Get Mystery Box with random crypto!

የሩዝ ምርትን እሴት በመጨመር ወደ ገበያ በማቅረባቸው ተጠቃሚ መሆናቸውን ነጋዴዎች ተናገሩ፡፡ ባሕ | Amhara Media Corporation

የሩዝ ምርትን እሴት በመጨመር ወደ ገበያ በማቅረባቸው ተጠቃሚ መሆናቸውን ነጋዴዎች ተናገሩ፡፡
ባሕር ዳር፡ ጥር 24/2013 ዓ.ም (አብመድ) ሩዝ በአማራ ክልል በደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ፣ ሊቦከምከም እና ደራ ወረዳዎች በብዛት ይመረታል፡፡ ካሁን ቀደም ሩዝ በባህላዊ መንገድ በመቀነባበሩ አርሶ አደሮችም ሆኑ ነጋዴዎች ማግኘት ያለባቸውን ጥቅም እያገኙ አልነበረም፡፡
ሚዳ እምርታ በተሰኘ ፕሮጀክት በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር ዞን ከሩዝ አምራች ወረዳዎች ጋር በጥምረት መሥራት በመጀመሩ አምራቾች፣ ነጋዴዎችና አቀነባባሪዎች የተሻለ ውጤት እያስመዘገቡ ነው ተብሏል፡፡
በባሕር ዳር ከተማ በዘርፉ የተሰማሩ አቀነባባሪዎች ምርታቸውን እንዲያስተዋውቁ አውደ ርዕይ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ በአውደ ርዕዩ ከተገኙት መካከል ወጣት ግዛው ተሰማ አንዱ ነው፡፡ “የነጭ ወርቅ” የተባለ ሩዝ አቀነባባሪ የአክሲዮን ማኅበር አስተባባሪ ነው፡፡ በሚዳ እምርታ ፕሮጀክት ታቅፎ ስልጠናና የማቀነባበሪያ ማሽን በብድር በማግኘቱ ጥራት ያለው ምርት ለሸማቹ እንዲያቀርብ አስችሎታል፡፡ ግዛው ፕሮጀክቱ የገበያ ትስስር ስለፈጠረላቸው የተሻለ ገቢ እያገኘ እንደሆነም ነግሮናል፡፡
በዘመናዊ መንገድ የተዘጋጀው ሩዝ የተሻለ ተፈላጊነት አለው ብሏል፡፡
ወጣት ፍቅር አቻምየለህ በደቡብ ጎንደር ዞን ፎገራ ወረዳ የወረታ ከተማ ነዋሪ ናት፡፡ ፍቅር በሜዳ ፕሮጀክት ያገኘችው ስልጠና ሩዝ የምግብ ይዘቱ ሳይለቅ ለተጠቃሚው እንድታቀርብ አስችሏታል፡፡
ፍቅር እንዳለችው አውደ ርዕዩ ያቀረበችውን የሩዝ ምርት ለማኅበረሰቡ እንድታስተዋውቅ ረድቷታል፡፡
አቶ በድሉ ክፍሌ በሀገር ውስጥ የማይገኙ አዳዲስ የሩዝ መፈልፈያ እና ማዘጋጃ ማሽኖችን ጥሬ እቃውን ከውጭ በማስመጣት ሀገር ውስጥ በመገጣጠም ለሩዝ አምራቾች እና አቀናባሪዎች ያስረክባሉ፡፡
እንደ አቶ በድሉ ገለጻ ሩዝ አቅራቢዎች የተቀነባበረ እና የታሸገ (ስቲም ወይም ፓርቦይልድ) የሚባለውን ሩዝ የሚያመርቱት እሳቸው በሠሩት ማሽን ነው፡፡ ሩዝ በዘልማድ ሲፈለፈል ይሰባበራል፤ የምግብ ይዘቱም ይቀንሳል ነው ያሉት አቶ በድሉ፡፡ ዘመናዊ መፈልፈያ እና ማቀነባበሪያ ማሽን በመጠቀም የሩዝ ምርትን በተሻለ መልኩ ማስተዋወቅ ይቻላል ብለዋል፡፡
በሚዳ እምርታ ፕሮጀክት የፕሮጀክት ትግበራ ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ዓለም ፀሐይ እጅጉ ፕሮጀክቱ በደቡብ ጎንደር ዞን በሦስት ወረዳዎች በፎገራ፣ ሊቦከምከም እና ደራ ወረዳዎች የሩዝንና የአትክልት ምርቶችን መሰረት አድርጎ እየሠራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ወይዘሮ ዓለምፀሐይ እንዳሉት ፕሮጀክቱ የተሻሻሉ የሩዝ ዝርያዎችን በማስተዋወቅ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ኢንተርፕራይዞችን በማቋቋም በምርቱ ላይ እሴት ጨምረው ለገበያ እንዲያቀርቡ እያደረገ በመሆኑ አምራቾች፣ ነጋዴዎችና አቀነባባሪዎች የተሻለ ገቢ እያገኙ እንደሆነም ነግረውናል፡፡
ሚዳ እምርታ ፕሮጀክት ለአቀነባባሪዎችና ለነጋዴዎች የብድር አገልግሎት በማመቻቸት ምርቱ በብዛት የሚቀርብበትን መንገድ እያመቻቸ እንደሆነም ሥራ አስኪያጇ ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአብመድ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2HYJBLZ
በዌብሳይት www.amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m