Get Mystery Box with random crypto!

ትምህርት ሚኒስቴር የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የሚሰጥበትን ቀን እንዲያሳውቅ ተጠየቀ፡፡ ባሕር ዳር | Amhara Media Corporation

ትምህርት ሚኒስቴር የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የሚሰጥበትን ቀን እንዲያሳውቅ ተጠየቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 24/2013 ዓ.ም (አብመድ) ትምህርት ሚኒስቴር የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የሚሰጥበትን 'ቁርጥ' ያለ ቀን እንዲያሳውቅ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ። ሚኒስቴሩ “ቀኑን ለመቁረጥ ለፈተናው የሚያስፈልጉት 400 ሺህ 'ታብሌቶች' ወደ አገር ውስጥ መግባት አለባቸው” ብሏል።
የምክር ቤቱ የግብርና፣ የአርብቶ አደርና አካባቢ ጥበቃ ቋሚ ኮሚቴ ሚኒስቴሩ በአርብቶ አደርና ልዩ ድጋፍ በሚሹ ክልሎች ያከናወነውን የሁለተኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ገምግሟል። ሚኒስቴሩ ለቋሚ ኮሚቴው ያቀረበው ሪፖርት እንደሚያሳየው በአፋር፣ በሶማሌ፣ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ በኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች አርብቶ አደር አካባቢዎች ትምህርት ለማስጀመር ሲሰራ ቆይቷል።
በእነዚህ አካባቢዎች የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከላከያ ግብዓቶች ተሟልተው ትምህርት ተጀምሯል።
በክልሎቹ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎች የተገነቡ ሲሆን የመምህራን እጥረት ችግርን ለማቃለልም በጎ ፈቃደኛ መምህራን እየተሳተፉ ነው።
ይሁን እንጂ በአካባቢዎቹ ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት በአማካይ 30 በመቶ ያህሉ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው አልተመለሱም ነው የተባለው። የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ አልማዝ መሰለ እንደሚሉት፤ በሕዝብ ንቅናቄ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ማድረግ ያስፈልጋል።
ከዚህ ጎን ለጎን ከክልሎችና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር መጀመር እንዳለበት ጠቁመዋል። እንደ ወይዘሮ አልማዝ ገለጻ፤ ድጋፍ የሚሹትን ጨምሮ በሌሎችም አካባቢዎች የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የሚሰጥበት ቀን በግልጽ ሊቀመጥ ይገባል።
ይህም ተማሪዎች ራሳቸውን ለፈተና እንዲያዘጋጁ ያደርጋል፤ ለወላጆችም እፎይታ ይሆናል ነው ያሉት። በሌላ በኩል የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና ውጤት በአፋጣኝ ተገልጾ የ9ኛ ክፍል ትምህርት መጀመር እንዳለበት አሳስበዋል።
የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማቲዮስ በበኩላቸው "ፈተናው የሚሰጥበትን ቀን ለማሳወቅ ለፈተናው የሚያስፈልጉት 400 ሺህ 'ታብሌቶች' ወደ አገር ውስጥ አልገቡም" ብለዋል።
ይህ የሆነው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በፈጠረው ዓለምአቀፍ ተፅዕኖ መሆኑን ገልጸው፤ "በቅርቡ የማጓጓዙ ስራ ይጀመራል" ብለዋል።
ለዚህም ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር እንደሚሰራና 'ታብሌቶቹ' ወደ አገር ሲገቡ ፈተናው የሚሰጥበት ቀን እንደሚወሰን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል። የፈተና አሰጣጥ ሂደቱን ለማቀላጠፍ በ1 ሺህ 500 የፈተና ጣቢያዎች አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው የ8ኛ ክፍል ፈተና ውጤት በአፋጣኝ እንዲገለፅ ክልሎች እንደሚደግፉ፤ ልዩ ድጋፍ በሚሹ አካባቢዎችም የትምህርት ቤት ምገባውን በቀጣዩ ወር አጋማሽ ለመጀመር መታቀዱን አብራርተዋል። በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከመግባቱ በፊት ትምህርት ሚኒስቴር 26 ሚሊዮን ያህል ተማሪዎችን ሲያስተምር ቢቆይም ዘንድሮ በርካታ ተማሪዎች ወደ ትምህርታቸው እንዳልተመለሱ ተገልጿል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በፌስቡክ https://bit.ly/2UwIpCw
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m