Get Mystery Box with random crypto!

#ባል_አስይዞ_ቁማር ፡ ፡ #ክፍል_ሰላሳ_ሶስት ፡ ፡ #በዘሪሁን_ገመቹ_ዋቤ /// ቀለበቱን ከቀረ | አትሮኖስ

#ባል_አስይዞ_ቁማር


#ክፍል_ሰላሳ_ሶስት


#በዘሪሁን_ገመቹ_ዋቤ
///

ቀለበቱን ከቀረቀረችበት ኪሷ አወጣችና ቀጥታ በድፍረት ወደሰውዬው ጠረጰዛ በመሄድ ፊቱ ቅጭልጭል አድርጌ ስታስቀምጥለት አንዴ ቀለበቱን አንዴ ደግሞ እሷን አንዴ ደግሞ ሴትዬዋ ወደሄደችበት መታጠቢያ ቤት እያፈራረቀ ሲያይ ቆየና እጅን ወደ ኪሱ ሰዶ ፈተሸ..
"አልገባኝም ከየት አገኘሽው?"ሲል ጠየቃት፡፡
"ቅድም መታጠቢያ ቤት ስንጋጭ መሠለኝ ከኪስህ የወደቀው...ከወለሉ ላይ ነው ያገኘሁት...ወዲያው አምጥቼ እንዳልሰጥህ ሴትዬህን ፈራሁ…አልተሳሳትኩም ያንተ ነው አይደል?።››
"አዎ የእኔ ነው ..አመሠግናለሁ..ሲወድቅ ግን እንዴት ድምፅ ሳልሰማ?"
"ምን አልባት ቀልብህ ሴትዬህ ላይ ስለሆነ ይሆናል"አለችውና የእሱን መልስ ሳትጠብቅ ወደ ወንበራ ተመለሰች።
ልዩ በእፍረት እንደተሸማቀቀች ከእዛ ሆቴል ተያይዘው ወጡ …ከቤት ሌላ መኪና ተልኳላት ስለነበረ ቀጥታ ምንም ሳይነጋገሩ በራሷ ፍቃድ ወደእራሱ ቤት ይዛው ሄደች፡፡ ….ከዛ ሁለቱም እሱ አልጋ ላይ በመሀከላቸው መተው ያለበትን ክፍተት አስጠብቀው ጋደም በማለት ማውራት ጀመሩ….እርግጥ እራሷ ነች እንዲያወሩ የመጀመሪያውን የመነሻ ጥያቄ የጠየቀችው….
‹‹ግን ከሌባ ጋር ጎደኛ መሆን አልደበረህም?››ዝም ብላ በውስጧ ስታብሰለስል የቆየችውን ጥያቄ ድንገት የጠየቀችው፡፡
"ሰው ሁሉ እኮ ሌባ ነው"አለት

ገርሟት"እንዴት ማለት?"ስትል ጠየቀችው፡፡

"በየቀኑ አንዳችን የአንዳችንን የህይወት ኃይል ስንዘርፍ ወይንም አስገድደን ስንቀማ ነው የምንውለው"

"አሁንም አልገባኝም"

"እኔ አሁን ብጮህብሽ ባመናጭቅሽ አንቺ መላ አካልሽ ሽምቅቅ ይላል ፤ ሰውነትሽ ይንቀጠቀጣል፤እኔ ጩኸቴንና ስድቤን እየቀጠልኩ ስመጣ አንቺ እየተሸማቀቅሽ በራስ የመተማመንሽ እየወረደ ይመጣል ..ያ ማለት ኃይልሽን እየመጠጥኩና አንቺን ባዶ እያደረኩሽ ነው ማለት ነው…ከዛ ደካማና ሽቁጥቁጥ በማድረግ እኔ በራስ መተማመኔን አሳድጋለሁ ማለት ነው..አየሽ ታዲያ ይሄ እንደውም ረቂቅ ሌብነት ነው፡፡ ››
‹‹እና እቤት ሰራተኞች ላይ ስጮህና ሳንቧርቅባቸው….ሲሸማቀቁና ሲሽቆጠቆጡ..ኃይላቸውን እየሰረቅኩባቸው መሆኑ ነው፡፡››

