Get Mystery Box with random crypto!

አተኳኮስ ትጣለህ!! እናተዬ ዘርሮ ነው የጣለው እኮ። አዲስ አበባ ልደታ አካባቢ የጀበና ቡና ለመ | Amde Ezra

አተኳኮስ ትጣለህ!!

እናተዬ ዘርሮ ነው የጣለው እኮ። አዲስ አበባ ልደታ አካባቢ የጀበና ቡና ለመጠጣት ከናቱ ማህጸን እንደወጣ እንደ መጨረቅ እንቦሳ ከሚያረገርግ እግረ-ተከል የፕላስቲክ ወንበር ላይ ተቀምጫለሁ።

ፊት...ለፊቴ ደግሞ ወጣቶች ከበዋል። ወጣቶቹ በወሪያቸው እንደ ተረዳሁት የተለያየ የብሔር ማንነት ያላቸው ናቸው። ከመካከላቸውም ህሉፍ የሚባል የትግራይ ብሔር ተወላጅ ነበረ።

የህሉፍን ሥምም ሆነ የብሔር ማንነቱን ማወቅ የቻልኩት ከበው ካሉት ወጣቶች መካከል አንዱ ስሙን ጠርቶ ግብረመልስ ሲሰጠው ነው። ህሉፍ በክርክሩ እምብዛም ተናጋሪ አልነበረም። በአብዛኛው አድማጭ ነበር።

የመከራከሪያም በሉት የመወያያ ርዕሳቸው ደግሞ ስፖርታዊ ነው። ስፖርታዊ ርስዕሱ ከአገር ውስጥ እስከ ውጪ አገራት ያሉትን ክለቦች ያዳረሰ ነበር። ከአገር ውስጥ እነቡና፣ እነቅዱስ ጊዮርጊስ፣ እነፋሲል...ከውጪ ደግሞ እነማንችስተር ዩናይትድ፣ እነአርሴናል፣ እነማንችስተር ሲቲ...የመሳሰሉት የእግርኳስ ክለቦች መነጋገሪያ ነበሩ። በተለይ በተጫዋቾች የዝውር ገቢያው ላይ ለሚደግፏቸው ክለቦች ከፔፕ ጋርዲዮላ፣ ከሚካኤል አርቴታ፣ ከእሪክ ቲህናግ...በላይ ሆነው "ምን አለ እከሌ የሚባለውን ተጫዋች ብንገዛው? እሱን እማ መግዛት ይኖርብናል!! አንዴ መልስ የሌለው ጥያቄ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ፓውንድ መዥላጭና ወሳኝ ሆነው ይደመድማሉ። ለእየሚደግፉት ክለባቸው ይስማማል የሚሏቸውን ተጫዋቾች እያነሱ "በምኞት አይከለከል።" ብሂል ይብከነከናሉ።

እንግዲህ በዚህ ክርክር መሃል ላይ ነው ሚሳኤሉ የተወነጨፈው። ተኩሱ የፈነዳው። ምን አለ ህሉፍ እስከመጨረሻው አድማጭ ሆኖ ቢቀጥል ኖሮ ያስብላል። ህሉፍ ምላሱን ሲበለዋ፣ ሲያቅለበልበው...

"እውነት ለመናገር ዲክላር ራስ ግን 105 ሚሊዬን ፓውንድ የሚያወጣ ተጫዋች ሆኖ ነው አርሴናል ሊገዛው የተስማማው?" ብሎ በጥያቄ ጀምሮ የሚካኤል አርቴታን ቀሽምነት ለማብራራት አፉን እያሾለ ሳለ...

አንዱ የአርሴናል ደጋፊ የሆነ ወጣት:- የህሉፍን ንግግር ከምላሱ ላይ አፈፍ አድርጎ
"ማነህ? ህሉፉ ቆይ...ቆይ...አንድ ጊዜ ቆዬኝ እማ? እየውልህ ህሉፉ አንተ #ስለፓራ #ኦሎፒክ ማውራት ስንጀምር ያ...ኔ በደንብ ማብራሪያ ትሰጣለህ።" ብሎት እርፍ።

ከዚህ በላይ የምላስ ተኩስ አለ እንዴ? የእውነት አተኳኮስ ትጠላለህ