Get Mystery Box with random crypto!

#ባል_አስይዞ_ቁማር ፡ ፡ #ክፍል_ሠላሳ_ሁለት ፡ ፡ #ዘሪሁን_ገመቹ_ዋቤ /// ቃል ቤት የተፈጠ | አትሮኖስ

#ባል_አስይዞ_ቁማር


#ክፍል_ሠላሳ_ሁለት


#ዘሪሁን_ገመቹ_ዋቤ
///

ቃል ቤት የተፈጠረው ድራማ ወር አልፎታል….በዚህ የጊዜ ክፍት ውስጥ መአት ነገሮች ተከስተዋል.ልዩ ትምህርቷን ተመርቃ ዲገግሪዋን ይዛለች…በምረቃት ፕሮግራሟ ላይ ቃል መድሀኔና ጊፍቲም ጭምር ተገኝተው ደስታዋ ተካፋይ ሆነዋል.እርግጥ ነገሩ ቀላል አልነበረም፤ በተለይ የልዩ እናት መድሀኔን ዝግጅቱ ላይ ሲመለከቱት ንዴታቸውን መቆጣጠር አቅቶቸው እንዴት ተደርጎ በማለት ሂድልኝ ሊሉት ፈልገው ነበር ፤በልዩ ግሳፄ ነው እንደምንም እራሳቸውን ተቆጣጥረው ሊያልፉት የቻሉት…፡፡በወቅቱ ልዩ ቃልን ከእናቷ ጋር ማስተዋወቅ ስለቻለች ከፍተኛ ደስታ ተስምቶታል…፡፡ሌላው ልዩና ቃል አንድ ላይ በመተጋገዝ    መድህኔ እና ጊፍቲ አብረው እንዲቀጥሉ ማድረግ ችለዋል፡፡መድሀኔም እንደምንም እቤተሰቦቹን በማሳመን የጊፍቲ ሆድ ከመግፋቱ በፊት በቅርብ ለመጋባት ወስነው ዝግጅት ላይ መሆናቸውን ለእነልዩ ነግረዋቸዋል፡፡እንደውም የጊፍቲ አንደኛ ሚዜ ልዩ የመድሀኔ ደግሞ ቃል ሊሆን እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተዋቸዋል፡፡ ያው ጓደኝነታቸውም ቃል በሚፈልገው መሰረት እንደድሮ ቀጥሏል‹‹..አሁን ይሄ ታሪክ ሙሉ ሊሆን የቀረው አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡የእኔና የቃል ጉዳይ..እሱንም ጠብቁኝ በቅርብ ይሆናል….እስከአሁን እኔ አስቤ ያላሳከሁት ነገር የለም፡፡››ስትል ዛተች
ቀኑ ቅዳሜ  ነው...ከቃል  ጋር   ለመገናኘት ተቀጣጥረው ነበር።
እሱ ወደሚገኝበት ቦታ እየነዳች ስለእሱ በማሰብ ትለፈልፋለች…ብቻዋን ስትለፈልፍ ለሚመለካተታ እግረኛ ከኃላ የመኪናው ወንበር ላይ  ተኝቶ የሚያዳምጣት ሰው አለ ብሎ ነው የሚያስበው
‹‹ቆንጆ ነው።ቆንጆ የሚጠላ ሰው የለም። ግን ከስጋው ቁንጅና ይልቅ በነፍስ ቁንጅና ነው ቀድሜ እጅ ሰጠሁት ።እርግጥ የነፍስ ውበትን ልክ እንደስጋ ውበት በቀላሉ  ለመለየት አይቻልም። ድብቅና ስውር ነው።መረጋጋትና በአስተውሎት መገምገምን ይጠይቃል። ውስጣዊ ስለሆነ በውስጣዊ አይን ብቻ ነው ሊታይና  ሊረጋገጥ የሚችለው።እሱን በተመለከተ ግን የውጭ ውበቱን ዘግይቼ ና ተረጋግቼ ነው ያየሁት።ቀድሞ ውስጤ የሠረገው የነፍሱ ውበት ነው። ያሽመደመደኝ ሰባአዊነቱና የተሞረደ አስተሳሰብ ነው።እንደእሱ አይነት ሰው ይኖራል ብዬ አስቤ አላውቅም።መኖሩን ካወቅኩም በኃላ የእኔ ሰው መሆን አለበት ብዬ ቀን ከሌት ከመቃዠት ውጭ ሌላ ምንም አይነት የስጋም ሆነ የነፍስ ስራ የለኝም፡፡ ››