‹‹አዎ ለዛውም የህይወት ኃይላቸውን…ሰው ተበሳጭቶ ተበሳጭቶ በመጨረሻ ምንድነው የሚሆነው..?ለመኖር ያለውን ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ያጣል…፡፡ ያ ማለት ምን ማለት መሰለሽ...ለመኖር የሚያስፈልገው ኃይል ውስጡ የለም ማለት ነው….የት ሄደ…. በዙሪያው ባሉ በተለያዩ ሰዎች ቀስ በቀስ እየተዘረፈ እንዲሞጠጥ ተደርጎል ማለት ነው….እና ትልቁ ሌብነት የሰውን የውስጥ ሰላም ማሳጣት ነው፡፡››

‹‹እና አንተ ለዛ ነው…ለሰው አስተያየት በምትሰጥበት ጊዜ ስሜትህን አብዝተህ ለመቆጣጠር የምትጥረው…?››

‹‹አዎ በተቻለኝ መጠን ከማንም ጋር ቢሆን ሰላማዊ የሆነ፤ከጭቀቅጭቅ የፀዳ፤በቁጣ ያልታጀበ ..በእኩልነት ላይ የተመሰረት ንግግር ማድረግ ነው ምፈልገው..እንደዛ ሲሆን ማለቴ አሁን እኔና አንቺ በጓደኝነት መንፈስ ጎን ለጎን ተቀምጠን ፍትሀዊ በሆነ በእኩልነት ሚዛን ሀሳብ ስንለዋወጥ ኃይልም እንደዛው ሚዛኑን በጠበቀ መልኩ እየተለዋወጥን ነው....ማለት ከእኔ ኃይል ወደአንቺ ይሄዳልም መልሶ ወደእኔ ይመጣልም …..የሁለታችንም ኃይል በእኩልነት እያደገ ደስተኛና ጤነኛ እየሆንን እንመጣለን..እና አንቺም ሁል ጊዜ ከሰዎች ጋር ያለሽ ግንኙነት እንደዛ እንዲሆን እንድታደርጊ ነው የምፈልገው፡፡››

‹‹እሞክራለሁ..ብቻ በውስጤ ያለውን ክፉ አመል በሆነ አስማታዊ ጨረር የሚያጠፋልኝ የሆነ መላአክ ቢኖር በህይወቴ የተከማቸውን ሀጥያት አንዴ ጥርግርግ አድርጌ በማፅዳት ንጽህ የሆነ ኑሮ ነበር መኖር ምኜቴ ››አለችው…የተናገረቸው ከአንጀቷ ነው…ልክ እንደእሱ አይነት ሰው መሆን ነው የምትፈልገው…

‹‹አይዞሽ.አንቺ ብቻ ከዚህ በፊትም እንደነገርኩሽ እራስሽን ለማከም ዝግጁ ሁኚ.. የልጅነትሽ ወይም የታዳጊነት የህይወት ክፍልሽ ላይ መድሀኒቱ ቁጭ ብሎ እንደሚጠብቅሽ ይሰማኛል….ከአባትሽ ጋር ያለሽ ግንኙነት እሱን በማጣትሽ የተፈጠረብሽ የስነልቦና ክፍተት፤ከእናትሽ ጋር የነበረሽ ግንኙነት…ብቻ በደንብ አስተውለሽ አሰላስይ….ከታሪክሽ የሆነ ጥግ ለምን የስርቆት ልክፍት እንደተፀናወተሸ የሚያስረዳ ምክንያት ይገለፅልሽ ይሆናል...ከዛ ዟምክንያቱን ባወቅሽ ቀን የበሸታሽ መርዝም በራሱ ይከስማል..ትድኛለሽ፡
አይን አይኑን በስስትና በአድናቆት እያየችው፡‹‹እንደቃልህ ይሁንልኝ››አለችው ፡፡
እና በሀሳብ ቁዝዝ አለች‹‹.አሁን እኔ ቃልዬ አንተን በጣም አፈቅርሀለሁ..ካየሁህ ቀንና ሰዓት ጀምሮ አንተን ከማለም ውጭ ሌላ ሀሳብ የለኝም ..ስለዚህ ምንም እንኳን ሴት ብሆንም በድፈረት እንድታገባኝ እየጠየቅኩህ ነውሪ’ዩ ››ልትለው ነው የምትፈልገው …ግን እነዛን ቃላቶች ከአንደበቷ አላቃ ማውጣት በድፍረት ለመጠየቅ ትልቅ እንቅፋት የሆናት እሱ በግልፅ ሚያውቀውን ድክመቷና ደግሞም በየሰው ቤት ካሜራ እየተከለች የሰው ሚስጥር የማነፍነፍ ክፍ በሽታዋ ምክንያት ነው፡፡

