Get Mystery Box with random crypto!

ገድለ ተክለ ሃይማኖት ፪ -------ጥያቄ ፪------- ‘የተክለ ሃይማኖት ተቅማጥ ከክ | ፩ ሃይማኖት

ገድለ ተክለ ሃይማኖት ፪


-------ጥያቄ ፪-------
‘የተክለ ሃይማኖት ተቅማጥ ከክርስቶስ ደም ጋር እኩል ነው’ ይላል ይላሉ፡፡ በውኑ ይላልን?

መልስ፡- ሙሉ ገጸ ንባቡ “ክቡር አባታችንም ጌታዬ ወደ ሰማዕትነት ዐደባባይ ሄጄ በስምህ እንድሞት እዘዘኝ አለው፤ ጌታም መጋደልስ ፈጸምክ ከሞት በቀር ምንም አልቀረህም፡፡” አለው ነው የሚለው፡፡ [ገድለ ተክለ ሃይማኖት፤ነሐሴ 1989 ዓ.ም፤ ምዕራፍ ፶፯፤ ገጽ. 195] ከዚህም በኋላ፡- “ወናሁ ትመውት በሕማመ ብድብድ በእኩይ ሞት ወእሬሲ ለከ ኪያሃ ከመ ስቅለትየ በከመ ደመ ሰማዕት እለ እምቅድሜከ አኮ ለባሕቲትከ አላ ደቂቅከኒ እለ ይመውቱ በሕማመ ብድብድ በውስተ ዛቲ ገዳም እኌልቆሙ ምስለ ሰማዕታት ወአወፍዮሙ ለከ በመንግሥተ ሰማያት፡፡”[ዝኒ ከማሁ] ነው ያለው፡፡

+ የቃሉ የግእዝ ትርጒም ሕማመ ብድብድ ማለት ቸነፈር ማለት ነው፡፡ ጻድቁ ተክለ ሃይማኖት የሞቱት በቸነፈር በሽታ ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በዕለተ ዐርብ እንደ ተቀበልኩት መከራ መስቀል አደርግልሃለሁ ያለው፤ ገድላቸውንና በደዌ የተቀበሉትን መከራ ነው፡፡ በመልክዐ ጊዮርጊስ ላይም እንዲህ የሚል አብነት ይገኛል፡፡ ሰላም ለሰኳንዊከ ምስለ ክልኤሆን መከየድ፡፡ ለአጻብዒከ ሰላም ወለአጽፋረ እግርከ አምሳለ መረግድ፡፡ ገባሬ መንክራት ጊዮርጊስ በአቊጽሎ ይቡስ ዐምድ፡፡ አድኅነኒ በጸሎትከ እምነ መከራ ክቡድ፡፡ እስመ እምኔሁ ይወጽእ ቀታሊ ብድብድ፡፡ (መልክዐ ጊዮርጊስ) ትርጓሜውም፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ ሆይ በሁለቱ ተረከዞችህ ጋር ለጫሞችህ ሰላም እላለሁ፡፡ እንደ ከበረ ዕንቊ ለሚያበሩት ለእግር ጽፍሮችህና ጣቶችህም ሰላም እላለሁ፡፡ ተአምር አድራጊው ሰማዕት ሆይ! ደረቁን ምሰሶ ለምለም ተአምራትህን ገልጸሃልና፡፡ ከጽኑ መከራ በጸሎትህ አድነኝ፡፡ ሰውስ ለሥቃይ የሚዳርጉ ረኀብ ቸነፈር ከእሱ ይፈልቃሉና፡፡ ማለት ነው፡፡ ስለሆነም "ብድብድ" የሚለው ረኀብ፤ ቸነፈር ተብሎ ይተረጎማል፡፡

+ የተሐድሶ መናፍቃኑ እንደ ሚሉት ‘ተቅማጥህ እንደ ስቅላቴ ደም ነው’ የሚል ሐረግም ከገድሉ ላይ አይገኝም፡፡ “… እሷንም እንደ ስቅላቴና ካንተ በፊት እንደ ነበሩ ሰማዕታት ደም እቆጥርልሃለሁ፤” [ዝኒ ከማሁ(Ibid)] ነው ያለው፡፡ ይህም ማለት የተክለ ሃይማኖት ሕማም ከሰማዕታት ደም ጋር እኩል እንደሆነ እንጂ ከክርስቶስ ደም ጋር እኩል እንደሆነ አያስረዳም፡፡
ይህም የሆነበት ምክንያት ከገድሉ ላይ እንደምንረዳው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አባ ተክለ ሃይማኖት ብዙ ተጋድለሃል ከእንግዲህ ይበቃሃል ነፍስህ ከመከራ ተለይታ ወደ እረፍት መሄጃህ ጊዜ ደርሷል ባላቸው ጊዜ አባ ተክለ
ሃይማኖት በሰማዕትነት እንድሞት አድርገኝ ብለው ስለለመኑት ነው፡፡ + በሚሞቱበት ጊዜ የሚደርስባቸውን ሕማም እንደ ራሱ መከራና በጦር ተወግተው በስለት ተቆርጠው ደማቸው እንደ ፈሰሰው ሰማዕታት ደም ሲቆጠርላቸው ነው፡፡ ሰማዕታት ለክርስቶስ ሲሉ በጦር ተወግተው በስለት ተቆርጠው ደማቸው እንደሚፈስ አባ ተክለ ሃይማኖትም ለክርስቶስ ሲሉ ሃገር ለሃገር ጫካ ለጫካ ሲንከራተቱ ሕማመ ብድብድን (ቸነፈርን) በጦር ተወግተው ደማቸው እንደፈሰሰው ሰማዕታት ቆጠረላቸው፡፡ ስለዚህ የአባ ተክለ ሃይማኖት ሕማመ ብድብድ (ቸነፈር) እንደ ሰማዕታት ደም ሆኖ ቢቆጠር ሃይማኖት ላለውና ለሚያስተውል ሰው አያደንቅም፡፡
@And_Haymanot
@And_Haymanot_bot