Get Mystery Box with random crypto!

ከ16 ሚሊዮን 400 ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የወሰን ቁርቁር አንደኛ ደረጃ ትምህርት | ATC NEWS

ከ16 ሚሊዮን 400 ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው የወሰን ቁርቁር አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተመረቀ
****

በአብክመ በኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን አስተዳደር ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ አሊ በጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ባለፉት አመታት በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት የወደመውን የወሰን ቁርቁር ቀበሌ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዛሬ ከሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መካሻ አለማየሁ ጋር በጋራ መርቀው ከፍተዋል።

በምርቃት መርሐግብሩም ላይ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት የ112ኛ አየር ወለድ ክ/ጦር አዛዥና የኮማንድ ፖስት አስተባባሪ ኮሎኔል አሰፋ አየለ፣ የኦሮሞ አስተዳደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ አሊ እና የኦሮሞ አስተዳደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብደላ ሼህ አህመድን ጨምሮ የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መካሻ አለማየሁ፣ የሰሜን ሸዋ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኤልያስ አበበ እና ሌሎች የሁለቱ ዞን ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ከአጎራባች ቀወት ወረዳ፣ ሸዋሮቢት እና አጣዬ ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ አመራሮች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ወጣቶችና ሴቶች ተገኝተዋል።

ትምህርት ቤቱ 10 የመማሪያ ክፍል ያለው 3 ብሎክ እና ስታንዳርዳቸውን የጠበቁ መፀዳጃ ቤቶች ያሉት መሆኑ ተገልጿል።

የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አሊ ሰይድ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር ባለፉት አመታት በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ጉዳት ከደረሰባቸው ቀበሌዎች መካከል የወሰን ቁርቁር ቀበሌ አንዱ መሆኑን ተናግረዋል። በአካባቢው በነበረው ግጭት የመሠረተ ልማት ተቋማት ላይ ጉዳት ከመድረሱ ባሻገር የነገ ትውልድ ተማሪዎች ላይ የስነልቦና ቀውስ መድረሱን ገልጸዋል።

የኦሮሞ አስተዳደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አህመድ አሊ በበኩላቸው ቀጠናው የሚሰቃየው በፅንፈኝነት አመለካከትና ተግባር ነው ብለዋል። "ፅንፈኝነት ያለ እኔ ላሳር የሚል ከራሱ ውጪ ለህዝቡ ክብር የማይሰጥ ነው" ቀጠናው የፅንፈኞች መነገጃ እንዳይሆን ሁላችንም ተባብረን መስራት ይኖርብናል ብለዋል።

ትምህርት ቤት ስንመርቅ እና እርሻ ስናርስ የማይጠይቁን አንድ ጥይት ሲተኮስ ለህዝብ ያዘኑ መስለው ሚዲያ ላይ የሚያራግቡ አካላት አሉ ያሉት ዋና አስተዳዳሪው÷ የሚዲያ አጠቃቀማችንን በአግባቡ መግራት እንዳለብንም አስገንዝበዋል። የተዛባውን ትርክት ማረም እንደሚገባም ነው ያሳሰቡት።

በመጨረሻም በምርቃት መርሐግብሩ ላይ ለተገኙ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ኃላፊዎች የአልባሳት ስጦታ ተበርክቷል።

ምንጭ :- ጅሌ ጥሙጋ መንግስት ኮምኒኬሽን

ለጥቆማ @atc_newsbot
https://t.me/atc_news