Get Mystery Box with random crypto!

በየትኛውም የኢትዮጵያ ጫፍ የተማራችሁ ሁሉ የተማራችሁባቸው ትምህርት ቤቶች ዛሬ የናንተን ድጋፍ ይሻ | Amhara Education Bureau

በየትኛውም የኢትዮጵያ ጫፍ የተማራችሁ ሁሉ የተማራችሁባቸው ትምህርት ቤቶች ዛሬ የናንተን ድጋፍ ይሻሉ - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ
................................................................................

ሰኔ 25/2015 (የትምህርት ሚኒስቴር) በየትኛውም የኢትዮጵያ ጫፍ የተማራችሁ ሁሉ ትናንት የተማራችሁባቸው ትምህርት ቤቶች ዛሬ የናንተን ድጋፍ ይሻሉ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥሪ አቀረቡ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሁሉም ዜጎችና ተቋማት ተሳትፎ የትምህርት ቤቶችን መሰረተ ልማት ለማሻሻል የተዘጋጀውን ሀገር አቀፍ “ትምህርት ለትውልድ” ንቅናቄን አስጀምረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ንቅናቄውን ባስጀመሩበት ወቅት ባደረጉት ንግግር÷ በየትኛውም የኢትዮጵያ ጫፍ የተማራችሁ ሁሉ ትናንት የተማራችሁባቸው ትምህርት ቤቶች ዛሬ የናንተን ድጋፍ ይሻሉ ብለዋል፡፡

ያለትምህርት መስፋፋት በመጪው ዓለም ተወዳዳሪ መሆን ስለማንችል ስለትምህርት ዛሬ የሚጠበቅብንን ልንወጣ ይገባልም ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ድጋፋችንን በተግባር ለማሳየት ሁላችንም በሐሳብ፣ በገንዘብ፣ በጉልበት እንዲሁም ያለንን ሁሉ ለትምህርት ቤቶች ለማዋል የሚያስችለንን "ትምህርት ለትውልድ" ሀገራዊ ንቅናቄ አስጀምረናል ነው ያሉት።

የላቀች ኢትዮጵያን ለመገንባት፤ ቀድመን የላቁ ትምህርት ቤቶችን አብረን እንገንባ ሲሉም በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

ንቅናቄው÷ የቀድሞ ተማሪዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ ባለሃብቶች እንዲሁም ሌሎች የሕብረተሰብ ክፍሎች በትውልድ ቦታቸው በተማሩበት ቦታ እና በሚሠሩበት አካባቢ የትምህርት ቤቶችን መሠረተ ልማት ለማሟላት አስተዋጽኦ የሚያደርጉበት መሆኑ ተገልጿል፡፡

የግልና የመንግስት ተቋማት እንዲሁም የልማት አጋሮች÷ በሚሰሩባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ትምህርት ቤቶችን መሰረተ ልማት ለማሟላት ዐሻራቸውን የሚሳርፉበት መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

ንቅናቄው በዋናነት ያስፈለገው÷ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች በመሆናቸው ነው ተብሏል፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ እንዳመላከ÷ በኢትዮጵያ ከሚገኙ አጠቃላይ ትምህርት ቤቶች 86 በመቶ የአንደኛና የመካከለኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ለመማር ማስተማር ሥራ አስፈላጊ የሆኑ የመሠረተ ልማት እጥረቶች አሉባቸው፡፡

እንዲሁም ከ71 በመቶ በላይ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በተመሳሳይ መሰረተ ልማት አልተሟሉላቸውም ነው የተባለው፡፡

በትምህርት ቤቶቹ ከሚስተዋሉ የመሰረተ ልማት ችግሮች መካከልም÷ የንጹህ መጠጥ ውኃ አገልግሎት፣ የመጸዳጃ ቤት፣ ኤሌክትሪክ እንዲሁም የትምህርት ግብዓት እጥረት በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር