Get Mystery Box with random crypto!

ዶ/ር ሹመቴ ግዛው ከ “ኢንሳ” ዳይሬክተርነታቸው ተነሱ ካለፈው ህዳር ወር 2014 ጀምሮ የኢንፎር | አማራ መረጃ ማዕከል (Amhara Information Center)

ዶ/ር ሹመቴ ግዛው ከ “ኢንሳ” ዳይሬክተርነታቸው ተነሱ

ካለፈው ህዳር ወር 2014 ጀምሮ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢንሳ) ምክትል ዋና ዳይሬክተር ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት አቶ ሰለሞን ሶካ፤ ተቋሙን በዋና ዳይሬክተርነት እንዲመሩ ተሹመዋል።

አቶ ሰለሞን የመሪነት ቦታውን የተረከቡት “ኢንሳ”ን ለሁለት ዓመት ከመንፈቅ ገደማ የመሩትን ዶ/ር ሹመቴ ግዛውን በመተካት ነው።

አቶ ሰለሞን ሶካ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሆነ መሾማቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ቢያረጋግጡም ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ግን ተቆጥበዋል።

ከማይክሮ ሊንክ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኮሌጅ በሶፍት ዌር ምህንድስና የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙት አቶ ሰለሞን፤ በ“ኢንሳ” ከሶፍት ዌር መሐንዲስነት እስከ ቡድን መሪነት ባሉት ቦታዎች አገልግለዋል።

አዲሱ ተሿሚ በኮምፒውተር ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ የማስተርስ ዲግሪያቸውን ያገኙት ከቻይና ኤሌክትሮኒክ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ነው።

አቶ ሰለሞን ከዘጠኝ ወር በፊት የምክትል ዳይሬክተርነት የኃላፊነት ቦታ ተሰጥቷቸው ወደ “ኢንሳ” ከመመለሳቸው በፊት፤ “ቴክ ማሂንድራ” በተባለ የህንድ የመረጃ ቴክኖሎጂ አገልግሎት እና አማካሪ ድርጅት የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ ሆነው ለአምስት ዓመታት ሰርተዋል።

ኃላፊነታቸውን ለአቶ ሰለሞን ያስረከቡት ዶ/ር ሹመቴ ግዛው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደርን ከጥር 2012 ጀምሮ ለሁለት ዓመት ከመንፈቅ ገደማ በዋና ዳይሬክተርነት መርተውታል።

ዶ/ር ሹመቴ ወደ ኢንሳ ከመምጣታቸው በፊት ለስምንት ወራት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በሚኒስትር ማዕረግ ኃላፊ ሆነው ሰርተዋል። ዶ/ር ሹመቴ የዲላ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝዳንትም ነበሩ።