Get Mystery Box with random crypto!

ወዳጄ ሆይ! ኃጢአተኛ ከኾንህ በደልህን ትናዘዝ ዘንድ ወደ ቤተ ክርስቲያን ና፤ ጻድቅም ከኾንህ ከጽ | 💠አምደ ሐይማኖት💠ዘ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ⛪️

ወዳጄ ሆይ! ኃጢአተኛ ከኾንህ በደልህን ትናዘዝ ዘንድ ወደ ቤተ ክርስቲያን ና፤ ጻድቅም ከኾንህ ከጽድቅ [ጎዳና] እንዳትወድቅ ወደ ቤተ ክርስቲያን ና፤ ቤተ ክርስቲያን የኃጥኡም የጻድቁም ወደብ ናትና፡፡

ኃጢአተኛ ነህን? ተስፋ አትቁረጥ፤ ወደ ቤተ ክርስቲያን መጥተህም ንስሐ ግባ፡፡ ኃጢአት ሠርተሃልን? እንግዲያውስ እግዚአብሔርን “በድያለሁ” በለው፡፡

እስኪ ንገረኝ! “በድያለሁ” ብለህ ለመናዘዝ ምን ውጣ ውረድ፣ ምን ዓይነት የሕይወት መርሕ፣ ምንስ መከራ አለው? “በድያለሁ” ብሎ አንዲት ቃል ለመናገር ክብደቱ ምኑ ላይ ነው? ምናልባት [ኃጢአት ሠርተህ ሳለ] በደለኛ አይደለሁም የምትል ከኾነ ዲያብሎስም አንተን አይወቅስህም፡፡ [በድያለሁ ብለህ ንስሐ የምትገባ ከኾነ ግን] ይህን [ዲያብሎስ ሊወቅስህ እንደሚችል] አስቀድመህ አስብ፡፡ …

ስለዚህ ክብርህን እንዳይወስድብህ ለምን አትከለክለውም? ለቅጽበት ያህልስ እንኳን የማይተኛ ከሳሽ እንዳለህ ዐውቀህ ለምን በደልህን ተናዝዘሃት አታስወግዳትም?

ኃጢአት ሠርተሃልን? እንግዲያውስ ወደ ቤተ ክርስቲያን መጥተህ እግዚአብሔርን “በድያለሁ” ብለህ ንገረው፡፡ እኔ ከዚህ ውጪ ከአንተ የምፈልገው ሌላ ምንም ነገር የለኝም፡፡
መጽሐፍ ቅዱስም፡- “ንግር አንተ ኃጣውኢከ ቅድመ ከመ ትጽደቅ - ትከብር ዘንድ አንተ አስቀድመህ ኃጢአትህን ተናገር” ይላል (ኢሳ.43፡26)፡፡ [ስለዚህ] ኃጢአትህን ታስወግዳት ዘንድ ተናዘዛት፡፡

ይህን ለማድረግ ውጣ ውረድ የለውም፤ ዙሪያ ጥምጥም የቃላት ድርደራም አያሻህም፤ ገንዘብ መክፈል አያስፈልግህም፤ ወይም እነዚህን የመሰሉ ሌሎች ነገሮች አያስፈልጉህም፡፡ አንዲት ቃል ተናገር፤ በደልህን በአንቃዕድዎ አስባት፤ “በድያለሁ” ብለህም ተናዘዛት፡፡