Get Mystery Box with random crypto!

በጎንደር በተከሰተው የፀጥታ ችግር ከፍተኛ ሚና የተጫወቱ 373 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለዋል - | የአማራ ተማሪዎች ማህበር [አተማ]

በጎንደር በተከሰተው የፀጥታ ችግር ከፍተኛ ሚና የተጫወቱ 373 ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ውለዋል - የአማራ ክልል ሰላም ግንባታ እና የሕዝብ ደህንነት ቢሮ
**

በጎንደር በተከሰተው የፀጥታ ችግር ከፍተኛ ሚና የነበራቸው 373 ግለሰቦች በፀጥታ መዋቅሩ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የአማራ ክልል ሰላም ግንባታ እና የሕዝብ ደህንነት ቢሮ አስታወቀ።

ግለሰቦቹ በቡድን በመንቀሳቀስ ለዝርፊያ እና ለቃጠሎ ተሰማርተው በመገኘት እና የግጭቱ ፊትአውራሪ በመሆን ለተፈጠረው ግጭት ምክንያት መሆናቸውን የቢሮው ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ጉዳዩ እንደተከሰተ ፈጣን እርምጃ ባለመውሰድ፣ ትዕዛዝ በመጠበቅ እና በቸልተኝነት በመመልከት ለችግሩ መባባስ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሚና በተጫወቱ የፀጥታ መዋቅር እና የፖለቲካ አመራር ላይም ከእስር ጀምሮ በሕግ ለመጠየቅ እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

በጎንደር ከተማ የፀጥታ ችግሩ እንዲያገረሽ የሚሠሩ ኃይሎችን እንደማይታገስ ነው የአማራ ክልል ሰላም ግንባታ እና የሕዝብ ደህንነት ቢሮ ያሳሰበው።

በከተማው የፀጥታ ችግር ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ እየተሠራ ስለሚገኘው የሰላም ማረጋገጥ ተግባራት ላይ መግለጫ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ሰጥተዋል።

ከሚያዝያ 18 ጀምሮ ለጎንደር የፀጥታ ችግር መነሻ እና መባባስ ምክንያቶችን ለመቅረፍ በርካታ ተግባራት እየተሠሩ ቢሆንም ከውስጥ እና ከውጭ፣ ማኅበራዊ ሚዲያ ጭምር በሚታየው ገፊ ምክንያቶች አለመረጋጋቱ እስከ ትናንት ሚያዝያ 20 ድረስ ቀጥሎ ከ20 በላይ የንግድ እና የመኖሪያ ቤቶች በመካከለኛ እና ከፍተኛ ሁኔታ ቃጠሎ መከሰቱን እንዲሁም 11 ቤቶች በከፊል እና በሙሉ መዘረፋቸውን ገልጸዋል።

በጉዳቱ እስከ አሁን ከሁለቱ እምነቶች 14 ዜጎች ሕይወታቸው ማለፉን እና ከእዚህ ውስጥ 7 አስከሬኖች ቤተሰቦቻቸው የሆስፒታል መረጃዎችን በማቅረብ ወስደዋቸዋል።

ከቀላል እስከ ከፍተኛ የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው 118 ሰዎች ደግሞ ሕክምና ላይ እንደሚገኙ ኃላፊው ገልጸዋል።

በከተማው ከምሽት 1 ሰዓት ጀምሮ የተሽከርካሪ እና የግለሰብ እንቅስቃሴ ገደብን ጨምሮ የጦር መሣሪያ ይዞ መንቀሳቀስን፣ የፀጥታ መዋቅር አልባሳት ለብሶ መገኘት፣ ከከተማ የሚገባም ሆነ የሚወጣ መሣሪያ መከልከሉም ተገልጿል።