Get Mystery Box with random crypto!

አሁን ያለውን የትምህርት ስርዓት መቀየር ካልቻልን በቀጣዩ አለም ተወዳዳሪ ሀገርና ትውልድ መፍጠር | Amhara Education Bureau

አሁን ያለውን የትምህርት ስርዓት መቀየር ካልቻልን በቀጣዩ አለም ተወዳዳሪ ሀገርና ትውልድ መፍጠር አንችልም¬- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ

ትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ቤቶችን መሰረተ ልማት ማሻሻል ላይ ያተኮር ህዝባዊ ንቅናቄ ለማካሄድ ያለመ የማስጀመሪያ ሀገር አቀፍ መድረክ ዛሬ አካሂዷል፡፡
..................................................//.............................

ሰኔ 25/2015 ዓ.ም (የትምህርት ሚኒስቴር) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሁሉም ዜጎችና ተቋማት ተሳትፎ የትምህርት ቤቶችን መሰረተ ልማት ለማሻሻል“ትምህርት ለትውልድ” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀውን ሀገር አቀፍ ህዝባዊ ንቅናቄን አስጀምረዋል፡፡

ዛሬ የተገናኘነው ትናንት ያሰተማረን ማህብረሰብ እዳ ስላለብን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒሰትሩ በየትኛውም የኢትዮጵያ ጫፍ የተማራችሁ ሁሉ የተማራችሁባቸው ትምህርት ቤቶች ዛሬ የናንተን ድጋፍ ይሻሉ ብልዋል፡፡

12ኛ ክፍል ሲደርሱ ተማሪዎችን ሰብስቦ መፈተን ብቻ ሳይሆን ከታች መሰረቱ ላይ መስራት ይጠበቃል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ያለውን የትምህርት ቤት ሁኔታ ለመቀየር በገንዘብ፣ በጉልበት እንዲሁም በዕውቀት ተባብረን የላቀች ኢትዮጵያን ለመገንባት፤ ቀድመን የላቁ ትምህርት ቤቶችን አብረን እንገንባ!ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው በተለያየ ጊዜ ትምህርትን ተደራሽ ለማድረግ የተሄደው ርቀት ጥራትን ከማረጋገጥ አንጻር የራሱ አሉታዊ ተጽዕኖ ነበረው ብለዋል፡፡

ለተማሪዎች ትምህርት መቀበል ዋናው ነገር የትምህርት መሰረተ ልማት ቢሆንም አሁን ካሉት ትምህርት ቤቶች ውስጥ 86 ከመቶ የሚሆኑት ከደረጃ በታች ናቸው ብለዋል፡፡

በመሆኑም እነዚህን ትምህርት ቤቶች በመንግስት አቅም ብቻ መገንባት የማይቻል በመሆኑ ሁሉንም ገንዘቡ፣ እውቀቱ እና ጉልበቱ ያላቸውን ማሳተፍ በማስፈለጉ ይህ ንቅናቄ ማስጀመሪያ መድረክ ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡

ትምህርት ቤቶች ላይ ያለውን ችግር ለነገ ልንተወው የሚገባ ባለመሆኑ ፊት ለፊት ልንጋፈጠው ይገባል ያሉት የትምህርት ሚኒስትሩ ይህ የትውልድና የሀገር ጥሪ መሆኑን አውቃችሁ ልትደግፉ ይገባል በማለት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ኢትዮጵያውን ከተባበርን የማናስተካክለው ነገር የለም በዚህም በሚመጡት አምስት ዓመታት የኢትዮጵያን ትምህርት ቤቶች ችግር ሙሉ በሙሉ እንፈታለንም ብለዋል፡፡

በትምህርት ቤቶቹ ከሚስተዋሉ የመሰረተ ልማት ችግሮች መካከልም የመማሪያ ክፍል ፣ የንጹህ መጠጥ ውኃ አገልግሎት፣ የመጸዳጃ ቤት፣ ኤሌክትሪክ እንዲሁም የትምህርት ግብዓት እጥረት በዋናነት ይጠቀሳሉም ተብሏል፡፡

ይህ የትምህርት ቤቶችን መሰረተ ልማት ማሻሻል ህዝባዊ ንቅናቄ በቀጣይም በየደረጃው በሁሉም ክልሎች በተዋረድ እንደሚካሄድ በመደረኩ ተገልጿል፡፡

በመድረኩም የሁሉም ክልል ርዕሰ መስተዳድሮች፣ ሚኒስትሮች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ባለሀብቶች፣አጋር ድርጅቶች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