የተቃጠሩበት ቦታ ለመድረስ ከአንድ ፌርማታ በታች ሲቀራት መኪናዋ ድንገት  ተበለሸባት፡፡እቤት ደወለችና ነገረቻቸው..ሌላ መኪና አምጥተው እስኪቀይሩላት መኪዋን ቆላለፈችና .በእግር ቃል ወደሚገኝበት ቦታ በእግሯ ወክ በማድረግ ሄዳ አገኘችው‹‹ ምሳ  ልጋብዝህ ብላው እዛው አካባቢ አንድ ሬስቶራንት ይዛው ገባች..።እሷ ቁርስ ስላልበላች በጣም እርቧታል..እሱ ይራበው አይራበው አታውቅም።ግን ከረሀቡም በላይ የእሷ ዋና አላማ ከእሱ ጋር የምታሳልፈው ጊዜ በሰበብ አስባብ ማስረዘም ነው።
ፊት ለፊት ተፋጠው ተቀመጠዋል ..የየምርጫችውን አዘዙ ።  ሰዓቱ ስድስት ሰዓት ያልሞላ ቢሆንም በሬስቶራንቱ ውስጥ ያሉት ተስተናጋጆች እነሱ ብቻ አይደለሉም።ቢያንስ 30 ፐርሰንት የሚሆነው ወንበር በጥንድም ነጠላም ሆነው በተቀመጡ ሰዎች ተይዞል።
ከተወሰነ ጥበቃ በኃላ ምግባቸው ቀርበ፡፡
እሷ ለመገብ እጇን ወደምግቧ በመዘርጋ ላይ እያለች ቃል  አንገቱን ለፀሎት ሲያቀረቅር አየችና በእፍረት በአየር ላይ ያንከረፈችውን እጆን ቀስ ብላ ወደሃላ ሳበችውና እሷም በተመሳሳይ አንገቷን ደፋች፡፡
እሱ ፀሎቱን ለእሷ በሚሰማ ነገር ግን ሌሎችን በማይረብሽ የተለሳለሰ ድምፅ ቀጠለ
‹‹እነዚህን የምግብ ግብአቶች ዘርተው ያበቀሉ ተንከባክበው ለፍሬ ያበቁ የገበሬ እጆች የተባረኩ ይሁኑ።የተመረቱትን ግብአቶች ከገበሬው በመግዛት ያለንበት ድረስ በማምጣት የሸጡልን ነጋዴዎች ምስጋናችን ይድረሳቸው።ይሄን እንጀራ ለማስገኘት ጤፍን ወደ ድቄትነት የቀየሩልን የወፍጮ ቤት ባለቤቶችና ሰራተኞች ባሉበት ምስጋናችን ይድረሳቸው ፤ ድቄቱን አብኩታና  ጋግራ ይሄን የመሠለ ማራኪ እንጀራ እንድንቆርስ ላደረገችን እንጀራ ጋጋሪዎ እመቤት እናመሠግናለን።ይሄንን መአዳችን ላይ የቀረበልንን ሚስጥራዊ ውሀ  እንድናገኝ  ኃላፊነታቸውን በበጎነት ለተወጡ የውሀ ልማት ባለሞያዎች እናመሠግናለን።ይሄንን ምግብ በግሩም ሁኔታ እንዲበስል የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲኖር ላደረጋችሁልን የማብራት ሀይል ሰራተኛች እናመሠግናለን።በቀን ውስጥ ስለተደረገልን ሁሉ አናመሰግናለን፡፡››
ብሎ የተለመደ ገራሚ አይነት ፀሎቱን ካንበለበለ በኃላ የቀረበላቸውን መመገብ ጀመሩ