ቃል ‹‹.ትንሽ እንተኛ እንቅልፌ መጣ›አለና ወደእሷ በመዞር እጁን ተከሻዋ ላይ ጣል አድርጎ በማቀፍ አይኑን ጨፈነ…..እሷም በተመሳሳይ ወደእሱ ዞረችና እጅን በትከሻው ላይ አዙራ አቀፈችውና ልክ እሱ እንዳደረገው አይኖቾን ጨፈነች…..ለመተኛት ፈልጋ ወይም እንቅልፍ ተጫጭኗት አይደለም…ፈፅሞ የእንቅልፍ ስሜት የለባትም…እፍረቱ እስከአሁን በደም ስራ እየተሰራጨ ነው..እና ደግሞ የመከራትም ነገር እያብሰለሰለችበትም ነው…

አባቷን ፍለጋ መንቀሳቀስ እንዳለባት ሰሞኑን ወስናለች፡፡ከዚህ በሽታዋ ለመፈወስ ምትችለው ሁለት ነገር ሳታደርግ እንደሆነ ሰሞንኑ ባደረገችው ማሰላለሰል ውሳኔ ላይ ደርሳለች፣..እንደኛው ከቃል ጋር ያለላትን ግንኙነት የሆነ መስመር ማስያዝ ስትችል..ከዛ ቀጥሎ አባቷን ፍለጋ መሰማራት ..ከዛ አባቷን በህይወት ካገኘችት ጥሩ ነው ፤ብዙ ጥያቄዎቼን ይመልስላታል..ቃል እንደሚለውም ምን አልባት የበሽታዋ መድሀኒት ከአባቷ መገኘት ጋር የተሳሰረ ሊሆን ይችላል……ስትል እምነት አድሮባታል..ሞቶም ከሆን የተንጠለጠለች ነፍሷ እርፍ ትልና ስለእሱ ማሰብ ታቆማለች፡፡

የቃልን ጉዳይ በቅርብ መቋጫ ልታበጅለት እንደሚገባ ተሰማት ‹‹….እንደውም ዝም ብዬ ከዛሬ ነገ እያልኩ ባንዛዛሁት ቁጥር ዛሬ እንደሰራሁት አይነት ሌላ ስህተት ፊቱ እሰራና ምንም ነገር ሳይል ከእጄ ሊሾልክብኝና እስከወዲያኛው ላጣው እችላለሁ…እንደውም ነገ ለምን አላደርገውም..አዎ ነገ..››ወሰነች ፡፡ውስጧ የሚጥለቀለቅ ደስታ መሰቃየት ጀመረ….ቃል ነቅቶ እጁን ከላዮ ላይ አነሳ፡፡ ከእንቅልፉ በመባነኑ በጣም ነው ደስ ያላት፡፡ውሳኔ ላይ ከደረሰችበት ደቂቃ ጀምሮ ወደቤት እስክትሄድ ቸኩላለች….ለምን ?ለነገ ለመዘጋጀት….ከአንድ ሰዓት እንቅልፍ በኃላ ሲነሳ ፈጠን ብላ ከአልጋዋ ወረደች፡፡
‹‹ልትሄጂ ነው እንዴ?››
‹‹አዎ እቤት የምሰራው ስራ አለኝ፡፡››
‹‹ልሸኝሽ ታድያ?››አላት.. አልጋውን ለቆ እየተነሳ..
‹‹አይ አልፈልግም…ቃልዬ ነገ ከሰዓት የምትሄድበት ቦታ አለ እንዴ?››ልስልስ ባለ አሳዘኝ ድምፅ ጠየቀችው፡
‹‹አይ ..ምንም ፕሮግራም የለኝም››
‹‹በቃ በጣም ለጥብቅ ጉዳይ እፈልግሀለሁ…ስድስት ሰዓት እዚህ እቤት እመጣለሁ…››
‹‹ከዛ የት ልትወስጂኝ ነው?››
‹‹የትም እዚሁ ነው ምናመሸው..ማለቴ ውለን ምናመሸው…. ነግሬሀለሁ…ስድስትሰ ሰዓት እመጣለሁ..ደግሞ እኔና አንተ ብቻ..ለጥብቅ ጉዳይ ነው የምልግህ››