Get Mystery Box with random crypto!

ጅብ አይበላሽ ጫማ-በቡትቶ ጨርቆች ከካብ ተደርድራ በማገር ከቆመች ቋሚዋም ጣራዋም ፍቅር ፍቅር ሚሸ | የዮቶር ልጅ - አምባዬ ጌታነህ

ጅብ አይበላሽ ጫማ-በቡትቶ ጨርቆች
ከካብ ተደርድራ በማገር ከቆመች
ቋሚዋም ጣራዋም ፍቅር ፍቅር ሚሸት
ከተከዜ ወዲህ
ከሎሚው ወደዚያ አለች ውብ የሳር ቤት
በዚያች የሳር ጎጆ
ችግር ያጠቆረው ወዝ ደምቆ ይታያል
ርሀብ በፈገግታ
በሳት ዳር ጨዋታ በሳቅ ይታለፋል
የእናት ተስፋና ቃል
እንደ ሙሴ በትር
የኑረትን ባህር ከፍሎ ያሻግራል
የተስፋ ምናቦች
የህልም ሀሳቦች በወግ ተሰድረው
ነፍስን በሚያሞቁ
ቀልብን በሚወስዱ ቃላቶች ታጅበው
ለልጅ ልጅ የሚተርፍ
የፅናት ውብ ዋጋ ይተረክበታል
የትዕግስትን ጥግ
በኑሮ መሠላል ዜማ ተቀምሮ ይዘመርበታል
እታተይ ማጀቱን
አባባ ማሳውን
እህቴም እንደ ልጅ
የእንጨት ሰበራውን
ወንድሜም እንደ ልጅ
በግ እረኝነትን
እኔ ያስኮላውን
በቀልድ የተዋዛ ሞቅ ያለ ጨዋታ
የልጅነት ታሪክ የፍቅር ትዝታ
የእቃቃ ሚስትነት
የእቃቃ ባልነት
በትዝታ ተረክ በፍቅር ተጠቅሶ ከማዕድ ይቀርባል
የልጅነት ጊዜ ያፍላ ፍቅር ወጎች ይተረኩበታል።

አምባዬ ጌታነህ @Adwa1888