Get Mystery Box with random crypto!

የጎንደርን ሰላም ለማናጋት ጠላት የሸረበው ሴራ በማኅበረሰቡ እና በጸጥታ ኀይሉ ጥረት ሳይሳካ መቅረ | የአማራ ተማሪዎች ማህበር [አተማ]

የጎንደርን ሰላም ለማናጋት ጠላት የሸረበው ሴራ በማኅበረሰቡ እና በጸጥታ ኀይሉ ጥረት ሳይሳካ መቅረቱን የክልሉ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ገለጸ።
***
በጎንደር ከተማ የተፈጠረውን የጸጥታ መደፍረስ አስመልክቶ የአማራ ክልል ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኀላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው ለአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ግጭቱ የተፈጠረው በጎንደር ከተማ የአንድ ታላቅ የሃይማኖት አባት ሥርዓተ ቀብር በሚፈፀምበት ወቅት ግለሰቦች ባነሱት አለመግባባት እንደሆነ አስረድተዋል።

አቶ ደሳለኝ እንዳሉት ግጭቱ የተፈጠረው የክርስትና እና የእስልምና እምነት በሚያመልኩባቸው አዋሳኝ ቦታዎች ላይ ለሥርዓተ ቀብር የሚሆን ድንጋይ ለማንሳት በነበረው ሂደት ሀብቱ የኛ ነው በሚል ግጭቱ መነሳቱን ገልጸዋል።

በግለሰቦች የተነሳው አለመግባባት የተለየ ተልዕኮ በነበራቸው አካላት ሰፍቶ የቡድን መልክ በመያዝ የከተማዋን ጸጥታ ለማድፍረስ መሞከሩን ነው ያስረዱት።

የሁለቱ እምነት ተከታዮች የቆየ ጠንካራ የመተሳሰብና የመረዳዳት ባህል እንዳላቸው የገለጹት ኀላፊው ጉዳዩ በምክክር እና በመግባባት የሚፈታ ቢሆንም ጠላት ጉዳዩን ለማስፋት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል ነው ያሉት።

የተለየ ተልዕኮ የነበረው ቡድን አጋጣሚውን በመጠቀም አካባቢው ወደ አለመረጋጋት እንዲገባ ቢሞክርም በሁለቱ እምነት ተከታይ ወጣቶች እና በፀጥታ ኀይሉ ጥረት ጉዳዩ ሳይሳካ መቅረቱን ነው ለአሚኮ የተናገሩት።

አቶ ደሳለኝ ጉዳዩን ለማረጋጋት የተቻለ ቢሆንም አሁንም ችግር ለመፍጠር የሚሞክር አካል ካለ ያለምህረት ሕጋዊ እርምጃ የፀጥታ ኀይሉ እንዲወሥድ መታዘዙን አስረድተዋል። መረጃው የአሚኮ ነው።