Get Mystery Box with random crypto!

ሳፋሪኮም በስድስት ሳምንታት ውስጥ አዲስ አበባ ላይ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ተባለ አምባ | Amba Digital - አምባ ዲጂታል

ሳፋሪኮም በስድስት ሳምንታት ውስጥ አዲስ አበባ ላይ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ተባለ

አምባ ዲጂታል፤ ረቡዕ ነሐሴ 25፣ 2014 ― በኢትዮጵያ ሁለተኛውን የቴሌኮም ፈቃድ በጨረታ አሸንፎ ሥራ የጀመረው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ፣ ሳፋሪኮም በስድስት ሳምንታት ውስጥ አዲስ አበባ ላይ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ተብሏል፡፡

ኩባንያው በኢትዮጵያ ለራሱ የመጀመሪያ የሆነውን የቴሌኮም አገልግሎት ሰኞ ነሐሴ 23፣ 2014 በድሬዳዋ ከተማ በራሱ መሠረተ ልማት ማስጀመሩ ይታወቃል፡፡ ሳፋሪኮም በቀጣይም ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በሌሎች የአገሪቱ ከተሞች እንደሚጀምር ገልጧል፡፡

ሪፖርተር ጋዜጣ የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ አንዋር ሶሳን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ሳፋሪኮም በዚሁ መሠረት በመጪዎቹ ስድስት ሳምንታት ውስጥ በተመሳሳይ የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት በአዲስ አበባ ከተማ ይጀምራል፡፡

አንዋር ሶሳ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ሲካሄድ የነበረው የመሠረተ ልማት ስምምነት በቶሎ ባለማጠናቀቁ አገልገሎቱን ለማስጀመር ጊዜ እንደወሰደባቸውም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ባልቻ ሬባ እንደገለጹት፣ ኩባንያው እስከ ሚያዚያ 2015 ባለው ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያን 25 በመቶ የኅብረተሰብ ክፍል የሚሸፍን አገልግሎት እንዲያቀርብ ውል ገብቷል፡፡ ኩባንያው በዚሁ በተጠቀሰው ጊዜ የሚጠበቅበትን ካላሟላ ኦዲት ተደርጎ በገባው ውል መሠረት ቅጣት ይጣልበታል፡፡ ይሁን አንጂ የቴሌኮም ኩባንያው አሁን በተሳካ ሁኔታ ሥራውን እያከናወነ እንደሆነ አቶ ባልቻ ገልጸዋል፡፡

የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ እንደሚሉት ኩባንያቸው የዋጋ ጦርነት ውስጥ የመግባት ፍላጎት እንደሌለው ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ ፈጣን የቴሌኮም አገልግሎት እንደሚያቀርብ አስረድተዋል፡፡

በድሬዳዋ ከተማ የኔትወርክ ሙከራ በ2G፣ በ3G እና በ4G ኔትወርኮች የጀመረ ሲሆን፣ ደንበኞች በ07 በሚጀምረው የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ መስመር የስልክ ቁጥሮቻቸውን መርጠው ሲም ካርድ መግዛት እንደሚችሉ ኩባንያው አስታውቋል፡፡

በድሬዳዋ ከተማ አገልግሎት በጀመረው የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ የሙከራ ኔትወርክ ደንበኞች ዳታ መጠቀም፣ ጥሪዎችና የጽሑፍ መልዕክቶችን ከሳፋሪኮም ኢትዮጵያና ከኢትዮ ቴሌኮም ደንበኞች ጋር መለዋወጥ፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ጥሪዎችን ማድረግ እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡ ሳፋሪኮም በደቂቃ 50 ሳንቲም እንደሚያስከፍልም ታውቋል፡፡
የመጀመሪያው የግል የቴሌኮም ኦፕሬተር ሆኖ በኢትዮጵያ የተመዘገበው ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ላገኘው የአገልግሎት ፈቃድ 850 ሚሊዮን ዶላር ለመንግሥት መክፈሉ ይታወሳል፡፡