Get Mystery Box with random crypto!

አሉታዊ ነህ ወይስ አዎንታዊ ? አሉታዊ ስህተትን ይፈላልጋል ፤ አዎንታዊ መፍትሄን ያገኛል | አስቂኝ ቀልዶችና ሌሎችም

አሉታዊ ነህ ወይስ አዎንታዊ ?

አሉታዊ ስህተትን ይፈላልጋል ፤ አዎንታዊ መፍትሄን ያገኛል ፡፡ አሉታዊ ከንፈር የሚመጥለት ሰው ይፈልጋል ፤ አዎንታዊ መፍትሄን ይፈልጋል ፡፡ አሉታዊ በሰዎችና በሁኔታዎች ሲፈርድ ይታያል ፤ አዎንታዊ ሁኔታዎችንና ሰዎችን ለመቀየር ራሱን ያቀርባል ፡፡ አሉታዊ በእጁ ላይ ስላለው ጥቂት ፍሬ ሲነጫነጭ ይታያል ፤ አዎንታዊ ተነስቶ ይዘራዋል ፡፡

አሉታዊ በፊቱ መከራና ውድቀት እንዳለ ያስባል ፤ አዎንታዊ የስኬት ዘመንን ወደ መኖር ለማምጣት ይሰራል ፡፡ አንድ ሰው አሉታዊውን አመለካከት በመጣል ወደ አዎንታዊው ለመዝለቅ ራሱ ማስለመድና አመለካከቱን ንድፍ መቀየር የግድ ነው ፡፡ አዎንታዊን ዝንባሌ ያዳበሩ ሰዎች እይታዎቻቸው አስገራሚና ለስኬት አመቺ ናቸው ፡፡ የሚከተሉትን የአዎንታዊ ሰዎች አመለካከት እንመልከት ፡፡

የዛሬ አለመሳካት ዘላቂ እንዳልሆነ ማወቅ “ጸሃይ የጠለቀችው በአዲስ ሁኔታ ልትወጣልኝ ነው” - Robert Browning ፡፡ በአዎንታዊ አመለካከት የተሞላ ሰው እይታው ይህ ነው ፡- የጠለቀ እንደገና ይወጣል ፤ የወደቀ እንደገና ይነሳል ፤ የጠፋ እንደገና ይገኛል ፤ የተበላሸ እንደገና ይታደሳል ፡፡

ነገሮች ከዚህ የከፉ ሊሆኑ እንደሚችሉ ማሰብ “ሁል ጊዜ የተበላሸውንና የጠፋውን ሳይሆን የተረፈውን አስብ” - Robert H. Schuller ፡፡ አዎንታዊ ሰው ነገሮች ተበላሽተው እያሉ እንዳልተበላሹ ለማስመሰል አይኑን አይጨፍንም ፡፡ በምትኩ እውነታውን ለመጋፈጥ አይኑን ይከፍታል ፣ የሚያተኩረው ግን የተበላሸው ላይ ሳይሆን የተረፈው ላይ ነው ፡፡

በስሜትና በጊዜአዊ ግምት አለመመራት “ነገ ዓለም ያከትምላታል ብባልም እንኳ ዘርን ከመዝራት አልመለስም” - Martin Luther ፡፡ ለአዎንታዊ ሰው ነገር የሚያከትምለት በርግጥም ሲያከትምለት ብቻ ነው ፡፡ እስከዚያው ድረስ እንደሚሳካ ፣ ሁኔታዎች እንደሚለወጡና ሊሻሻሉ እንደሚችሉ ከማሰብ አያቆምም ፡፡ በአሉባልታና ለጊዜው በተናፈሰ መረጃ-ቢስ ወሬ አደራረጉን አይለውጥም ፣ ወደ ፊትም ከመገስገስ አይገታም ፡፡

የስህተትን አይቀሬነት መቀበል “አብዛኛዎቹ እርሳሶች ለመጻፊያ ሰባት ኢንች ርዝመት ሲኖራቸው ለማጥፊያ ደግሞ ግማሽ ኢንች ላጲስ አላቸው - አዎንታዊ አመለካከት” - Robert Brault ፡፡ ከአንድ እርሳስ ጋር አብሮ ማጥፊያ ላጲስን መስራት የአዎንታዊ ሰው እይታ እንጂ የአሉታዊ አይደለም ፡፡ አዎንታዊ ሰው ነገሮች እንደተጀመሩ ሊቀጥሉ እንደማይችሉ ያውቃል ፡፡ ከዚህ እውቀቱ ጋር ግን የተበላሹ ነገሮች ሊሰረዙና ሊሻሻሉ እንደሚችሉ ጽኑ እምነት አለው ፡፡
═════════❁✿❁ ═════════