ዶክተር መማር እፈልጋለሁ በዛ ላይ የሰው መሳቂያ ነው የምሆነው.... ማንም ተደፍራ ወለደች የሚለኝ የለም...." ንግግሬን ሳግ አቋረጠኝ

"እርሶስ ወይዘሮ ወይንሸት ምን ይላሉ"

"እኔ ቆሜ እያለሁ ልጄን ለሞት አሳልፌ አልሰጣትም በፍፁም አይሆንም" እርግጠኝነት በተሞላበት መንፈስ ተናገረች።
......
"እኔም የእናንተን ሀሳብ ልስማ ብዬ እንጂ ፅንሱ ሶስት ወር አልፎታል በዛ ላይ ልጅ ነሽ ከማስወረዱ ብትወልጂው ይሻላል ለሱም ቢሆን እድሜሽ ገና ስለሆነ ያላቋረጠ የህክምና ድጋፍ ያስፈልግሻል......" ይሄን እና የመሳሰሉትን ሲያወራ እናቴ 'እህ' እያለች አንገቷን እየነቀነቀች ትሰማዋለች።

ትቻቸው በሀሳብ ነጎድኩ ከዛስ አልኩ ለራሴ...... ከዛስ ትምህርቴ ሊቀር..... የሰፈር ሰው መጠቋቆሚያ ልሆን...... ከዛስ እ...... የወደፊት እጣ ፋንታዬስ.... እዚሁ የተወለድኩበት ሀገር በናቴ እግር ተተክቼ ፓስቲ እና ጠላ ስሸጥ ልጄን ለማሳደግ ደፋ ቀና ስል በህሊናዬ ሳልኩ።
....
"አይሆንም" አልኩ ቃል አውጥቼ.... ያልኩት መልሶ አስደነገጠኝ

"ምኑ ነው የማይሆነው ሚጣዬ.... ዶክተር ያለውን ሰምተሻል አይደል እንደዛ እናደርጋ...." ዶክተር! ዶክተር ምንድነው ያለው?...... ምንም ይበል ምን አገባኝ። ዶክተር እኮ ህልሙ ይሁንም አይሁንም ዶክተር ሆኗል አይደል.... ደግሞ እሱ ምን አለበት በሰው ቁስል ላይ እንጨት መስደድ ለሱ ቀላል ነው.... "ውለጂው" አለ አይደል? መውለዴ የሚያሳጣኝ ነገር ግን ግድም አይሰጠው.... ይቺ የአስራ ሶስት አመት ልጅ ከምታስወርድ ትውለድ ሲል ይቺ የአስራ ሶስት አመቷ ህያብ ህልሟን ትቅበረው ማለቱ እንደሆነ አልገባውም።

''ወለድኩ ማለት ህልሜ ሁላ ይቀበራል" አልኩት የመጨረሻ እድሌን ልሞክር ብዬ

"አንቺ ከምትቀበሪ ህልምሽ ቢቀበር አይሻልም" አለችኝ እናቴ.... ምንም ሳልናገር ቢሮውን ለቅቄ ወጣሁና ወደቤት መንገድ ጀመርኩ እማዬ ከኋላዬ ደረሰችብኝ። ምንም ሳንነጋገር ጎን ለጎን ትንሽ ከሄድን በኋላ

"እስኪ ሚጣዬ ሆድሽን ሸፈን አድርጊው" ብላ የለበስኩትን ፎጣ ስባ ሆዴን አለበሰችው.....
..........
እና ሁሉም ነገር እንደዚህ ሊቀጥል ነው? አይሆንም! እናቴም እኔም አንገታችንን ከምንደፋ የሆነ ሀሳብ በውስጤ መጣልኝ። እንደማደርገው እርግጠኛ ሆንኩ.....

ይቀጥላል