Get Mystery Box with random crypto!

እቴቴ -------- (ደበበ ሰይፉ) ድሮ ነው ፊት በልጅነቴ ሰዐት፤ “ፉራፉሬ” ከማበርበት ቦታ መጥ | ሥነ-ግጥም

እቴቴ
--------
(ደበበ ሰይፉ)
ድሮ ነው ፊት
በልጅነቴ ሰዐት፤
“ፉራፉሬ” ከማበርበት ቦታ
መጥታ
ትጠራኝ ነበር ያች እቴቴ
የጎረቤቴ፤
“ቡጡ ና፣ ወንዝ እንውረድ
ሸንኮራ ቆርጨልህ እንደትጎምድ…”
“እሺ እቴትዬ” ብዬ
ጣሳውን ከእጅዋ ተቀብዬ
እከተላታለሁ ወንዝ እቴቴን
እቴቴን- የጎረቤቴን፡፡
ውሃውን
ፀሐይዋ ስታፀኸየው
በወርቅ መርገፏ ስታጌጠው
እቴቴም
ጨርቋን ስታንጠፈጭፈው
ስታሽ ስትጠመዝዘው
ስትዘረጋ ስትቀለብሰው፤
ደሞም ስትዘፋፍነው
“የኔ ቤት እቆላ ያንተ ቤት አፋፉ
ልቤን አመጡልህ እየደጋገፉ”
ስትለው… ስትለው
ትንሹን ልቤን እንዴት ነበር ደስ የሚለው
ደስ የሚለው?
ታዲያ አፍታም ሳትቆይ እቴቴ
እቴቴ የጎረቤቴ
ዘረረረረር አድርጋ ልብሷን፣
ውሃ ውሃ እሚል ጨርቋን
ሣሩም ላይ ጉቶውም ላይ
በየቅርንጫፉም ላይ፣
ትለኛለች እኔን
እኔን ትንሹን ቡጡን
ውሃ ውስጥ የምንቦራጨቀውን፤
“እስቲ ደግሞ ተራዬን
እኔ ልታጠብ ገላዬን
አፋፏ ላይ ቁምልኝ
መንገድ መንገዱን እይልኝ
ሰው አለመምጣቱን ጠብቅልኝ … ”
እሺ ብዬ ዲዲዲዲ ወዳፈፏ
እሷም ፈታ ፈታ መቀነቷን
ገልመጥ ገልመጥ ዙሪያዋን
ፍትት ፍትት ፍትትትት ሻሿን
ግልብ ግፍፍ ውልቅልቅ ቀሚሷን
ሙልጭልጭልጭ ውስጥ ልብሷን
ብቅ ጥልቅ ብቅ ጥልቅ ራቁቷን፤
እኔም ዐየት - ዐየት መንገዱን
ገረፍ ገረፍ - ደሞ ወንዙን
እቴትዬ እርቃኗን የምትንቦራጨቅበቱን፤
ጸጉሯን ወደ ኋላዋ እየሳበች እየጎተተች
ጡቶቿን ለፀሐይዋ እየሰጠች እየለጠጠች
ኋላዋንም ነካ ነካ — ነካ እያደረገች
ስትጫወት እያሾለቅሁ አየት … አየት
ደግሞ መንገዱንም መልከት… መልከት፤ …
ታዲያ በጉርምስና ዘመኔ
ያ የጥንቱ ትይታ ተመልሶ መጣ ካይኔ
የረሳኋት እቴቴ
ብዥ ትልብኝ ጀመር ከፊቴ፤…
ወንዙ ውስጥ ስትንቦራጨቅ
ጸጉሯን ወደ ኋላዋ እየሳበች እየጎተተች
ጡቷን ለፀሐይዋ እየሰጠች እየለጠጠች
ኋላዋንም ነካ – ነካ እያደረገች፤…
------------
1964
(ከ"የብርሃን ፍቅር" ፣ ገፅ 42 የተወሰደ)