አልፎ አልፎ እያወሩ በመሀልም እየተጓራረሱ በመብላት ላይ ናቸው ።የእሷ አይኖቸ ግን በመሀል ሳትፈልግ ከጎናችው አንድ ወንበር ተሻግሮ ከሴት ጋር ካለው ጎልማሳ ሰው ላይ ይንከራተት ጀመር ‹‹..አሁን ፊት ለፊቴ ያለው ሰው ቃል ባይሆን  ግንባሬን ብሎ በተቀመጥኩበት ጎልቶኝ ይሄድ ነበር?››ስትል አሰበች፡፡
ቢሆንም ግን እራሷን መግታት አልቻለችም፡፡እርግጥ ችግሯ ሰውዬው አይደለም  …፡፡ከጣቱ ወርቅ አውልቆ ኪስ ወስጥ ሲከት አይታ ነው...፡፡ሰውዬው እንደዛ  ያደረገው አብራው ያለችው  ሴት ወደ ጠረጰዛው መጥታ ከፊት ለፊቱ ከመቀመጧ በፊት ነው።ወርቁን ከእጣቱ በችኮላ መንጭቆ በማውለቅ ጃኬት ኪስ ውስጥ  እንደነገሩ    ሻጥ ስላደረገው  በተንቀሳቀሰ ቁጥር  አይኗ ላይ በማብረቅረቅ  እየተፈታተናት ስለሆነ ነው...አስሬ   አይኗ ወደእሱ አየቀባዠረ  የምትቅበጠበጠው።ለጥንዶቹ ምግብ ሲቀርብላቸው ሰውዬው  ሊታጠብ ቀድሞ  ከተቀመጠበት ተነሳና ወደ መታጠቢያ ቤት አመራ..
ልዩም ምንም ሳትናገር ድንገት ከተቀመጠችበት ተነሳችና ምግብ ስትበላበት የነበረ እጇን እንዳንከረፈፈች ከኃላው ተከተለችው... መታጠቢያ ቤት ገብቶ እጅን ሲታጠብ ከአጠገብ ያለው መታጠቢያ ስር ቆመችና ለመታጠብ እጇን ዘረጋች...ታጥቦ ጨርሷ ለመውጣት ሲራመድ እሷም መታጠቧን አቁማ ለመዞር የፈለገች መስላ ተጋጨችው...ቀድሞ ይቅርታ ጠየቃት‹‹...ችግር የለውም› ብላ አሳለፈችው...አንድ አስር እርምጃ ከተራመደ በኃላ ጠበቃችና ከኃላ ተከተለችው።ስትደርስ ወንበሩ ላይ ተደላድሎ ተቀምጦ አብራው ያላቸውን ሴት ለማጉረስ እጅን እየዘረጋ ነበር ...በፊት ለፊታቸው አልፋ ወደ ወንበሯ ሄደችና  ተቀመጠች...ምግብና ሳትጠግብ ያቆመች ቢሆንም መልሳ መብላት መጀመር አልቻለችም ..እጇን ከታጠበቸ በኃላ እንዴት ብላ እጇን ትዘርጋ?

ቃል በዝምታ አቀርቅሮ ምግብን እየተመገበ ነው...ካቀረቀረበት ቀና ብሎ ሳያያት"ምነው ብይ እንጂ ››አላት፡
"አረ ጠገብኩ እኳ ...ታጥቤ ስመጣ እያየሀኝ"
"ከጠገብሽ ጥሩ ነው...እስከአሁን በልተሽ የጠገብሽው ለራስሽ ነው..ቀጥሎ ደግሞ ለእኔ ብይልኝ"አላት፡፡
አባባሉ ግራ አጋባት"እውነትህን ነው?"
"አዎ እውነቴን ነው"አለ ኮስተር ብሎ።
"እንዲህ ብለኸኝማ  እምቢ አልልህም"አለችና እንደአዲስ መብላት ጀመረች።
ምግባቸውን ጨርሰው፤ እጃቸውን ታጥበው ፤  ብና አዘው እየጠጡ ነው። ምንም እያወራት አይደለም ።ሁለቱም የራሳቸው ሀሳብ እያመነዠጉ ነው።ከጎናቸው ያሉት ጥንዶች የሚበሉትን ጨረሱና ለመታጠብ ሴቲቱ ቀድማ ወደመታጠቢያ ቤት ሄደች ...እሱ ቁጭ ካለበት ሳይነሳ ፊቱ ያለውን የቢራ ጠርሙስ እያነሳ እየተጎነጨ ነው...