Get Mystery Box with random crypto!

ኦፌኮ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተማጽኖ አቀረበ አምባ ዲጂታል፤ ረቡዕ ነሐሴ 25፣ 2014 ― የኦሮሞ | Amba Digital - አምባ ዲጂታል

ኦፌኮ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተማጽኖ አቀረበ

አምባ ዲጂታል፤ ረቡዕ ነሐሴ 25፣ 2014 ― የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ፓርቲ የኢትዮጵያ ሕዝብ ‹‹ግጭት ከሚያባብሱ ንግግሮች በመታቀብ ችግሩን ለማርገብ እና ለመፍታት›› እንዲተባበር ተማጽኖ ያቀረበው ዛሬ ረቡዕ ነሐሴ 25፣ 2014 ባወጣው ወቅታዊ መግለጫ ነው፡፡

ፓርቲው በዚህ ተማጽኖው ለገዥው ፓርቲ፣ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ የመገናኛ ብዙኃን፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ባለሞያዎች እና አክቲቪስቶች ተመሳሳይ መልእክት ሰዷል፡፡

ኦፌኮ በዛሬው መግለጫው፤ ‹‹ሐገራችንን ለከፍተኛ ሰብአዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ኪሳራ የዳረጋት›› ነው ባለው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ማገርሸት እና ‹‹በኦሮሚያ የቀጠለው ግጭት በመባባሱ›› ማዘኑን ገልጧል፡፡

የፓርቲው መግለጫ ጦርነት ‹‹ውስብስብ›› ነው ላለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግር መፍትሔ ሊሆን እንደማይችል አጽንኦት ሰጥቶት አልፏል፡፡ አክሎም እነዚህ ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት ‹‹በእውነተኛ እና ሁሉን አቀፍ ድርድር ብቻ›› መሆኑን የገለጸው ኦፌኮ፤ በሁሉም ወገን የሚገኙ ተፈላሚ ኃይሎች ‹‹ግጭቱን በማብረድ ሰለማዊ መፍትሔ እንዲሹ›› ጠይቋል፡፡

ኦፌኮ በመግለጫው ክልላዊ እና ዓለም አቀፍ አሸማጋዮች አንጻራዊ መረጋጋት በነበረባቸው ባለፉት ወራት ተፋላሚ ወገኖች ወደ ድርድር ጠረጴዛ ለማምጣት እና አጠቃላይ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማስፈን መጠቀም ባለመቻላቸው ‹‹ከፍተኛ ፀፀት›. እንደተሰማው የገለጸ ሲሆን፣ አሁንም በግጭት በተጎዱ አካባቢዎች ‹‹ተጨማሪ ሞት እና የዜጎችን መከራ ለማስቀረት›› ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ‹‹በንቃት እና በተቀናጀ መልኩ እንዲረባረብ›› ጥሪ አቅርቧል፡፡

በሌላ በኩል ኦፌኮ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኦሮሚያ ተስፋፍቷል ያለውን ጦርነት ‹‹ለመፍታት ቀርቶ እውቅና ለመስጠት አለማቻሉን›› አሳስቦኛል ብሏል፡፡ በክልሉ በተለይም በግጭት እና በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች ያለው ሰብአዊ ሁኔታ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ መድረሱን በመግለጽ፤ ዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ‹‹እየተባባሰ ያለው ግጭት በአስቸኳይ እና ሰላማዊ በሆነ መልኩ በድርድር እንዲፈታ›› ሁኔታዎችን ያመቻች ብሏል፡፡

ላለፉት አምስት ወራት ጋብ ብሎ የነበረው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ካገረሸ ዛሬ አንድ ሳምንት አስቆጥሯል፡፡